1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባበሩት መንግሥታትና የሚሌኒየሙ የልማት ግብ

ሐሙስ፣ መስከረም 5 1998
https://p.dw.com/p/E0eN
ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን ንግግር ሲያሰሙ
ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን ንግግር ሲያሰሙምስል AP

ሁኔታውን በዚህ መልክ ካጤኑት ወገኖች መካከል አንዱ የአውሮፓው ሕብረት ኮሚሢዮን የሚሌኒየሙ የልማት ዕቅድ በጉባዔው ላይ ዋናው የአጀንዳ ርዕስ እንዲሆን በዋዜማው ጥሪ ማድረጉ አይዘነጋም። የሚሌኒየሙ የልማት ግቦች ዕቅዱ ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ ዕውን ሊሆኑ ይችላሉ ወይ? በጉባዔው ጭብጥ ዕርምጃ የመታየቱስ ዕድል እስከምን ነው? እነዚህን ጥያቄዎች የሚያነሱት ታዛቢዎች ጥቂቶች አይደሉም።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን የዓባል መንግሥታት ተደራዳሪዎች ከሶሥት ሣምንታት ውጣ-ውረድ በኋላ ነገ ለፊርማ ለመሪዎች እንዲቀርብ በተስማሙበት ረቂቅ ሰነድ ላይ በጉባዔው ዋዜማ ምሽት ለጋዜጠኞች የሰጡት አስተያየት ብዙም የሚያበረታታ አልነበረም።

“የሰነዱን አንዳንድ ይዘቶች ጠንከር ባሉ ቃላት ለመግለጽ በወደድሁ ነበር። አንዳንድ መንግሥታት የራሳቸውን ጥቅም ማስቀደም መርጠዋል፤ አዋኪዎችም አልታጡም።” የኮፊ አናን አነጋገር የሚሌኒየሙን የልማት ግብ በተመለከተ በዓለም ሕብረተሰብ ዘንድ ሃሣብና ተግባር ገና ብዙ ተራርቀው እንደሚገኙ ነው አሁንም እንደገና የሚያረጋግጠው። የመንግሥታቱ መሪዎች ይህን ተገንዝበውት ከሆነ ባልከፋ!

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሚሌኒየም የልማት ዕቅዱ በቀሩት በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥ ከግብ ለማድረስ ከተነሣባቸው ዓላማዎች መካከል በታዳጊ አገሮች ድህነትን በግማሽ መቀነስ፣ የአንደኛ ደረጃ ትምሕርት በዓለም ላይ ለሁሉም መዳረሱ፣ የሚሞቱ ሕጻናትን ቁጥር በሁለት-ሶሥተኛ መቀነሱና የጾታ እኩልነትን ማስፈኑ፤ እንዲሁም የኤይድስን፣ የወባንና ሌሎች ደዌዎችን መስፋፋት መግታቱ ቀደምቱ ናቸው። ዕቅዱ የተፈጥሮ ጥበቃንና የሰሜን-ደቡቡን የሃብታም-ድሃ ክፍለ-ዓለማት የልማት ሽርክናን የማራመድ ዓላማንም ይዞ የተነሣ ነው። ይሁንና ሃሣቡ ከተጸነሰ ወዲህ ባለፉት አምሥት ዓመታት የተባለውን ገቢር ለማድረግ ብዙ የተነገረውን ያህል የረባ ዕርምጃ አልታየም።

እንዲያውም በወቅቱ ያለው አጠቃላይ ግንዛቤ ብዙዎች ታዳጊ አገሮች ለዕቅዱ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ፤ ማለትም እ.ጎ.አ. እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ ዓላማውን ከግብ ማድረስ መቻላቸው ሲበዛ አጠያያቂ መሆኑ ነው። 189 የዓለም መንግሥታት መሪዎች በመስከረም ወር 2000 ዓ.ም. ድህነትና ረሃብን በግማሽ የመቀነሱን ሃሣብ የጠቀለለውን የሚሌሊየሙን ዕቅድ ገቢር ለማድረግ ቃል ከገቡ ወዲህ የጊዜውን ሂደት የተከተለ የኤኮኖሚና የልማት ዕርምጃ ሲደረግ የሚታየው በምሥራቅና በደቡብ እሢያ፤ በተወሰነ ደረጃም በላቲን አሜሪካ አካባቢ ብቻ ነው።

በአፍሪቃ፤ በተለይም ከሣሃራ በስተደቡብ ባለው የአሕጉሪቱ ክፍል በአንጻሩ ብዙዎች አገሮች የተጣለውን ተሥፋ እንደማያሟሉ ከአሁኑ መተንበይ ብቻ ሣይሆን እርግጠኛ ሆነው የሚናገሩት የምጣኔ-ሐብት ጠበብት ጥቂቶች አይደሉም። ለዚህም ነው በወቅቱ በርካታ ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶችና በልማት ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ጠበብት የመንግሥታቱ መሪዎች ጉባዔ የተሰናከለውን ሂደት መሥመር በማስያዝ ዕቅዱን ከመክሸፍ እንዲያድን መወትወት ይዘው የሚገኙት።

የሚሌኒየሙ ዕቅድ እንደታሰበውና እንደተወጠነው የተቀመጠለትን የ 15 ዓመት የጊዜ ገደብ ተከትሎ እንዳይራመድ ያሰሩትና የተበተቡት ምክንያቶች ብዙዎች ናቸው። ዋናው የበለጸጉ መንግሥታት አስፈላጊውን የልማት ዕርዳታ ለማቅረብ የገቡትን ቃል በሚገባ ገቢር አለማድረጋቸው፤ በተለይ ደግሞ ለጸረ-ሽብር ትግል ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የምትሰጠው አሜሪካ ጉዳዩን ክብደት የሚያሳጣ መሰናክል ፈጥራ መቆየቷ ነው።

ዋሺንግተን በፊታችን አርብ ለመንግሥታቱ መሪዎች ለፊርማ የሚቀርብ ሰነድ ለማጠናቀቅ ባለፉት ሶሥት ሣምንታት በዲፕሎማቶች ደረጃ ሲካሄድ በቆየው ድርድር የራሷን የለውጥ ሃሣቦች በገፍ በማቅረብ አስቸጋሪ ሁኔታን ስትፈጥር ነው የቆየችው። በአውሮፓ ሕብረት የሚደገፈው የበለጸጉ መንግሥታት በመጪዎቹ አሥር ዓመታት የልማት ዕርዳታቸውን ከአጠቃላይ ብሄራዊ ገቢያቸው አንጻር ወደ 0.7 በመቶ ከፍ እንዲያድጉ የቀረበው ሃሣብ አሣሪነት እንዳይኖረው አድርጋለች።

የአሜሪካ መንግሥት ለልማቱ አጀንዳ፣ ለግቡም ሆነ ለአፈጻጸሙ፤ እንዲሁም በተለይ በአፍሪቃ አስፈላጊ ለሆነው ብርቱ ተግባር መሰናክል ሲፈጥር ነው የቆየው። ሁኔታው የተባበሩት መንግሥታትን የሚሌኒየም ዕቅድ ክፍተኛው ክስረት አሰኝቶ ለታሪክ የሚያበቃ ውድቀት እንዳይሆን በጣሙን ያሰጋል። የዛሬ አምሥት ዓመት የዓለም መንግሥታት መሪዎች ረሃብን፣ ድህነትንና መሃይምነትን ለማሸነፍ ሲነሱ ዓላማው በተለይ ከአንዲት ዶላር ባነሰች የቀን ገቢ የዕለት ኑሮውን በመከራ ለሚገፋው ከሚሊያርድ የሚበልጥ ሕዝብ የብሩህ ጊዜ ተሥፋ ነበር የሆነው። የተከተለው ሃቁ ግን ሌላ ነው! ከዚያን ወዲህ ዓለም በሰፊው ያተኮረው በጸረ-ሽብር ተብዬው ትግል እንጂ በሚሌኒየሙ ግቦች ላይ አልነበረም።

በአጠቃላይ በዓለምአቀፍ ጸጥታና በድርጅቱ ጥገና እንዲሁም ሌሎች አርዕስት የተዋጠው ያለፉት ሣምንታት ድርድር በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠር ሕዝብ መቅሰፍት የሆነውን ድህነት የማለዘቡን ጉዳይ ተገቢውን ክብደት ነፍጎታል። ጉዳዩን በጥሞና የታዘቡት የዓለምአቀፉ ግብረ-ሰናይ ድርጅት የኦክስፋም ባልደረባ ኒኮላ ራይንድሮፕ የዓለም መንግሥታት የልማት ግቡን በተመለከተ፤ ይህም ድህነትና ረሃብን ይጠቀልላል፤ ጭብጥ ግዴታዎችን ካላስቀመጡ አዝጋሚ በሆነ ዕርምጃ ከሚሌኒየሙ ግብ በመቶ ዓመት እንኳ ሊደረስ አይቻልም ሲሉ ነው ያስጠነቀቁት።

“Action Aid International” የተሰኘው ድርጅትም በጉዳዩ ባወጣው ዘገባ ኒውዮርክ ላይ የተሰበሰቡት የመንግሥታት መሪዎች ድህነትን የማጥፋቱን ጉዳይ ዓበይት ክብደት በመስጠት ወደ አጀንዳቸው ካልመለሱና በተለይም የግቡን ፈር የለቀቁት ድሆቹ የአፍሪቃ አገሮች መልሰው መሥመር የሚይዙበትን ዕርምጃ ለይተው ካላስቀመጡ እስካሁን በጥቂቱ የተገኘው ዕድገት ሁሉ ከንቱ እንደሚሆን አስገንዝቧል።

በመሠረቱ ልማት፤ ጸጥታና ሰብዓዊ መብቶች እርስበርስ የተሳሰሩ፤ አንዱ ካለሌላው ተነጣጥለው ሊረጋገጡ የማይችሉ ነገሮች ናቸው። ሆኖም አሜሪካ የምታራምደው ጸረ-ሽብር ፖሊሲ በገቢር ይህን ሃቅ የሚያንጸባርቅ ሆኖ አይገኝም። የዋሺንግተን ዕርዳታ ተጠቃሚዎች የዚሁ ትግል አበር መሆን እንጂ የግድ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችን የሚያከብሩ መሆን የለባቸውም። ያለፉት ዓመታት ሃቅ በተለይ በአፍሪቃ ጉልህ አድርጎ ያሳየው ይህን ነው።

የሚሌኒየሙ ዕቅድ የዚህ መብት ከበሬታ ባዕድ በሆነባቸው አገሮች ፍትሃዊ አስተዳደር እንዲሰፍን የሚጠይቅ ነው። ከሆነ የዕርዳታው ገንዘብ ለሕዝብ በቀጥታ በመድረስ ፈንታ ለጥቂት ባለሥልጣናት የግል መካበቻ ሆኖ እንዳይባክን ለዴሞክራሲያዊ ተሃድሶ መስፈን ቁርጠኛ ግፊት ማድረጉ ግድ ይሆናል። አለበለዚያ የኤኮኖሚና የልማት ዕድገት ይገኛል ብሎ ማሰብ ከንቱ ነው።

እርግጥ ዛሬ በዓለም ላይ ለአያሌ ሕዝብ ስቃይ መንስዔ ሆኖ ከሚገኘው የረሃብና የድህነት አዙሪት ለመውጣት ገንዘብ የግድ ያስፈልጋል። ግን ይህ ብቻ አይደለም ወሣኙ ነገር። ወሣኙ ፍትሃዊ አስተዳደር በተጓደለባቸው ቦታዎች ሁሉ፤ ለምሳሌ በአፍሪቃ በየቦታው መስፈኑና ሰብዓዊ መብቶች መከበራቸው፤ ሙስና መወገዱና ለልማት አመቺ ሁኔታ መፈጥሩ ነው። ታዲያ የሚሌኒየሙ ዕቅድ ከወጣ ወዲህ እስካሁን ምናልባት በጉዳዩ ብዙ ተወርቶ እንደሆን እንጂ በተግባር የተደረገው ጥቂት ነው።

በአፍሪቃ ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከዚምባብዌ እስከ ግብጽ ምርጫዎች ተካሂደዋል። ግን አነሳስ፤ አካሄዳቸው፤ የአንዳቸውም ዴሞክራሲያዊ መስፈርቶችን ያሟላ አልነበረም። ምርጫው በየቦታው ለተሃድሶ፤ የሕዝብን ፍላጎት ለማክበርና ለዕድገት አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር ሣይሆን ሥልጣንን ሕጋዊ ልባስ ለመስጠት የተወጠነ ነው መስሎ ያለፈው። የሚሌኒየሙን የልማት ዕቅድ በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥ ከግቡ በማድረሱ በኩል ተጎታች ሆኖ በሚገኘው በዚህ ክፍለ-ዓለም ዕቅዱ ስኬት እንዲያገኝ ከተፈለገ ይህ የዴሞክራሲ ጥያቄ የዓለም ሕብረተሰብን አንድ ወጥ ምላሽ የሚሻ ነው።

ለመሆኑ የሚሌኒየሙ ዕቅድ በጊዜው ገቢር አለመሆን ምን ሁኔታን ነው ሊያስከትል የሚችለው? ጠበብት ጉዳዩን ከተለያየ አቅጣጫ በማጤን የሚሰጡት ማስገንዘቢያ ሲበዛ አስደንጋጭና አሳሳቢ ነው። በዛሬው ጊዜ ስድሥት ሚሊያርድ ከሚጠጋው የዓለም ሕዝብ ግማሹ የሚኖረው በከተሞች ነው። ከአሁኑ ከፍተኛ የቤት እጥረት አለ። በቅርብ ተካሂዶ የነበረ አንድ ጥናት እንዳመለከተው በታዳጊ አገሮች በሚቀጥሉት 25 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የከተማው ነዋሪ ቁጥር ከሁለት ሚሊያርድ ባላነሰ ሕዝብ እንደሚጨምር ይገመታል።
ይህን ሁኔታ ለመቋቋም ደግሞ በያመቱ 35 ሚሊዮን አዳዲስ የመኖሪያ ስፍራዎች መታነጻቸው ግድ ነው የሚሆነው። ለዚሁ ተግባር፤ የንጹሕ ውሃና የመጸዳጃውን ሁኔታ ጨምሮ፤ ጉዳዩን ለመቋቋም አስፈላጊው ገንዘብ በጊዜው በሥራ ላይ ካልዋለ ድህነትና በሽታ ይበልጥ መስፋፋቱ የማይቀር ይሆናል። ይህም አምራች የሥራ ሃይልን ማጣት፤ የልማትን ዕድል ይበልጥ መቅጨት ማለት ነው።

የሚሌኒየሙ ዕቅድ እንደታሰበው በ 2015 ዓ.ም. ከግቡ አለመድረስ ሌላ መዘዝም ይኖረዋል። ጉዳዩን የሚከታተሉ ጠበብት የሚናገሩት በዚሁ ሰበብ ሊተርፉ የሚችሉ ሰላሣ ሚሊዮን ሕጻናት ሊሞቱ እንደሚችሉ ነው። 230 ሚሊዮን ሕዝብ አስፈላጊውን የምግብ ዋስትና በማጣት ለረሃብ ይዳረጋል። ለመጪው ትውልድ የአካባቢን ተፈጥሮ ጠብቆ ማውረሱም ከንቱ ሊሆን ነው፤ ሌላም ብዙ ችግር ይከተላል።

ታዲያ የሚያሳዝነው ይህን መሰሉ ዓቢይ ችግር ተገቢውን ክብደትና ትኩረት አጥቶ መቀጠሉ ነው። በተባበሩት መንግሥታት መቀመጫ የተሰበሰቡት የመንግሥታት መሪዎች ባለፈው ምሽት ጸረ-ሽብር ትግላቸውን በጋራ ለማራመድ እንደገና ተስማምተዋል። የሚያስገርመው የሽብርም ሆነ የውዝግብ ዋነኛው መንስዔ አያሌ ሚሊዮን የዓለም ሕዝብ የወደቀበት የከፋ ረሃብ መሆኑ ተገቢውን ግንዛቤ አለማግኘቱ ነው። ዛሬ ታዳጊ አገሮች በልማት አቅጣጫ ለማምራትና ድህነትን ለማሸነፍ የበለጸገውን ዓለም ዕርዳታ የመፈለጋቸውን ያህል ምዕራባውያን መንግሥታትም ሽብርን ለማቆም ድህነትን ማስወገዱ አንድ ዓቢይ ቅድመ-ግዴታ መሆኑን ቢያምኑበት ምንኛ በበጀ ነበር።