1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተካረረው የአባይ ጉዳይና የብርቱኳን ቃለመጠይቅ

ዓርብ፣ ግንቦት 14 2012

የ«ሕዳሴው ግድብ» ግብፅ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያን አፋጦ የዓለም አቀፍ ተቋማት እና ታዋቂ ሰዎችንም ትኩረት ስቧል። የምርጫ ጉዳይ ዛሬም በኢትዮጵያ አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል። በኮሮና ጉዳይ ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ሰው የመዘናጋት ኹኔታ እያሳየ እንደኾነ ይነገራል።

https://p.dw.com/p/3cdTN
Äthiopien Luftbild Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre
ምስል DW/Negassa Desalegen

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የሕዳሴው ግድብ ጉዳይ ከግብፅ፤ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ባሻገር ዓለም አቀፍ ትኩረትን መሳብ ጀምሯል። የዓለም ባንክ እና ዩናይትድ ስቴትስ መጀመሪያ ሰሞን በሦስቱ ሃገራት ውይይት ላይ በ«ታዛቢነት» ብቅ ብለው ነበር። ኋላ ላይ ግን ግልጽ በኾነ መልኩ ለግብጽ ባጋደለ የ«ማደራደር» ሒደት መጠመዳቸው የበርካቶች መነጋገሪያ ኾኖ መሰንበቱ ይታወሳል።

የቄስ ጄሲ ጃክሰን ደብዳቤ

አኹን ደግሞ ግብጽ አቤት ለማለት የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤትን በር አንኳኩታለች። ኢትዮጵያም መልስ ስትሰጥ፤ በዩናይትድ ስቴትስ ታዋቂ የኾኑት ቄስ ጄሲ ጃክሰንም ለዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮችም ምክር ቤት ግብጽን በብርቱ የሚወቅስ ደብዳቤ አስገብተዋል። ደብዳቤው የብዙዎችን ትኩረት ስቧል፤ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮችም በስፋት ተዘዋውሯል።

ታዋቂው ጥቊር አሜሪካዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ ሲነሳ የሳቸውም ስም አብሮ ይነሳል። ገና ከለጋ እድሜያቸው አንስቶ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሲቪል መብቶች ተሟጋችነታቸው ዛሬም ድረስ ዝነኛ ናቸው። አሜሪካዊው የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ቄስ ጄሲ ጃክሰን።  

USA Gedenkgottesdienst für Boxer Muhammad Ali - Jesse Jackson
ምስል Reuters/L. Jackson

እኚሁ ቄስ ግብጽ የቅኝ ግዛት ዘመን ሕግጋት ላይ ዛሬም ተንጠልጥላለች በሚል ግብጽ ለጸጥታ ምክር ቤት ያስገባችውን ደብዳቤ በመቃወም በዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት የጥቊር እንደራሴዎች ኮሚቴ ሊቀመንበር ለኾኑት ካረን ባስ ከሰሞኑ እሳቸውም ደብዳቤ አስገብተዋል።

የግብፅ አቤቱታ በፀጥታው ምክር ቤት

ግብጽ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ያስገባችው ደብዳቤ ምላሽ ከማግኘቱ በፊት ጥቁር እንደራሴዎቹ ፈጣን ውሳኔ እንዲያሳልፉ ይጠይቃል ደብዳቤው። የቄስ ጄሲ ጃክሰን ደብዳቤን በትዊተር ገጹ ላይ ያያዘው ኄኖክ ኢትዮጵያ፦ በእንግሊዝኛ ቀጣዩን መልእክት ጽፏል። «ለመኾኑ ግብጽ በአባይ ወንዝ እና በሕዳሴ ግድብ ላይ የያዘችውን እርባና ቢስ የቅኝ ግዛት ዘመን አቋም  ከተከበሩ ቄስ ጄሲ ጃክሰን በተሻለ ያጋለጠ ይኖር ይኾን» በሚል ይነበባል የኄኖክ ጽሑፍ።

ቄስ ጄሲ ጃክሰን፦ «ቀስተደመና ለሰብአዊነት የተባበሩ ሕዝቦች ጥምረት» የተሰኘው ለማኅበረሰብ ለውጥ የሚታገል ድርጅት መሥራች እና መሪ ናቸው። ለካረን ባስ ባስገቡት ግብጽን የሚቃወም ደብዳቤያቸው መግቢያ፦ ግብፅ ከ11 የአፍሪቃ ሃገራት በተቃራኒ የቅኝ ግዛት ዘመን ውልን የሙጥኝ ብላ የዓለም ባንክን፤ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥትን እና የፀጥታው ምክር ቤትን እየተጠቀመችባቸው ነው ሲሉ ወቅሰዋል።  

ደብዳቤያቸውን የጻፉበትን ምክንያት ሲያብራሩም፦ «የግብጽ መንግስት በአባይ ወንዝ ላይ ፈላጭ ቆራጭ ሊያደርገው የሚያስችለውን የቅኝ ግዛት ዘመን ውል ኢትዮጵያ እንድትፈርም ጫና ለማሳረፍ ደብዳቤ ለጸጥታው ምክር ቤት ማስገባቱ እጅግ ረብሾኛል» ብለዋል።  በእርግጥም የግብፅ መንግሥት የ«ሕዳሴ ግድብ»ን በውኃ መሙላት እና ሥራ ማስጀመር በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ዜጎቼን ዋስትና አደጋ ላይ ይጥላል በሚል ለጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ደብዳቤ ጽፎ አስገብቷል።

Äthiopien Addis Abeba | Report | Grand Ethiopian Renaissance Dam
ምስል DW/N. Desalegen

ኢትዮጵያዊው ዲፕሎማት ነቢዩ ተድላ በትዊተር ገጹ ላይ፦ «በአፍሪቃ ከሕዝብ ብዛት 2ኛ በኾነችው ሀገር፤ ከ65 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ አቅርቦት የላቸውም» ሲል ጽፏል። «ያም በመኾኑ በኢትዮጵያ ኹለት ሦስተኛ የሚኾኑት ሕጻናት በጨለማ ውስጥ እንዲቆዩ ይገደዳሉ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶችም ውኃ ለመቅዳት እና የማገዶ እንጨት ለመሰብሰብ ረዥም ጉዞ ያደርጋሉ። እናም የሕዳሴው ግድብ እጅግ ወሳኝ ፕሮጀክት ነው» ብሏል።

መላኩ አዲራሮ በሚል የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «ኢትዮጵያ ግድቡን በውኃ ለመሙላት የግብጽን ፈቃድ እንድትጠይቅ በሕግ አትገደድም’ በውጭ ጉዳይ ሚንስተር ገዱ አንዳርጋቸው የተናገረው፤ እንቅጩን አወራላቸው፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን ለግብጽ አፍ አፏን የምያስይዝ እንደ ገዱ ያለ ሰውን እንፈልጋለን» ሲል ጽፏል።

«የግብፅን የተኮል አካሄድ ማመን አይቻልም። ኢትዮጵያ በአቋምዋ መፅናት አለባት የውኃው ሙሌት በጊዜው መጀመር አለበት፤ ግብፅን ማመን ቀብሮ ነው» በማለት ፌስቡክ ገጹ ላይ የጻፈው ደግሞ ዳንኤል አበበ ነው።

ቄስ ጄሲ ጃክሰን፦ ኢትዮጵያ ካልተሳተፈችበት ግብፅ የአባይ ወንዝ ምሉዕ ብቸኛ ተጠቃሚ እንደኾነች ከጠቀሰችበት እና እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1929 ካዘጋጀችው የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነት አንስቶ አቀራረቧ ጠብ አጫሪ ነው ብለዋል። በ1959 ግብጽ ከሱዳን ጋር የፈረመችውን ስምምነትም ቢኾን አኹንም ድረስ ዋጋ እንዳለው ትቆጥራለች ሲሉ የግብጽን አካሄድ በደብዳቤያቸው ነቅፈዋል። ከፕሬዚደንት አንዋር አንስቶ እስከ ሆስኒ ሙባረክ። ከፕሬዚደንት ሞሐመድ ሞርሲ እስከ አኹኑ ፕሬዚደንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ድረስ ያሉ የግብጽ መሪዎች «የቅኝ ግዛት ዘመን የአባይ ውኃ ውልን ለማስጠበቅ ጦርነት እስከመጠቀም የሚደርስ ማስፈራራት ይፈጽማሉ» ሲሉም የግብጽ አስተዳደርን በብርቱ ወቅሰዋል።

USA Wirtschaft Washington DC Zentrale der Weltbank Gebäude Logo
ምስል ullstein bild - Fotoagentur imo

የሀገራቸው የዩናይትድ ስቴትስት መንግሥት እና የዓለም ባንክ ታዛቢ ተብለው ግን ደግሞ ከማደራደር እስከ ሰነድ ማዘጋጀት የተጓዘበትን መንገድም «መሠረታዊ ኅጸጽ» ብለውታል። «ዩናይትድ ስቴትስም ኾነች የዓለም ባንክ ሕጋዊ ሠነዶችን እንዲያረቁ እና እንዲያዘጋጁ  ኢትዮጵያ ፈቃዷን አልሰጠችም አልተስማማችምም» ሲሉ ጽፈዋል። ሀገራቸው ዩናይትድ ስቴትስም ኾነች የዓለም ባንክ የተባለውን ሠነድ አዘጋጅተው ከኾነ ለታዛቢነት የተሰጣቸውን ሚና ጥሰዋል ብለዋል።  

ያም በመኾኑ አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ለፀጥታው ምክር ቤት ሚናቸው ማደራደር ሳይኾን ታዛቢነት እንደነበር ሊገልጡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። የአረብ ሊግ እና ግብጽ የቅኝ ግዛት ዘመን ውልን ይዘው የሚያደርጉትን ድርጊት የሚወቅስ መግለጫ በዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት የጥቊር እንደራሴዎች ኮሚቴ በፍጥነት  እንዲያወጣ ጠይቀዋል። ጉዳዩም ከምንም በላይ ትኩረት የሚያሻውና ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል።

«እውነት ይዘው ከጎናችን ስለቆሙ እናመሠግናለን። የአሜሪካ ምክር ቤት ትክክለኛ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ተስፋ አደርጋለሁ» ሲል ቄስ ጄሲ ጃክሰንን በማመስገን ፌስቡክ ላይ በእንግሊዝኛ የጻፈው ብሩክ ዋኬና ነው። እየሩሳሌም እሸቱ በበኩሏ፦ «ግድቡ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው። በድኅነት ማቀን እንሞታለን፤ አለያም በጀግንነት እየተዋጋን። ኹለተኛው ለልጆቻችን ብሩኅ ተስፋ ይፈነጥቃል። ግድቡ የእኔም ነው» በማለት ፌስቡክ ላይ በእንግሊዝኛ ጽፋለች። በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች የግብጽ፤ የዩናይትድ ስቴትስ እና የዓለም ባንክ ኢፍትሐዊ አካኼድን ኮንነዋል። የኢትዮጵያ አቋም እና የቄስ ጄሲ ጃክሰን ለእውነት በመቆም መቆርቆርን እጅግ አወድሰዋል።

ምርጫ በኢትዮጵያ

Äthiopien Sidama stimmen für Teil-Autonomie
ምስል AFP/M. Tewelde

የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው የምርጫ ሰሌዳ መሠረት መካሄድ እንደማይችል ከተገለጠበት ወቅት አንስቶ አነጋጋሪነቱ እንደቀጠለ ነው። የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ በዚሁ ጉዳይ ከሰሞኑ በሀገር ውስጥ ከሚገኝ አንድ የመገናኛ አውታር ጋር ያደረጉት ቃለ መጠይቅ የበርካቶችን ትኩረት ስቧል። ብዙዎች ቃለ መጠይቁን በተመለከተ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ጽፈዋል።

ዘአተ መድኅን በሚል የትዊተር ተጠቃሚ ቃለ መጠይቊ እንዳበሳጨው በመግለጥ፦ «ጋዜጠኛው ለቃለ መጠይቊ የነበረው ዝግጅት ዜሮ ነው። ይኽ በቅጥር ወቅት የፓርቲ ታማኝነት ከብቃት በልጦ ሲገኝ የሚከሰት ነው» ሲል በእንግሊዝኛ ጽፏል። «ቡርቴ ቀላል ሰው መስላሃለች...እንደ ሌላው መስላህ ተጨባጭ  ያልሆነ ነገር ይዘህ ስትቀርብ ረጋ ብላ በራስ መተማመን መንፈስ ትንን ታደርግልሃለች!» ሲል የጻፈው ደግሞ ካሳዬ በሚል ስም የትዊተር ተጠቃሚ ነው።

አብዛኛው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አስተያየቶች ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ በቃለ መጠይቁ ወቅት ያሳዩት ወጥ እና የተረጋጋ መንፈስን አድንቀዋል። ጋዜጠኛው በተገቢው መንገድ አለመዘጋጀቱን ብሎም የፖለቲካ ተጽእኖ ይጎትተው እንደነበር ጠቅሰዋል።

የኮሮና ተሐዋሲ

ኢትዮጵያ ውስጥ የጤና ሚንስትር ይፋ እንዳደረገው እስከ ዛሬ ድረስ 73,164 የኮሮና ተሐዋሲ መለያ ምርመራ ተከናውኖ 429 ሰዎች በኮሮና ተሐዋሲ ተጠቅተዋል። በ24 ሰአታት ውስጥ የሚደረጉ የምርመራ ውጤቶች እንደሚያመለክቱት ከኾነ በተሐዋሲው የሚያዘው ሰው ቁጥር ከቀድሞው እየጨመረ ነው።  ምናልባትም ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ ቀን ውስጥ የሚደረገው የምርመራ ቊጥር ቢጨምር አኹን ያለው ቊጥር የተለየ መልክ ሊኖረው እንደሚችል የሚጠቅሱም አሉ። ከ100 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ባሏት ኢትዮጵያ እስካኹን ድረስ በቀን የሚደረገው ምርመራ ከአምስት ሺህ  በታች ነው። ምርመራው ከአጀማመሩ አንጻር ሲታይ እድገት እያሳየ መኾኑን ግን ደግሞ የምርመራ ቊጥሩ ይበልጥ ማደግ እንዳለበት የሚጠቊሙ አስተያየቶች ብዙ ናቸው።  በድንበር አካባቢም ልዩ ቊጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ጠቊመዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ