1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተሰደዱ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ስጋት

ሐሙስ፣ ነሐሴ 29 2006

በኢትዮጵያ ፍትሕ ሚኒስቴር መከሰሳቸውን ተከትሎ ሀገር ጥለው የተሰደዱ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የደኅንነት ስጋት ገጥሞናል ይላሉ። የጋዜጠኞቹ የደኅንነት ስጋት ተዓማኒ ከሆነ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት የኬንያ ፅ/ቤት ተናግሯል።

https://p.dw.com/p/1D7Kn
ምስል picture-alliance/dpa

አቶ ግዛው ታዬ የሎሚ መጽሔት ስራ አስኪያጅ ነበሩ። በመጽሔታቸው በወጡ ጽሁፎች ድርጅቱና ሥራ አስኪያጆቹ ሐሰተኛ ወሬ አትሞ በማውጣትና ሕዝብን በማነሳሳት ወንጀል' በሚሉ ሁለት ክሶች ሰኔ 6 ቀን 2006 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፍትሕ ሚኒስቴር መከሰሳቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤት ቆመውም ነበር። አቶ ግዛው ታዬ በመጀመሪያው የፍርድ ቤት ውሎ የተጠየቁትን የ50 ሺህ ብር ዋስትና አስይዘው ሌላ ቀጠሮ ከተቀበሉ በኋላ ግን በኢትዮጵያ አልቆዩም። እርሳቸው የኢትዮጵያ መንግስት ያስረኛል ወይም ሌላ ጠንካራ እርምጃ ይወስድብኛል በሚል ስጋት ከሃገር ለመውጣት ቢችሉም አሁን ባሉበት ሃገር የደህንነት ስጋት ተሰምቶኛል ይላሉ።

የአፍሮ ታይምስ ጋዜጣ ስራ አስኪያጅ አቶ ቶማስ አያሌው ና የጃኖ መጽሄት ስራ አስኪያጅ አቶ አስናቀ ልባዊም ከኢትዮጵያ ከተሰደዱ ጋዜጠኞች መካከል ይገኙበታል።አቶ ግዛው ታዬን ጨምሮ አሁን በጎረቤት ሃገር በአብሮነት የሚኖሩት ሶስቱ የግል-ፕሬስ ባለሙያዎች የደህንነት ስጋት ተደቅኖብናል ይላሉ።

Symbolbild Zeitungen in Ketten
ምስል Fotolia/parazit

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት የኬንያ ቢሮ ቃል አቀባይ ኢማኑኤል ኒያቤራ የደህንነት ስጋትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ከ14 የተለያዩ ሃገራት የመጡ ስደተኞች መኖራቸውንና ይናገራሉ። የሶስቱን ጋዜጠኞች የደህንነት ጉዳይ ተጠይቀው ሃሳብ ከመስጠት የተቆጠቡት ቃል አቀባዩ የተለያዩ ድጋፎች እንደሚያደርጉ ግን ተናግረዋል።

''የመጡት በተለያዩ ፈተናዎች ምክንያት ነው። ይህ የደህንነት ስጋትን ይጨምራል።ለምሳሌ የኢትዮጵያውያኑ ጉዳይ ተዓማኒ መሆኑን ለማረጋገጥ ቃለ-መጠይቅ እናደርግላቸዋለን። ጉዳያቸው ተዓማኒ ሆኖ ስናገኘው ደህነታቸው ሊጠበቅ የሚችልበትን እርምጃ እንወስዳለን። ለፖሊስ ጣቢያዎች በቀረቡና ደህንነታቸው የተጠበቀ አካባቢዎች እናስቀምጣቸዋለን። ልዩ ትኩረት እንዲያገኙም እናደርጋለን። ለምሳሌ አንዳንዶቹ ያለባቸው የደህንነት ስጋት በቋሚነት እስኪቀረፍ ድረስ ወደ አደባባይ መውጣት ስለማይችሉ የሚፈልጉትን አግልግሎት እና ምግብ እናቀርባለን።''

በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት ድረ-ገጽ መረጃ መሰረት 19,920 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በኬንያ የሚገኙ ሲሆን 11,670ው ጥገኝነት ፈላጊዎች ናቸው።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ