1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተከሰከሰው አውሮፕላን የበረራ መረጃ ሳጥን መገኘት ምን ይፈይዳል?

ሰኞ፣ መጋቢት 2 2011

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ቦይንግ 737 -800 ማክስ አውሮፕላን ለመከስከስ ያበቃውን ምክንያት ለማወቅ የሚደረገው ምርመራ ውስብስብ አስቸጋሪ እንደሚሆን ባለሙያዎች ይናገራሉ። ምርመራው ከኢትዮጵያ ባሻገር የቦይንግ ኩባንያ፤ የአሜሪካ የበረራ አስተዳደር ባለሥልጣን እና የተለያዩ መንግሥታትን ያሳትፋል።

https://p.dw.com/p/3EojU
Äthiopien Flugzeugabsturz Ethiopian Airlines Flight ET 302
ምስል Reuters/T. Negeri

ካፒቴን አማረ ገብረሃና ስለ ቦይንግ 737-800 ማክስ

እሁድ ማለዳ ከቢሾፍቱ አቅራቢያ የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የበረራ መረጃ መቅጃ መሳሪያ ተገኝቷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባወጣው መግለጫ የዲጂታል የበረራ መረጃ መቅረጫ እና የአብራሪዎች ክፍል የድምፅ መቅጃ መሳሪያ መገኘታቸውን አረጋግጧል።

ካፒቴን አማረ ገብረሃና የበረራ መረጃ የሰነደው መሳሪያ "የአውሮፕላኑ ፍጥነት፤ በምን አይነት ኹኔታ እንደነበረ፤ በውስጡ የነበሩ እንቅስቃሴዎችን መዝግቦ የሚይዝ" መሳሪያ ሲሉ ይናገራሉ። የአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎት ምክትል ኃላፊ የሆኑት ካፔቴን አማረ የአብራሪዎች ክፍል የድምፅ መቅጃ መሳሪያ "በበረራ ሰራተኞች መካከል የነበረውን ንግግር፤ ከመቆጣጠሪያ ማማ ጋር የነበረውን ግንኙነት፤ በተለይ ደግሞ አብራሪው እና ምክትል አብራሪው እርስ በርሳቸው ሲያደርጉ የነበረውን ግንኙነት" ይይዛል። በተለይ ለአደጋ ምርመራ ወሳኝ የሆነ መሳሪያ በመሆኑ መገኘቱ እጅግ አስፈላጊ እንደነበር ጭምር ካፒቴን አማረ አስረድተዋል።

Äthiopien Flugzeugabsturz Ethiopian Airlines Flight ET 302
ምስል Reuters/T. Negeri

ወቀሳ የበረታበት ቦይንግ 737-800 ማክስ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በትናንትናው ዕለት አደጋ የደረሰበትን የመሰሉ አራት 737-800 ማክስ አውሮፕላኖች ላልተወሰነ ጊዜ ከበረራ አግዷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ "ምንም እንኳ የአደጋው መንስኤ ምን እንደሆነ ባናውቅም፤ ለጥንቃቄ እነዚህ አውሮፕላኖች እንዳይበሩ ወስነናል" ብሏል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራዎች ኃላፊ ካፒቴን ዮሐንስ ኃይለማርያም "ቦይንግ በመጨረሻ የሰራቸው የ737 ሞዴል ማክስ የሚባለው አውሮፕላን ነው። ከዚህ ቀደም ከነበሩት ትንሽ የቴክኖሎጂ ልዩነት አለው" ሲሉ ቢሾፍቱ አቅራቢያ አደጋ ስለገጠመው አውሮፕላን ይናገራሉ።

ካፒቴን አማረ በበኩላቸው "አውሮፕላኑ በጣም ጥሩ አውሮፕላን ነው። በጣም ዘመናዊ አውሮፕላን ነው። በተለይ በነዳጅ ቆጣቢነቱ በጣም የታወቀ ነው። ቴክኖሎጂው የወለደው አውሮፕላን ነው። በዚሁ በቴክኖሎጂው ምክንያት ደግሞ የሚመጡ የተለያዩ ችግሮች አሉ" ሲሉ ይናገራሉ።

በዕለተ እሁድ ከቢሾፍቱ አቅራቢያ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ቦይንግ 737 -800 ማክስ አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ ሌሎች አገሮች ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ አስገድዷቸዋል።

ቻይና የአገሪቱ አየር መንገዶች 737-800 ማክስ አውሮፕላኖችን ከበረራ እንዲያግዱ መመሪያ አስተላልፋለች። ኬይማን አየር መንገድ በኢትዮጵያ ከተከሰተው አደጋ በኋላ ሁለት 737-800 ማክስ አውሮፕላኖች ከበረራ ማገዱን አስታውቋል። የበረራ ተንታኙ አሌክስ ማቼራስ በትዊተር ገፃቸው እንደፃፉት በአሜሪካን አገር መንገደኞች በዚሁ አውሮፕላን ለመብረር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

Äthiopien Flugzeugabsturz Ethiopian Airlines Flight ET 302
ምስል Reuters/T. Negeri

ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በመጓዝ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ቦይንግ 737 -800 ማክስ አውሮፕላን የተከሰከሰው ከቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ከተነሳ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ነበር። ኢትዮጵያ አውሮፕላኑን ከአምራቹ ቦይንግ ኩባንያ የተረከበችው ኅዳር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ነበር።

ንብረትነቱ ላየን ኢየር የተባለው የኢንዶኔዥያ አየር መንገድ ተመሳሳይ አውሮፕላን ጥቅምት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ተከስክሶ 189 ሰዎች ሞተዋል።ካፒቴን ዮሐንስ ኃይለ ማርያም "ሁለቱን አደጋዎች ለማገናኘት ጊዜው ገና ነው። ምርመራው ሳይጠናቀቅ ሁለቱ ተያያዥ ናቸው ማለት ከባድ ነው" ብለዋል። ካፒቴን አማረ ግን በኢንዶኔዥያ እና በኢትዮጵያ የደረሱት አደጋዎች ይመሳሰላሉ ባይ ናቸው። ቦይንግ 737 -800 ማክስ በኢንዶኔዥያ ከገጠመው አደጋ በኋላ "የፌድራል አቪየሽን አድሚኒስትሬሽን እና የቦይንግ ኩባንያ ሲነጋገሩበት"እንደነበር ገልጸዋል። የበረራ ባለሙያው በመላው ዓለም 350 የዚሁ አይነት የአውሮፕላን ዝርያዎች ግልጋሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

የድምፅ ማዕቀፎቹን በመጫን ካፒቴን ዮሐንስ ኃይለማርያም እና ካፒቴን አማረ ገብረሃና የሰጧቸው አስተያየቶች ያድምጡ።

እሸቴ በቀለ

ተስፋለም ወልደየስ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ