1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባበሩት መንግሥታት የፀረ-ዘረኝነት ጉባኤና ዉዝግቡ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 19 2001

በጉባኤ ላይ ቢገኙ ኖሮ በመከራከር፥ እምነት አስተሳሰብን በመግለፅ ነፃነት፥ ለሚያምነዉ ለዲሞክራሲያዉ ሥርዓት ሥርፀት ልዩ ትኩረት መስጠታቸዉን ባስመሰከሩ ነበር

https://p.dw.com/p/HfIz
ጉባኤዉምስል AP

27 04 09


ሐምሌ-18 1950 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የተባበሩት መንግሥታት የትምሕርት የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (UNESCO) ያሳተመዉ ወፍራም ጥራዝ የዘረኝነትን አስተሳሰብን ለመዋጋት የመጀመሪያዉ አለም አቀፋዊ ሠነድ ነበር።የዚያ ዘመን በርካታ እዉቅ አጥኚዎች የምር ምር ዉጤት የሆነዉን ጥራዝ የአለም ዘዋሪዎች መቀበላቸዉ እስከ ሁለተኛዉ የአለም ጦርነት ፍፃሜ ድረስ አለም ሥለ-ዘር የነበረዉን የተሳሳተ አመለካከት ለመስተካከል የመፍቀዱ ምልክት፥ በጎ ተስፋም ነበር።ጥሩዉ-ምልክት በታየ፥ በጎዉ ተስፋ በፈነጠቀ በሐምሳ-ዘጠነኛ አመቱ ዘንድሮ-የአለም ሐያላን ሥለ ዘረኝነት የጋራ-አቋም መያዝ አይደለም በጋራ ለመምከር እንኳን መጠየፋቸዉ እንጂ ሰቀቀኑ።ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።ባለፈዉ አርብ የተጠናቀቀዉን የአለም የፀረ-ዘረኝነት ጉባኤ የሒደት ዉጤቱን አስታከን ጥቂት እንላለን ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

---------------------------------------------------------------------

እንደ አስተሳሰብ እምነታቸዉ፥ እንደ መርሕ-ቃላቸዉ በቆዳ-ቀለም የመታበይን-ሌሎችን የመናቅ፥ የማግለል፥ የመግዛት፤ የመርገጥ ምናልባትም የማጥፋትን እኩይነትን ለመዋጋት የዘመናችን አለም ከሳቸዉ የሚቀድም፥ የሳቸዉን ያክል አቅም፥ብልሐት ያለዉ ሰዉ በርግጥ የላትም።ፕሬዝዳት ባራክ ሁሴይን ኦባማ።አለም ኦባማን የሚደግፍ፥ የሚያደቅ፥ የሚወድበት ብዙ ምክንያት ሊኖረዉ ይችላል።የአብዛኛዉ ምክንያት ግን ከሳቸዉ በፊት የነበሩት መሪዎች ይከተሉት የነበሩትን መርሕ-አስተሳሰብ ለመቀየር ከመወሰን፥ ቃል-ከመግባት-መሞከራቸዉ ብዙ የራቀ አይሆንም።

የጄኔቩ አለም አቀፍ ጉባኤ ከመደረጉ በፊት ከለንደን-እስከ ኬል፥ ከሽትራስቡርግ-እስከ አንካራ፥ ከሜክሲኮ-እስከ ፖርቶ ኦ ፕሪንስ በተደጉት ስብሰባ-ጉባኤዎች ላይ አስተናጋጅ፤ አቻዎቻቸዉን የማረኩት ብዙ የፖለቲካ አዋቂዎች ከብዙ ጊዜ በላይ እንዳሉት ኦባማ ሁለት ነገሮችን ደጋግመዉ በማለታቸዉ ነበር።


የመጣሁት እንደ አቻ ልነጋገር-ነዉ ማለታቸዉ አንድ።«ገለፃ ለማድረግ ሳይሆን የናንተን ሐሳብም ለመስማት ዝግጁ ነኝ»-ማለታቸዉ-ሁለት።በርግጥም ኦባማ በየደረሱበት ያሉትን ማድረጋቸዉ ካንዴ በላይ ተመስክሮላቸዋል።ይሕ የኦባማ መርሕ-ቃል ድርጊት ቀዳሚያቸዉ-የተጠሉትን ያክል እንዲወደዱ፥ እንዲከበሩ ተባባሪ እንዲያገኙም ምክንያት ሆኗል።ከለንደን ተጀምሮ-ፖርቶ ኦ ፕሪስ ባሰረገ ጉብኝታቸዉ ላሉ ላደረጉት ድጋፍ አድናቆቱ ተዥጎድጉዶ ሳያበቃ የፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ መስተዳድር ከስምንት አመት በፊት ደርባን ላይ ያደረገዉን ዤኔቭ ላይ መድገማቸዉ ነዉ-ጉዱ።

«ችግሩ እዚሕጋ ነዉ-ያለዉ።ከዚሕ ቀደም ሌላ ጉባኤ ነበር።ጉባኤዉ ሰዎች በእስራል አንፃር ብዙ ጊዜ ጨራሽ ተመፃዳቂነት የታየበትና መጥፎ ዉጤት የሚያመጣ ተቃዉሞ ያሳዩበት ስብሰባ ነበር-የሆነዉ።»

ኦባማ «ከዚሕ በፊት» ያሉት በ2001 ደርባን-ደቡብ አፍሪቃ የተደረገዉን አለም አቀፍ የፀረ-ዘረኝነት ጉባኤን ነበር።በደርባኑ ጉባኤ ላይ ተካፍለዉ የነበሩት የአሜሪካና የእስራኤል መልዕክተኞች ጉባኤዉ እስራኤል ለማዉገዢያ ዉሏል፥ ፅዮናዊነት እንደ ዘረኝነት ተቆጥሯል በሚል ጉባኤዉን አቋርጠዉ ወጥተዉ ነበር።የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራትም የጉባኤዉን የአቋም መግለጫ ሰነድ አልተቀበሉትም ነበር።ጉባኤዉን ያስተናገዱት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣናት በተለይም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የበላይ የነበሩት ሜሪ ሮቢንሰን እንደገለጡት የደርባኑ ጉባኤ የመካከለኛዉ ምሥራቅ ተቀናቃኞች መፋለሚያ መድረክ አልነበረም።

Memoclick KW17 KW 17 Spanisch Anti-Rassismus-Konferenz 2009
አወዛጋቢዉ መሪ-ፕሬዝዳንት አሕመዲንጃድ


ጉባኤዉ ገና ሲጠነሰስ በጥቂት ነጮች-አገዛዝ ሚሊዮነ-ሚሊዮናት ጥቁሮች ለበርካታ አመታት ሲረገጡ፥ሲጋዙ፥ ሲገዙ በነበሩባት ሐገር-ደቡብ አፍሪቃ እንዲደረግ የተወሰነዉ የዘረኝነትን መጥፎነት ለማሳየት አብነታዊነቱም ታስቦበት ነበር።የደርባኑ ጉባኤ እንደ ለፀረ-ዘረኝነት እንደ ምሳሌ ከመታሰቡ ጋር በባርነት ለተገዙ፥ ለተሸጡ፥ ለተለወጡ፥ ወገኖች የሚቆረቆሩ፥ ጥቁር በመሆኑ ብቻ ለተረገጠዉ ሕዝብ እኩልነት የሚታገሉ ሐይላት ድምፅ የተሰማበትም ነበር።የዲሞክራሲ መሥራች፥ የሰብአዊ መብት ቀንዲል፥ የእኩልነት ሐገር የምትባለዉ ዩናይትድ ስቴትስና ተከታዮችዋ ያን ስብሰባ ረግጠዉ ሲወጡ በእስራኤል ላይ የተሰነዘረዉን ዉንጀላ መቃወም ብቻ ሳይሆን ለጥቁሮች እኩልነት የተነሳዉን ጥያቄ ተገቢነትም አለመቀባለቸዉን ነዉ ያሳዩት።

ከደርባኑ እስከ ዤኔቩ-ጉባኤ በነበረዉ የስምንት አመት ጊዜ የፕሬዝዳት ቡሽ መስተዳድር ያደረሰዉን ሥሕተት ለማረም ቃል-የገቡት አንዳድ ምልክቶችም ያሳዩት፥ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ለዤኔቩ ጉባኤ ሲሆን የሌሎችን ለመስማት ፍላጎቱ አልነበራቸዉም።ዩናይትድ ስቴትስ እስራኤል፥ አዉትራሊያና ሌሎች ምዕራባዉያን ሐገራት በጉባኤዉ አለመከፋለቸዉ የአለምን ችግር ለማስወገድ የሚደረገዉን ጥረት ሙሉ በሙሉ አያዉከዉ ይሆናል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን እንዳሉት የጥረቱን አድማስ ማጥበቡ፥ ዉጤቱን ማዘግየቱ ግን አያጠያይቅም።

«ለወደፊቱ አለም የተሻለ እድል ለመፍጠር መብት የነበራቸዉ አንዳድ ሐገራት አልተገኙም።ከነዚሕ አዳራሾች ዉጪ የየራሳቸዉ ጥቅም ያላቸዉ ቡድናት ወይም ደግሞ ፖለቲካዊ ርዮታቸዉን ለማንፀባርቅ የሚፈልጉ ብዙ ወገኖች አንዱ በሌላዉ ይጮሕ-ይሆናል።እነዚያም ቢሆኑ እዚሕ ተገኝተዉ ከኛ ጋር መነጋገር ነበረባቸዉ።»

ለሰብአዊ መብት፥ ለእኩለት የሚታገሉ ወገኖች እና አንዳድ ፖለቲከኞች እንዳሉት በጉባኤዉ ያልተገኙት ሐገራት በጉባኤ ላይ ቢገኙ ኖሮ በመከራከር፥ እምነት አስተሳሰብን በመግለፅ ነፃነት፥ ለሚያምነዉ ለዲሞክራሲያዉ ሥርዓት ሥርፀት ልዩ ትኩረት መስጠታቸዉን ባስመሰከሩ ነበር።ለመሰረቱት አለም አቀፍ ድርጅት ተልኦኮ ስኬት ከልብ መቆማቸዉን ባሳዩ ነበር።አላደረጉትም።ወይም አልፈለጉም።ዩናይትድ ስቴትስና ተከታዮችዋ ማድረግ የነበረባቸዉን ባለማድረግ ወይም ባለመፈለጋቸዉ የኢራኑን ፕሬዝዳት የማሕሙድ የአሕመዲኒጃዲን ስድብ ማስቆም አልቻሉም።

«ከ1945 በሕዋላ ከዩናይትድ ስቴትስ፥ ከአዉሮጳና ከሌላዉ የአለም ክፍል የተላኩት ስደተኞች በሐይል በተያዙት የፍልስጤም ግዛቶች የዘረኛ መንግሥት ለመመሥረት በቅተዋል።»

የፕሬዝዳት አሕመዲኒጃድን የዉንጀላ ንግግር በርካታ ሰዎች ተቃዉመዉታል።የራስዋ የኢራን ስደተኞች በሰልፍ-አዉግዘዉታል።በጉባኤዉ ላይ የተካፈሉ የምዕራብ ሐገራት ተወካዮች ሥብሰባዉን ረግጠዉ ወጥተዋል።


ዩኔስኮ በ1950 «የዘር ጥያቄ» በሚል ርዕሥ ያሳተመዉ ጥራዝ ለዘረኝነት የሚሰጠዉን ሳይንሳዊ ትንታኔ እና ምክንያት ከመሠረቱ በሳይንሳዊ ጥናት ያፈረሰ ነዉ።አለም ሥለ-ዘረኝነት የጋራ አቋም እንዲይዝ ለማድረግ ግን አለም አቀፉ ድርጅት አራት ጉባኤዎች አስተናግዷል።በ1978 የተደረገዉ የመጀመሪያዉ ጉባኤ የደቡብ አፍሪቃን የጥቂት ዘረኞች አገዛዝ በሚቃወሙት ባብዛኛዉ የአፍሪቃዉያን እና ያን ሥርዓት ይደግፉ የነበሩት የምዕራባዉያን መነታሪኪያ ነበር-የሆነዉ።

በ1983-ዤኔቭ የተደረገዉ ጉባኤም የፕሪቶሪያ ዘረኛ-መንግሥት አረመኔነት ነበር የደመቀበት።ሕዝቧ-በነጭ ዘረኞቹ አገዛዝ ለበርካታ አመታት የማቀቀባት ደቡብ አፍሪቃ ጉባኤዉ ስታስተናግድም አለም ከሚስማማበት ይልቅ-የሚለያይበት ርዕሥ አላጣም።

Antirassismus Konferenz in Genf
«--ጉባዉ የጥላቻ አልነበረም» ፒላይምስል AP

ባለፈዉ አርብ በተጠናቀቀዉ በአራተኛዉ ጉባኤ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሐገራት ከሰወስት አራተኛዉ የሚበልጡት ተወክለዋል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ምክር ቤት የበላይ ወይዘሮ ናቪ ፒላይ እንዳሉት ጉባኤተኞች ባለፈዉ ማክሰኞ ያፀደቁት ሰነድ-ጉባኤዉ የተሳካ መሆኑን መስካሪ ነዉ።ጉባኤዉ ፅዮናዊነት እንደ-ዘረኝነት የተቆጠረበት፥ በእስራኤል ላይ ጥላቻ የተነዘባት የሚለዉን ወቀሳና ትችም ወይዘሮ-ፒላይ «አለማወቅ» በማለት አጣጥለዉታል
ድምፅ

የደርባኑን መግለጫ እና መርሐ-ግብር አንብበዉ ቢሆን ኖሮ እንዲሕ የሚለዉ ምዕራፍ መካተቱን ይገነዘቡ ነበር።እጠቅሳለሁ፥-«ሆሎኮስት መዘንጋት የለበትም።»ሌሎች ሁለት ምዕራፎችም አሉ፥ እጠቅሳለሁ፣-ፀረ-ሴማዊነትና እስልምናን ጥላቻ። የፍልስጤሞችን ስቃይ በሚመለከተዉ ምዕራፍ ደግሞ ፍልስጤሞች የራሳቸዉን እድል በራሳቸዉ የመወሰን መብታቸዉ እንዲጠበቅና እስራኤልን ጨምሮ የሁሉም ሐገራት ደሕንነት መጠበቅ እንደሚገባዉ ተጠቅሷል።ሌሎች ሁለት ምዕራፎችም አሉ።እነዚሕ ሁሉ በመካከለኛዉ ምሥራቅን ላይ ያተኮሩ ናቸዉ።አንዳድ ትላልቅ ጋዜጦች በተለይ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ የሚታተሙት እነዚሕ ምዕራፎችን ሳያካትቱ «ጥላቻ» እያሉ የፃፉትን ከዚሕ በላይ ባልኩት መሠረት አስተካክለዉ እርማት ማተማቸዉን ማየት አልቻልኩም።
-----------------------------------------

ፒላይ ለጉባኤያቸዉ ድል ዋቢ ያደረጉት ሰነድ ገቢራዊነት ሌላ ሐምሳ-ዘጠኝ አመት ላለመጠየቁም ምንም ዋስትና የለም።

Dw,dpa,Afp,wikipedia

ነጋሽ መሐመድ