1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባበሩት መንግሥታት የፊናንስ ጉባዔ

ረቡዕ፣ ሰኔ 24 2001

ዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ከሃብታም ይልቅ ታዳጊ አገሮችን ይበልጥ እንደጎዳና እየጎዳ እንዳለም በተደጋጋሚ ሲነገር የቆየ ጉዳይ ነው።

https://p.dw.com/p/If22
ምስል AP

ቀውሱ እ.ጎ.አ. እስከ 2015 ዓ.ም. ድህነትን በግማሽ ለመቀነስና ረሃብን ለመታገል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የወጣውን የሚሌኒየም ዕቅድ ገቢርነት፤ ከግቡ መድረሱንም እንዲሁ አጠያያቂ አድርጎታል። ችግሩን ለመወጣት ዓለምአቀፉ ሕብረተሰብ ምን መንገድ ሊኖረው ይችላል? በዚህ ከባድ ወቅት መፍትሄው በተናጠል የራስን መውጫ ቀዳዳ መፈለግ ነው ወይስ በጋራ መታገል? ለነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ባለፈው ሣምንት ማብቂያ ላይ ኒውዮርክ ውስጥ የተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የፊናንስ ጉባዔ ታሪካዊ ግምት በተሰጣቸው በጋራ በሚወሰዱ ዕርምጃዎች ላይ ተስማምቶ ነበር። እርግጥ ስምምነቱ እንደታሰበው ገቢር መሆኑን አጠያያቂ የሚያደርጉ ወገኖችም አልታጡም።

ዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ያስከተለውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል የጋራ መፍትሄ ለማፈላለግ የተካሄደውን የተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ሃሣብ ያንቀሳቀሱት የጠቅላይ ጉባዔው ፕሬዚደንት ሚጉዌል-ዲ.ኤስኮቶ-ብሮክማን ነበሩ። በሌላ በኩል ሃሣቡን አጠያያቂ ያደረጉ ተጠራጣሪ ወገኖችና የአንዳንድ መንግሥታት ዲፕሎማቶች ጉባዔው መካሄዱን ከንቱ ጊዜ ማባከን ሲሉ ገና ከዋዜማው መተቸታቸው አልቀረም። የሆነው ሆኖ በቀውሱ በጣሙን የተጎዱትን ድሆች አገሮች ጨምሮ ሁሉም መንግሥታት ለጋራ መፍትሄ እንዲጥሩ የተወጠነው ጉባዔ ዲ.ኤስኮቶ እንዳለሙት ግቡን መትቷል።

በጉባዔው ላይ የተሳተፉት የ 140 መንግሥታት ተጠሪዎች ችግሩን ለመወጣት የሚያስችሉ ዕርምጃዎችን በጠቀለለ ሰነድ ሲስማሙ ውሣኔው የተላለፈውም አንዳች የተቃውሞ ድምጽ ሳይገጥመው ነው። ከአዘጋጆቹ አንዱ ጉባዔው እንዳበቃ በተካሄደ ጋዜጣዊ ጉባዔ ላይ እንዳሉት ስምምነቱ ታሪካዊ ክብደት የሚሰጠው ነው።

“በተባበሩት መንግሥታት ታሪክ ውስጥ በኤኮኖሚና በፊናንስ ዓለማችን ተሃንጾ ላይ ይህን መሰል ክብደት ያለው ሰነድ በአንድ ድምጽ ተቀባይነት ማግኘቱ ታላቅ ዕርምጃ ነው”

የጠቅላይ ጉባዔው ፕሬዚደንት ዲ-ኤስኮቶ በበኩላቸው ስምምነቱን በስብዕና አቅጣጫ የተደረገ ዕርምጃ ብለውታል። በጉባዔው ላይ ጀርመንን ወክለው የተሳተፉት የአገሪቱ የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ሃይደማሪ-ቪቾሬክ-ሶይል እንዳሉት ደግሞ በምዕራቡ ዓለምና በታዳጊ አገሮች መካከል ሲካሄድ ከቆየው ክርክር አንጻር የዓለምአቀፉ ድርጅት የፊናንስ ጉባዔ ሊካሄድ መቻሉ በጣም ጠቃሚ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ሚኒስስሯ በጉባዔው ላይ ባሰሙት ንግግር እንዳስረዱት በደህና የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ እያሉ ራሳቸው ባልፈጠሩት መዘዝ የቀውሱ ሰለቦች የሆኑት ታዳጊዎቹ አገሮች ናቸው። እና ተገቢው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።

“ይህም በመሆኑ በጋራ ከዚህ ቀውስ መላቀቅ እንዳለብን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኤኮኖሚ መጠናከር እንደሚኖርበትና ድምጻቸውም እንደሚሰማ በግልጽ እንዲያውቁት መደረጉ ጠቃሚ ነው”

ሃይደማሪ-ቪቾሬክ-ሶይል በዚሁ ንግግራቸው ድርጅቱ ሳይውል-ሳያድር አቅጣጫ መጠቆሙ አስፈላጊ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

“አሁን የሚፈለገውን ዕርምጃ ካልወሰድን በያመቱ ከ 200 እስከ 400 ሺህ ሕጻናት ይሞታሉ። በመሆኑም ዓለምአቀፉ ትብብር ብቸኛው አማራጭ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም አቅጣጫ ማሣየት መቻል አለበት”

እንደ ጀርመኗ ባለሥልጣን ዘግይቶ ስብርባሪን ከመልቀም ቀድሞ መከላከሉ የሚመረጠው መንገድ ነው።

“ሁላችንም የምንለው በመጨረሻ ጉዳቱን ለማረቅ ከመነሣት ይልቅ ቀድሞ መከላከል ይጠቅማል ነው። እነዚህ ሃገራት በችግሩ አዙሪት ከመጠመዳቸው በፊት ተገቢውን ዕርምጃ መውሰድ እንዲችሉ፣ አዲስ የዕዳ ወጥመድ ውስጥ እንዳይገቡና እንደገና በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እንዳይሞቱ አሁን አስተዋጽኦ መደረግ ይኖርበታል። ይህ ነው ትልቁ ተግባር!”

ሃይደማሪ-ቪቾሬክ-ሶይል ለታዳጊዎቹ አገሮች ልማት ይበልጥ ገንዘብ መቅረብ እንዳለበትም አስገንዝበዋል። ባንኮችም ራሳቸው ለቀሰቀሱት ቀውስ የተወሰነውን የፊናንስ ሃላፊነት እንዲወስዱ ጠይቀዋል። እንደርሳቸው አባባል የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከአካባቢ አየር ጥበቃና ከአክሢዮኖች ንግድ ገቢ ለማግኘትም ይቻላል። በአጠቃላይ አንድ ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ማገገሚያ ዕቅድ መኖሩ አስፈላጊ ነው ባይ ናቸው።

“የድሃ ድሃ የሆኑት ወገኖችም ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዓለምአቀፍ ማገገሚያ ፓኬት ያስፈልገናል። እዚህ ላይ ታዲያ ስለ አካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃም ማሰባችን ግድ ነው። በሌላ አነጋገር አንድ አዲስ አረንጓዴ ውል ያስፈልገናል”

ይሄው “Green New Deal” ወይም አዲስ አረንጓዴ ውል የሚል ለአረንጓዴ ልማትና ተፈጥሮን ለጠበቀ የቴክኖሎጂ ዕርምጃ የተነሣ መፈክር በመንግሥታቱ ተጠሪዎች ዘንድ ሰፊ ድጋፍን ነው ያገኘው። ቀጣይነት ያለው የኤኮኖሚ ዕርምጃና ተፈጥሮን ያከበረ ቴክኖሎጂ መስፋፋት በብዙዎች፤ በተለይም በታዳጊው ዓለም ተጠሪዎች ዘንድ ከቀውሱ ለመውጣት መልካም ዕድል ሆኖ መታየቱ አልቀረም።

የጋራ መፍትሄ ለመሻት በተካሄደው የሶሥት ቀናት ጉባዔ ሌላው ዓቢይ ጉዳይ ድርጅቱ በኤኮኖሚ-ነክ ውሣኔዎች ላይ ሊኖረው የሚገባው ቁልፍ ሚናና በሚሌኒየም ግቦቹ ላይ መጽናቱም ነበር። ከሚሌኒየሙ ግቦች አንደኛውና ዋናውም ረሃብን በዓለምአቀፍ ደረጃ በግማሽ መቀነስ መሆኑ ይታወቃል። ዋና ጸሐፊ ባን-ኪ-ሙን እንዳሉት ድሕነትን መታገልና ትምሕርትን ማዳረስ ቅንጦት ሣይሆን ለዓለም በጎነት አስፈላጊ ጉዳይ ነው።

ከዚሁ በተጨማሪ የዓለም የፊናንስ ድርጅቶች የጥገና ለውጥም በስምምነቱ ሰነድ ላይ ከሰፈሩት ዓበይት ጉዳዮች አንዱ ነው። የፊናንሱ ቀውስ በታዳጊ አገሮች ላይ ያስከተለውን ተጽዕኖ የሚመረምረውን ኮሚሢዮን የሚመሩት የምጣኔ-ሐብት የኖቤል ተሽላሚ ጆዜፍ ስቲግሊትስ መለስ ብለው የችግሩን መነሻ ምክንያቶች ዘርዝረዋል። ከአንግዲህ አንድ ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚና የፊናንስ አዋቂዎች ሸንጎ ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ቀውሶችን ቀድሞ በመጠቆም አደጋን ለመከላከል ነው የሚታሰበው። እርግጥ ስቲግሊትስ እንዳስረዱት በሶሥት ቀናት ስብሰባ ከፊናንሱ ቀውስ ጋር ለተያያዙት መላ ችግሮች መፍትሄ ማግኘት የሚቻል ነገር አልነበረም።

“በዚህ መሰሉ ስብሰባ አንዳንድ የቀውሱን መንስዔዎች በተሻለ ሁኔታ በጋራ ለመረዳት እንደተቻለና ለስኬት ተሥፋ የሚሰጥ ምን ነገር መደረግ እንዳለበት የተሻለ ግንዛቤ እንደተገኘ ተሥፋ ይደረጋል። እናም ወቅቱ ምናልባት የተሥፋ ነው”

በአጠቃላይ የጉባዔው ውጤት ተሥፋ ሰጭ፤ ከዚያም አልፎ ታሪካዊ ሲባል በሌላ በኩል ተቺዎቹና ተጠራጣሪዎቹ እንደ ዋዜማው ሁሉ አሁንም ዕርምጃ መደረጉ አይታያቸውም። ስምምነቱ አንዳች የሚያስከትለው ውጤት አይኖርም ማለት ይዘው ነው የሚገኙት። በተለይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተግባሩን ለማራመድ ትክክለኛው ወይም ተስማሚው አይደለም ከሚሉት መካከል አሜሪካም ትገኝበታለች። ሆኖም የጠቅላይ ጉባዔው ፕሬዚደንት ሚጉዌል-ዲ-ኤስኮቶ ግን ይህን መሰሉን አባባል ጨርሶ አልተቀበሉትም።

“ምንድነው የሚያስቡት? እኛ እኮ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላይ ጉባዔ ነን። እኔ የምመራው ቡድን ከማንኛውም በዓለም ላይ ከሚገኝ መንግሥት የተሻለ ነው። ይህን ደግሞ ያውቁታል”

ለማንኛውም ጉባዔው በአንድ ድምጽ የስምምነት ሰነድ ማስፈኑ ተሳክቶለታል። በተግባር ምን ይከተል ግን ለጊዜው የሚቀረው ምርጫ ጠብቆ መታዘብ ብቻ ነው የሚሆነው።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ