1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተዘነጋዉ የዳርፉር ግጭት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 3 2005

ላለፉት አስር ዓመታት መኖሪያቸዉ ድንኳን እና መጠለያ ሆኗል። ሁለት መቶ ሺህ ከዳርፉር የተፈናቀሉ የሱዳን ስደተኞች ዛሬም ቻድ ዉስጥ ይገኛሉ።

https://p.dw.com/p/17vjh
ምስል picture-alliance / dpa

ጀርመን የሚኖረዉ አህመድ ሙሳ አሊ በየጊዜዉ «ዳርፉርን ርዱ» ከተሰኘዉ የረድኤት ድርጅት ጋር ወደሱዳን ይጓዛል። በስደተኛ መጠለያ የሚገኙ ሰዎች ጉዳይ ያሳስበዋል፤

«ሰዎች እንዲህ ረዥም ጊዜ ይቆያል ብለዉ ስላልጠበቁ ተስፋ የመቁረጡ ሁኔታ ከፍ ብሏል። ከመጠለያ ጣቢያዉ ዉጭ የደህንነታቸዉ ነገር አስተማማኝ አይደለም። ቻድም ራሷ የተረጋጋች ባለመሆኗ ሁኔታዉ በጣም አስከፊ ነዉ። ስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ያደጉት አብዛኞቹ ልጆች የትምህርት እድል አላገኙም።»

ድርጅቱ ዳርፉር ዉስጥ መሥራት እንዳልቻለ የሚገልፀዉ አሊ፤ የረድኤት ድርጅቶች ፈቃድ ከሱዳን መንግስት በቀላሉ ማግኘት እንደማይችሉ ነዉ የሚያስረዳዉ። እሱ እንደሚለዉ ለእያንዳንዱ ነገር ህጋዊ ፈቃድ ከመንግስት ማግኘት ያስፈልጋል። በዚህ ሁኔታ ዳርፉር ተነጥላ ለችግር እንደምትጋለጥ አንዳንድ ግብረሠናይ ድርጅቶች አስቀድመዉ ለሱዳን መንግስት አሳዉቀዉ እንደነበርም ያስታዉሳል።

Darfur - JEM Kämpfer
ምስል Getty Images

ቻድ ዉስጥ የሚገኙት ስደተኞችም ወደሀገራቸዉ መቼ ሊመለሱ እንደሚችሉ መገመት ተስኗቸዋል። የግጭት መንስኤን በሚያጠናዉ ሬፍትቫሊ ተቋም የሱዳን ጉዳይ አዋቂ ማግዲ ኤል ጊዞሊ እንደሚሉት ከሆነም ዳርፉር ዉስጥ በአጭር ጊዜ ሰላም የመስፈኑ ነገር አነጋጋሪ ነዉ፤

«ጦርነቱ ቀጥሏል፤ ነገር ግን የሚዋጉት ወገኖች ማንነት በሂደት ተቀይሯል። የዛሬ 10ዓመት በአማፅያንና በመንግስት ወታደሮች መካከል ነበር። እናም የዳርፉር የፀጥታ ሁኔታ ለመረዳት በጣም የሚያዳግት ነዉ። ምክንያቱም የመንግስት ተባባሪ የነበሩት ኃይሎዎች አሁን እርስ በዕርስ ነዉ የሚዋጉት።»

ከጎርጎሮሳዊዉ 2003ዓ,ም ወዲህ በምዕራባዊ ሱዳን ግዛት ዳርፉር የሚገኙ ወገኖች ከጦርነት የተላቀቀ ህይወት መምራት አልቻሉም። በአካባቢዉ የተካሄደዉ ዉጊያ 300,000 ሰዎች ፈጅቷል፤ ሁለት ሚሊዮኖቹን ለስደት ዳርጓል። በሱዳን ነፃ አዉጭ ጦር SLM በተሰኘዉ አማፂ ቡድን እና ነፍጥ ባነሳዉ በእስላማዊ ቡድን ለፍትህና እኩልነት ንቅናቄ መካከል በተደጋጋሚ ከባድ ዉጊያ በአካባቢዉ ተካሂዷል። በየጊዜዉ የጦርነቱ ሰለባዎች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል፤ ዓለምም ይህን እያስተዋለ ነዉ። የዳርፉር ግጭት ዓለም ዓቀፉን መገናኛ ብዙሃን ዋነኛ ርዕሰ ጉዳይ በመሆነበት ወቅት አሜሪካዊዉ የፊልም ተዋናይ ጆርጅ ክሉኒ የዓለምን ትኩረት ወደዚያ ለመሳብ ወዳርፉር ተጉዟል። ክሉኒ በየካቲት ወር ለዚህ ተግባሩ የጀርመን መገናኛ ብዙሃንን ሽልማት ቢያገኝም ዳርፉር ግን በዚህ ሀገር ያን ያህል የፕረስ ሽፋን አላገኘም።

UN UNAMID Sudan Darfur
ምስል UNAMID/AP

በጎርጎሮሳዊዉ 2007ዓ,ም የተመድ እና የአፍሪቃ ኅብረት በጋራ ለዳርፉር የሰላም ተልዕኮ UNAMIDን አዋቀረዉ ሰላም አስከባሪ ኃይል አሰማሩ። ከአራት ዓመታት በኋላ በሐምሌ ወር ቀጠር ላይ ሁለት የሰላም ስምምነቶች ተፈረሙ። የሱዳን መንግስትና የፍትህና የእኩለት ንቅናቄ JEM ተኩስ ለማቆም ተስማሙ። ሆኖም ይህ ስምምነት ያመጣዉ ሰላም የለም ይላሉ በኒዉዮርክ የተመድ ቃል አቀባይ ኤሪ ካንኮ፤

«ዳርፉር ዉስጥ የተለያዩ አንጃዎች እና የተለያዩ ጎሳዎች ይንቀሳቀሳሉ። መንግስት ለምሳሌ ከሁሉም ሳይሆን ከጥቂቱ ጋ የሰላም ዉል ተፈራርሟል። ለዚህ ነዉ እኛ ዓለም ዓቀፉ ኅብረተሰብ ትኩረቱን እዚያ አድርጎ ሁሉም ቡድኖች መሳሪያቸዉን ማስቀመጣቸዉን እንዲያረጋግጥ የምንጠይቀዉ።»

በአሁኑ ሰዓት የUNAMID ሰላም አስከባሪ ኃይሎች አማፅያኑ መሳሪያቸዉን እንዲያስረክቡ እያግባቡ ነዉ። በእርግጥ በያዝነዉ ዓመት ሐምሌ ወር ላይ የUNAMID ተልዕኮ ያበቃል፤ ሆኖም ለስድስተኛ ጊዜ ተልዕኮዉ ይራዘም አይራዘም የሚለዉን የፀጥታዉ ምክር ቤት በሚቀጥለዉ ወር ይወስናል። ያኔ ምናልባት የተዘነጋዉ የዳርፉር ግጭት ይዞታ ዳግም በዓለም መድረክ መወያያ ይሆናል የሚል ተስፋ አለ።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ