1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባባሰዉ የምሥራቅ ዩክሬን ዉጊያ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 14 2006

ምሥራቅ ዩክሬን ዉስጥ ዉጊያዉ መባባሱ እየተነገረ ነዉ። በሩሲያ ይደገፋሉ የሚባሉት አማፅያን ከሚንቀሳቀሱባቸዉ ከተሞች አንዷ በሆነችዉ ዶኔስክ 34 ሰዎች ሲገደሉ 29 ሰዎች ባለፉት 24 ሰዓታት መቁሰላቸዉ ተገልጿል። ዘጠኝ የዩክሬን መንግሥት ወታደሮችም መሞታቸዉን ባለስልጣናት አመልክተዋል።

https://p.dw.com/p/1CyLd
Ostukraine Krise Donezk 18.08.2014
ምስል D.Dilkoff/AFP/Getty Images

የመንግሥት ወታደሮች በአካባቢዉ የሚካሄደዉን የአማፅያን እንቅስቃሴ ለመግታት እየታገሉ መሆኑ ቢነገርም አሁንም ዶኔስክ በሩሲያ አፍቃሪ ታጣቂዎቹ ቁጥጥር ሥር ናት። ፓቬል፤ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ እንዴት ተፈታቶ እንደሚጠራረግ የሚያውቀዉ ነገር አልነበረም። ወታደር መሆንንም በፍፁም አስቦት አያዉቅም፤ ከምሥራቅ ዩክሬን አካባቢ የተገንጣዮቹን እንቅስቃሴ ለማክተም የኪየቭ መንግስት ወዶ ዘማቾችን ሲያስተባብር ተመዝግቦ አሁን በጦርነት መሀል ይገኛል። ላለፉት 45 ቀናት ከዶንባስ ወዶ ዘማቾች ግብረ ኃይል ጋ በመሆን ምሥራቅ ዩክሬን በጦር ግንባር ተሰልፏል፤

Ostukraine Krise Gelübde der Freiwilligen der Donbass Selbstverteidigung
ምስል Reuters

«የምታገለዉ ዩክሬን መልሳ ነፃ እንድትሆን ነዉ። ከሉንስክ እና ዶኔስክ ተገንጣዮች፤ እንዲሁም ከሩሲያና ከቼኮች ነፃ መሆን አለባት። እንደዚያ ያለ ነገር እኛ እዚህ አንፈልግም።»

የዩክሬን መንግሥት ወታደሮች ሰሞኑን በሚያካሂዱት የጥቃት ርምጃ ለመገንጠል የሚታገሉ ታጣቂዎ ከያዟቸዉ ስልታዊ ከሚባሉ አካባቢዎች አንዱን መቆጣጠራቸዉ እየተነገረ ነዉ። የኪየቭ መንግሥት ባለስጣናት እንደሚሉት ወታደሮቹ በዶኔስክ ከተማ አቅራቢያ የምትገኘዉን ሎቫይስክ የተሰኘችን ከተማ አብዛኛ ክፍል አሁን ይዘዋል። መንግስት የአማፅያኑ ኃይሎች ጠንካራ ይዞታና ዋና ጽሕፈት ቤታቸዉ የሚገኝባትን ዶኒየስክ ከተማ ቀለበት ዉስጥ ለመክተት የተካሄደዉ ዘመቻም ክሬሚያ ግዛት ወደሩሲያ ከተገነጠለች አንስቶ በታጣቂዎቹ እጅ የነበሩ ወሳኝ ከሚባሉት ግዛቶች አብዛኞቹን መልሰዉ በመንግሥት ኃይሎች ሥር ማስገባት እንዳስቻላቸዉም ተገልጿል። ሁኔታዉም አማፅያኑ በያዟቸዉ አካባቢዎች የኑሮዉ ሁኔታ እየከፋ ከመምጣቱ የተነሳም አንዳንድ ቤቶች ላለፉት ሳምንታት ለኤሌክትሪክና ዉኃ እጦት ተጋልጠዋል። እስካሁንም በመንግሥት ኃይሎችና በታጣቂዎቹ መካከል የሚካሄደዉ ዉጊያ ከሁለት ሺ በላይ ሕይወት አጥፍቷል፤ 344 ሺዎችን ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸዉ አፈናቅሏል። የተቃጠሉ ቤቶች፤ እንዳልነበሩ የተፈነቃቀሉ ጎዳናዎች ናቸዉ የሚታዩት፤ የአካባቢዉ ኗሪም እንዴትና ወዴት መሄድ እንደሚኖርበት አላወቀም። አማፅያኑ በቴሌቪዥን የሚያሳዩት ይህን በመሆኑም የዩክሬን ኃይሎች ወዳሉበት ከመጡ ሊከተል የሚችለዉን የሚገምት የለም። የዩክሬን መንግሥት በበኩሉ ለመገንጠል የሚንቀሳቀሱትን በዚሁ ድርጊት ይከሳል። ችግሩ ግን እነዚያን የፈጸማቸዉ ማንነቱ በግልፅ አለመታወቁ ነዉ። ትናንት ሰላማዊ ሰዎች እንደጫነ ጥቃት የደረሰበት ተሽከርካሪ መንግሥት በአማፅያኑ እንደተመታ ይናገራል፤ አማፅያኑም እንዲሁ ክሱን ወደጎን በማድረግ መንግሥት ላይ ጣታቸዉን ጠቁመዋል። እነሱ ይካሰሱ እንጂ እስካሁንም ሉሃንስክ ላይ ለተፈፀመዉ ድርጊት ተጠያቂዉ ማን እንደሆነ ግልፅ አልሆነም። የኪየቭ መንግሥት ግን ጥቃቱን እንደዋና መረጃ በማሳየት የምዕራባዉያንን ወታደራዊ ድጋፍ ጠይቆበታል። ፕሬዝደንት ፔትሮ ፕሮሼንኮ የአማፅያኑን ተግባር እንዲህ ይዘረዝራሉ፤

Ostukraine Krise Donezk 18.08.2014
ምስል D.Dilkoff/AFP/Getty Images

«መሠረት ልማቶችን እያወደሙ ነው ። የኅይል ማመንጫ ጣቢያዎችን እያፈነዱ ነው ። ድልድዮችን ያወድማሉ። ድርጅቶችን እንዳልነበሩ ያደርጋሉ ። ይህ ጥፋት የተፈጸመው በአማፅያኑና በውጭ ረዳቶቻቸው ብቻ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ ።»

Merkel und Poroschenko 06.06.2014 Normandie
ምስል Damien MeyerAFP/Getty Images

ይህ በእንዲህ እንዳለም በምሥራቅ ዩክሬን ችግር ላይ ለሚገኙት ወገኖች ሩሲያ ወደ300 የሚገመቱ ትላልቅ ተሽከርካሪዎችን የሞላ እርዳታ ልኬያለሁ ብትልም ተሽከርካሪዎቹ እስካሁን በድንበር አካባቢ እንደቆሙ ነዉ። የዩክሬን ፕሬዝደንት ፔትሮ ፕሮሼንኮና የሩሲያ አቻቸዉ ቪላድሚር ፑቲን ቤላሩስ ዉስጥ እንደሚገናኙ እቅድ ተይዟል። ፕሮሼንኮ ከፑቲን ጋ ከመነጋገራቸዉ አስቀድሞም በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ ከጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጋ ኪየቭ ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል። የዩክሬንና ሩሲያ መሪዎች በቀጠሯቸዉ የሚነጋገሩ ከሆነም ከሰኔ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ