1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተማሪዎች ተቃዉሞ በጅማ ዩንቨርሲቲ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 15 2010

በጅማ ዩንቨርሲቲ ካለፈዉ ሳምንት ጀምሮ የመማር ማስተማር ስራ ሙሉ ለሙሉ መቆሙን አንዳንድ የዩንቨርሲቲዉ ተማሪወች ገለፁ።ተማሪወቹ ትምህርታቸዉን ያቆሙት ሶማሌ ክልል በሚገኘዉ ጅጅጋ ዩንቨርሲቲ የኦሮሚያ ክልል ተማሪወች ሊመደቡ አይገባም በሚል ተቃዉሞ ነዉ።

https://p.dw.com/p/2mUPU
Symbolbild US-Botschafter bei den UN - in Äthiopien
ምስል DW/E. Bekele

protest in Jimma University /Final/ - MP3-Stereo


ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንዳንድ የጅማ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች እንደገለፁት ባለፈዉ ሳምንት በዩንቨርሲቲዉ ግቢ ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጎ ነበር።ተማሪዎቹ ሰላማዊ ሰልፉን ያካሄዱት  በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል የተከሰተዉን ግጭት ተከትሎ በጅጅጋ ዩንቨርሲቲ ከተመደቡ የኦሮሚያ ክልል ተማሪዎች መካከል የተወሰኑትን  የጅማ ዩንቨርሲቲ ተቀብሎ ያስተናግድ በሚል ነበር።
«ከዚህ ከሶማሌ ክልል ጋር ከተፈጠረ ችግር ጋር ተያይዞ ፤ሶማሌ ክልል ያሉ ተማሪዎች  ጅማ ዩንቨርሲቲ መቀበል አለበት የሚል ነዉ ተማሪዎቹ እያነሱት ያለዉ።ጅማ ዩንቨርሲቲ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ያድርግ ቢያንስ 1 ሽህ ተማሪወችን ይቀበል።ሌሎችም በኦሮሚያ ክልል ያሉ ዩንቨርሲቲወች የተወሰኑ ተማሪወችን ተከፋፍለዉ ወደ 5 ሺህ የሚደርሱ ተማሪዎች አሉ በግቢዉ/በጅጅጋ ዩንቨርሲቲ/ እነዚያ ተከፋፍለዉ  ይወሰዱ የሚል ነዉ የተማሪዉ ጥያቄ።የዩንቨርስቲዉ አስተዳደር የሚለዉ ከኔ አቅም በላይ ነዉ መፍታት አልችልም።ጉዳዩን ግን አስተላልፌያለሁ ነዉ የሚለዉ።»
ከሰላማዊ ሰልፉ በኋላ የዩንቨርስቲዉ አስተዳደር  ስብሰባ ጠርቶ ተማሪዎቹን ለማነጋጋር የሞክረ ቢሆንም  የተሰጠው ምላሽ አጥጋቢ አይደለም በሚል ተማሪዎቹ ስብሰባዉን ረግጠዉ ወጥተዋል ነዉ የተባለዉ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዩንቨርሲቲዉ የመማር ማስተማር ስራ ሙሉ ለሙሉ መስተጓጎሉን ነዉ ተማሪዎቹ የተናገሩት።
አንዳንድ የትምህርት ክፍሎችና ተማሪወች ትምህርት ለመጀመር ቢሞክሩም ከሌሎች የዩንቨርሲቲዉ  ተማሪወች  በተደረገባቸው ጫና  ትምህርት መቀጠል አልቻሉም ። 

Äthiopien Jimma Geschlossene Geschäfte
ምስል DW User via Whatsapp

«ማለት ክላስ የገቡ ተማሪዎች ነበሩ ።ባለፈዉ ሳምንት እነሱን ካስወጧቸዉ በኋላ ክላስ ሙሉ በሙሉ ቆሟል በቃ።ለምሳሌ ሜዲስን አካባቢ የገቡ ተማሪዎች ነበሩ። ጆግራፊ አካባቢ ያሉ ተማሪዎችም ገብተዉ ነበር ባለፈዉ ሳምንት ግን አስወጧቸዉ።»
በዩንቨርሲቲዉ ትምህርት ከመቋረጡ በስተቀር ተማሪዎቹ አሁንም ድረስ ግቢ ዉስጥ ሆነዉ የምግብና የመኝታ አገልግሎት እያገኙ  ናቸዉ ተብሏል።እንደተማሪዎቹ ገለጻ በጸጥታ በኩልም ቢሆን እስካሁን  የሚያሰጋ ነገር አልተፈጠረም። ትምህርት መቋረጡ እንዳሳሰባቸው ግን አልሸሸጉም።

«በቃ እስካሁን ድረስ ጸጥ ያለ ነገር ነዉ ያለዉ።የጸጥታ ሀይሎችም ቢሆን ወደ ግቢዉ አልገቡም ።የዩንቨርሲቲዉ ፕሬዝዳንት አልፈቀደም የሚል ነገር የተማሪዎች ህብረት አካባቢ ይወራል።እስካሁን ግን ምንም ነገር የለም። እኛ ግቢ ላይ ማለት ነዉ።ምግብ አልቆመም የቆመ ትምህርት ብቻ ነዉ።ግን አብዛኛወቻችን ትምህርት እንዲቀጥል እንፈልጋለን።»

ጉዳዩን በተመለከተ የዩንቨርሲቲዉን የአስተዳደር አካላት በስልክ ለማነጋገር ብንሞክርም ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታቸዉ እንዲመለሱ ጥረት እያደረግን ነዉ ከሚል አጭር ምላሽ ዉጭ ተጨማሪ ማብራሪያ ሊሰጡን አልፈቀዱም። 

ፀሐይ ጫኔ

አርያም ተክሌ