1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባ መ የአሠርቱ-ምእት ግቦች ክትትል

ሐሙስ፣ መስከረም 13 1997

የተባ መ ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን ያው የዓለሙ ድርጅት ከአራት ዓመታት በፊት ስለተለማቸው የአሠርቱ ምእት ግቦች ሂደት ከቅርብ ጊዜ በፊት የሰጡት ዓመታዊ መግለጫ፥ አንዳንድ የሚደረጁ ሀገሮች ፍፁሙን ድህነት በማሳነስና ረሃብን በማስወገድ፣ በሽታንም በመታገል ረገድ ጉልህ እመርታ ማሳየታቸውን አረጋግጧል። ግን ይኸው የኮፊ አናን ዘገባ እንደሚያስገነዝበው፣ እጅግ ኋላቀር በሆኑት በ፶ው ድሆች ሀገራት ውስጥ የግቦቹ እመርታ እጅግ አስቸጋሪ እየሆነ ነው የተገኘው። ከ

https://p.dw.com/p/E0fM

ነዚሁ ከ፶ው መካከል የድሆቹ ድሆች የሚሰኙት ፴፬ቱ የሚገኙት በሰሐራ ደቡቡ የአፍሪቃ ከፊል ነው። እጅግ ኋላቀሮቹ ሀገሮች በእስያ ከአፍጋኒስታንና ከባንግላዴሽ አንስቶ በአፍሪቃ እስከ ሴራሊዎንና እስከ ዛምቢያ የሚደርሱ ናቸው።

ዋና-ፀሐፊው አናን መንግሥታዊ ያልሆኑ ግብረሠናይ ድርጅቶች ከቅርብ ጊዜ በፊት በተባ መ ዘንድ ላካሄዱት የሦሥት ቀናት ዓመታዊ ጉባኤ ባሰሙት ንግግር እንዳስረዱት፣ ብዙዎቹ የአፍሪቃ ሀገሮች ወደ አሠርቱ ምእት የልማት ግቦች በሚደረገው ጉዞ ረገድ በቀጣዮቹም ዓመታት ውስጥ ገስጋሾቹን መለጠቅ የሚሳናቸው መስለው ነው የሚታዩት።

የዓለም መንግሥታት መሪዎች እ.ጎ.አ. በመስከረም ፪ሺ ኒው ዮርክ ውስጥ በተባ መ ዘንድ በተሰባሰቡበት ወቅት የተስማሙባቸው ስምንቱ የልማት ግቦች ረሃብ የሚወገድበትንና ድህነት የሚቀነስበትን፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ለሁሉ የሚዳረስበትን፣ የጾታዎች እኩልነት የሚተገበርበርበትን፣ የሕፃናት ሞት የሚገታበትን፣ የእናቶች ጤንነት የሚጠበቅበትን፣ በበሽታዎች አንፃር ትግሉ የሚጠናከርበትን፣ ለተፈጥሮ ጓዳ እንክብካቤ የሚሰጥበትን እና ዓለምአቀፍ የልማት ትብብር የሚነቃቃበትን ሁኔታ የሚመለከቱ ናቸው። ድህነት በግማሽ የሚቀነስበትን ሁኔታ ጨምሮ ለእነዚሁ ግቦች ክንውን የተገደበው የ፲፭ ዓመታት ጊዜ እ.ጎ.አ. በ፪ሺ፲፭ ነው የሚያበቃው--ከእንግዲህ ወዲያ የአሥር ዓመታት ጊዜ የቀረው መሆኑ ነው።

ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን መልካም ዜና ብለው በዓመታዊ መግለጫቸው ያቀረቡት፥ ዛሬ በምሥራቅ፣ በደቡብ እና በደቡብ-ምሥራቅ እስያ በፍፁሙ ድህነት ላይ የሚገኙት ሰዎች አሃዝ ከ፪-መቶ ሚሊዮን በሚበልጥ ደረጃ የተቀነሰበትን ሁኔታ ነው። ሌላው ቀርቶ፣ አናን እንደሚሉት ከሆነ፣ በሰሜን አፍሪቃ ያሉትም ሀገሮች በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ ፍፁሙን ድህነት በግማሽ ለመቅረፍ በሚችሉበት የእመርታ መንገድ ላይ የሚገኙ ሆነው ነው የሚታዩት።

በመግለጫው መሠረት፥ እመርታ የሚታየው በአንደኛ ደረጃ ትምህርትም ስርጭት ነው። በላቲን-አሜሪካና በከራይብ፣ በብዙዎቹ የእስያ አካባቢዎች፣ በሰሜን አፍሪቃና በቀድሞዎቹ ሶቭየት-ሬፑብሊኮች የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ምዝገባ ይዘት አሁን ፺ በመቶ የደረሰ ሆኗል--በዚህ አኳኋን በእነዚያው ሀገሮች ውስጥ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ምዝጉብነት ይዘት እ.ጎ.አ. በ፪ሺ፲፭ መቶ በመቶ ሊደርስ እንደሚበቃ ነው የሚገመተው--የዓለሙ ድርጅት መግለጫ እንደሚለው።

በዚህ አንፃር ግን፣ ዋና-ፀሐፊ ኮፊ አናን እንደሚያስገነዝቡት፣ መጥፎ ዜና ሆኖ የሚታየው፣ እጅግ ኋላቀር በሆኑት ሀገሮች ውስጥ በዚሁ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ስርጭት ረገድ አንዳች እመርታ አለመኖሩ ወይም ደግሞ በትምህርቱ ገበታ ላይ የሚሳተፉት ተማሪዎች አሃዝ ጭራሹን የተቀነሰ መሆኑ ነው። ባለፉት ፲፪ ወራት ውስጥ የእጅግ ኋላቀሮቹ ሀገሮች የልማት ግብ ክትትል ጨርሶ ያልተነቃቃ ሆኖ ነው ዋና ፀሐፊው የሚያዩት። በዚህ ረገድ በቀሳፊው በሽታ ኤድስ አንፃር የሚደረገው ትግል አለመጠናከሩም ነው የሚጠቀሰው። ባለፈው ዓመት በድሆቹ ሀገሮች ውስጥ የታየው ፈጣኑ የኤድስና የኤድስ ተሃዋሲ መስፋፋት ከምንጊዜውም የባሰ ሆኖ ነው የተገኘው። ይህም ብዙ ሚሊዮን ሕዝብ ለሠፈረባቸው አካባቢዎች የልማት ዕድል ከባድ እንቅፋት ሆኖ ነው የሚታየው።

ማዕከላዊ መሥሪያቤቱን በብሩክሴል ያደረገ እና እጅግ ኋላቀር በሆኑት ሀገሮች ውስጥ የሚንቀሳቀስ አንድ የግብረሠናይ ድርጅቶች አስተባባሪ ቡድን አሁን እንደሚያስገነዝበው፥ እጅግ ኋላቀሮቹ ሀገሮች ላለባቸው ከባድ የውጭ እዳ ጠንካራው ማቃለያ ርምጃ ሳይወሰድ የአሠርቱ ምእት ግቦችን እንዲፈጽሙ መጠየቅ ፋይዳ አይኖረውም። እንዲያውም፣ የተባ መ የልማት መርሐግብር ባለፈው ሐምሌ ስለ ሰብዓዊው ዕድገት ባቀረበው ዓመታዊ ዘገባ እንደሚያስረዳው፥ አፍሪቃ ውስጥ በሰሐራው ደቡብ የሚገኙት፣ ቡርኪና ፋሶን እና ሴራሊዎንን የመሳሰሉት ሀገሮች ከአራት ዓመታት በፊት የተባ መ የአሠርቱ ምእት ግቦች በተተለሙበት ወቅት ከነበራቸው ሁኔታ ይልቅ አሁን የሚገኙበት ሁኔታ በይበልጥ የተጎሳቆለ ሆኖ ነው የሚታየው። እጅግ ኋላቀሮቹ ሀገሮች የዓለሙ ድርጅት ስለ ሰብዓዊው ዕድገት ሀገባ ባቀረበ ቁጥር ሁልጊዜ በዝርዝሩ ዘብጥ ላይ ነው የሚመዘገቡት። በሰሐራው ደቡብ የሚገኙት ብዙዎቹ ሀገሮች--ለምሳሌ ሱዳን፣ ሴራሊዎን፣ ጊኔቢሳውና ሞዛምቢክ--የተሸከሙት የውጭው ዕዳ ከወ’ጭው ንግድ ገቢያቸው ከ፭፻ በመቶ የሚበልጥ ሆኖ ነው የሚታየው። በዚህ አኳኋን፣ ግብረሠናይ ድርጅቶች እንደሚያስገነዝቡት፣ ድሆቹ ሀገሮች የወ’ጭ ንግድ ገቢያቸውን ለውጭው ዕዳ ግፍገፋ እንዲያውሉት በሚገደዱበት ጊዜ፣ የአሠርቱ ምእቱን ግቦች ለመፈፀም ጨርሶ ተሥፋ ሊኖራቸው አይችልም። ስለዚህ ለእጅግ ድሆቹ ሀገሮች እዳ ቅነሳ ሳይሆን፣ መቶ በመቶ የእዳ ምኅረት መደረግ እንዳለበት ነው ግብረሠናይ ድርጅቶች የሚያስገነዝቡት። በጦርነት የተመሰቃቀለችውን ሀገር ኢራቅ መልሶ ለመገንባት ይቻል ዘንድ፣ ከ፹ እስከ ፺ ሚሊያርድ ዶላር የሚደርሰውን እዳ የሠረዙላት ለጋሾቹ መንግሥታት የብዙ ዓመታት ውዝግብ ላለባቸውም እጅግ ድሆቹ ሀገሮች ተመሳሳይ ርምጃ እንዲወስዱ በጥብቅ ነው የሚጠየቁት።

ዋና-ፀሐፊ ኮፊ አናን በዓመታዊ የግምገማ ዘገባቸው ውስጥ በሚያቀርቡት አስተያየት መሠረት፣ የአሠርቱ ምእት ስምንት የልማት ግቦች በድሆቹም ሀገሮች ውስጥ ሊፈፀሙ የሚችሉ በሆኑም ነበር፣ ግን የዕድሉ በሮች እየተፋጠኑ መጥበባቸውና የፖለቲካውም በጎፈቃድ በብዛት መጓደሉ ነው ችግሩ። አፍሪቃም ውስጥ ቢሆን፣ የፖለቲካው በጎፈቃድ ምኑን ያህል ግቦቹን ሊያፋጥን እንደሚችል ለማስረዳት የተባ መ ወኪሎች በትምህርት ስርጭት ረገድ ማላዊንና ሩዋንዳን ምሳሌ አድርገው ያቀርባሉ። በዚህም መሠረት፣ እነዚሁ ሀገሮች ለትምህርት የደረሱትን መላውን ሕፃናት ወደ ትምህርትቤት ለመላክ በቅተዋል ነው የሚባለው። ቀጥሎም፣ ሌላይቱ አፍሪቃዊት ሀገር ታንዛኒያ ወደ ንፁሕ ውሃ አቅርቦት ግቧ መቃረቧ፣ ኡጋንዳና ሴኔጋል የኤድስ ወረርሽኝን መስፋፋት ለማገድ መቻላቸው፣ ሞዛምቢክ ደግሞ በሕፃናት ላይ የሚደርሰውን የሞት አደጋ ለመግታት በምታደርገው ትግል ረገድ እመርታን ማሳየቷ በዓለሙ ድርጅት ዘገባ ውስጥ ተጠቅሷል። በዚህ አኳኋን፣ የፖለቲካው በጎፈቃድ ካለ፣ በሰሐራራ ደቡቡ አፍሪቃም ቢሆን የአሠርቱ ምእት ግቦች ክትትል ተሥፋ ሊታይበት ይችላል ማለት ነው።

ግን እውነተኛው ችግር ከራሳቸው ከመንግሥታቱ ነው የሚመነጨው። የዓለም መሪዎች በተባ መ መድረክ ላይ በጥኡመ ልሳን ተሥፋ የሚሰጡ ቃላትን ይለፍፋሉ፣ ሙሉ ቃል ይሰጣሉ፣ ይሁንና ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ቃላቱን በተግባር ለመተርጎም መነሳሳት ይሳናቸዋል። በዚህ ረገድ አንድ ምሳሌ የሚሆነው፥ የዓለም መሪዎች ከየሀገራቸው ጠቅላላ ብሔራዊ ገቢ ነጥብ-ሰባት በመቶውን ለድሆቹ ሀገሮች ልማት-ርዳታ እንዲያውሉት ከዓመታት በፊት የተስማሙበት ሁኔታ ነው የዓለሙ ድርጅት እንደሚለው። እስካሁን ታዲያ፣ ከለጋሾቹ መንግሥታት መካከል ስዊድን፣ ዴንማርክ፣ ኖርዌ፣ ኔደርላንድ እና ሉክሰምቡርክ ብቻ ናቸው ይህንኑ የነጥብ-ሰባት በመቶ ግብ ሊደርሱበት ወይም ሊያልፉት የበቁት። ከአራት ዓመታት በፊት በዓለሙ ድርጅት ዘንድ በተተለሙት የአሠርቱ ምእት ግቦችም ረገድ ተመሳሳይ ሁኔታ ነው የሚታየው። ቃላትን በተጨባጭ ተግባር መተርጎም የሁልጊዜ ችግር ሆኖ መገኘቱ ነው።