1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተጠናከረው የተፈጥሮ ቁጣ

ማክሰኞ፣ ጳጉሜን 2 2013

የአየር ንብረት ለውጥ ውሎ እያደረ እውንነቱን እያሳየ መምጣቱን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ተመራማሪዎች ማስረጃ መጥቀስ ከማያስፈልጋቸው ደረጃ መድረሳቸውን ይናገራሉ። ባለፈው እና በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የተደረሱ ተከታታይ የተፈጥሮ ቁጣዎች በሚቀጥሉት ዓመታት በእጥፍ ተጠናክረው እንደሚከሰቱም ከወዲሁ ያስጠነቅቃሉ።

https://p.dw.com/p/402cw
Griechenland | Waldbrände auf der Insel Evia
ምስል Nikolas Economou/REUTERS

የዘንድሮው የተፈጥሮ አደጋ

ያለፉት ወራት ሐምሌ እና ነሐሴ ጠንከር ያለ የተፈጥሮ ቁጣ የታየባቸው ወራት መሆናቸው ተመዝግቧል። እሳት ያስከተለው ደረቅ አየር በደቡብ አውሮጳ ሃገራት፤ በሩሲያ እና በሰሜን አሜሪካ የሰደድ እሳት ሲቀሰቅስ፤ ለቀናት የወረደው ከባድ ዝናብ ደግሞ በምዕራብ አውሮጳ፤ አፍሪቃ እና እስያ ውስጥ አደገኛ ጎርፍ አስከትሏል። ባለፉት ወራት በተለያዩ ሃገራት የተከሰተው የተፈጥሮ ቁጣ በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ በማለፉ የበርካታ ወገኖች ኑሮ ተናግቷል፤ በየሃገራቱም የኤኮኖሚ አቅም ላይ ተጽዕኖውን አሳርፏል። በቀጣይስ?

1000 ስኩየር ኪሎ ሜትር ያዳረሰ ሰደድ እሳት ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለባት ግሪክ የአየር ንብረት ቀውን የሚመለከት አዲስ ኮሚቴ ለማቋቋም ተገድዳለች። 170 ሺህ ሄክታር መሬት ያካለለው ቱርክን ከሁለት ሳምንት በላይ ያስጨነቀው የሰደድ እሳትም በሀገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ እጅግ የከፋ መሆኑ ተመዝግቧል። በምዕራብ አውሮጳ የነበረው ከፍተኛ ሙቀትም ስፔን እና ፈረንሳይንም ለሰደድ እሳት አጋልጧል። ወደ ሰሜን አሜሪካም ካናዳ እና ዩናይትድ ስቴትስ እሳት ሲያጠፉ ነው የከረሙት፤ ከእሳቱ በተጓዳኝ የባሕር ማዕበል እና ውሽንፍር ያጀበው ከባድ ዝናብ ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል። ኃይለኛው ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በምዕራብ የጀርመን ግዛት፣ በቤልጂየም፣ ኔዘርላንድ እንዲሁም ሌሎችም ሃገራት ሕይወት አጥፍቷል ከፍተኛ የንብረት ውድመት አስከትሏል። በተለያዩ ሃገራት የታየው የተፈጥሮ ቁጣ በአመዛኙ የአየር ንብረት ለውጥ አይነተኛ ማሳያ ተደርጎ ነው የተወሰደው። የዘርፉ ባለሙያ እና በካናዳ ካልጋሪ ዩኒቨርሲቲ የአዛላቂ ምርት እና አገልግሎት ልማት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ጌታቸው አሰፋ የተመለከትነው የተፈጥሮ አደጋ ያልተጠበቀ አይደለም ነው የሚሉት።

USA Nach Hurricane Ida
አይዳ የተሰኘው ከባሕር የተነሳው ሞገድ በዩናይትድ ስቴትስ ምስል Mike Segar/REUTERS

 «በሳይንሱ ዓለም ይኽ ድንገቴ አይደለም፤ ለብዙ ዓመታት በየትኛው ወቅት በምን ሁኔታ፤ በየትኛው ቦታ ምን ሊሆን እንደሚችል ሲነገር የነበረ፤ እየተነገረም ያለ ነገር ነው።» እናም ፕሮፌሰር ጌታቸው እንደሚሉት በመከታተል የሚከሰቱት የተፈጥሮ አደጋዎች የሰዎች እንቅስቃሴ እና አካባቢው የሚሸከመው የጫና ብዛት ሚዛን የመሳቱ ማሳያ ነው።  በአሁኑ ጊዜ በተደጋጋሚ የሚታዩት የተፈጥሮ አደጋዎች ቢያንስ ላለፉት 150 ዓመታት ታይተው እንደማያውቁ ያመለከቱት የዘርፉ ተመራማሪ ትርጉም ያለው ሥራ ካልተሠራ እየባሰ ይሄዳል ባይ ናቸው።

Türkei | Waldbrände in Mugla
በቱርክ ሰደድ እሳት ያደረሰው ውድመትምስል Umit Bektas/REUTERS

የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎችም ሆኑ የዘርፉ ተመራማሪዎች በየጊዜው በተለይ በኢንዱስትሪ የበለጸጉት ሃገራቱ የፖለቲካ መሪዎች በየበኩላቸው ተገቢውን የበካይ ጋዞች ቅነሳ ተግባራዊ ርምጃ እንዲወስዱ ጥሪያቸውን ያቀረባሉ። ፖለቲከኞቹም በሚያገኙት መድረክ ሁሉ ቃል ይገባሉ። ተግባራዊ ርምጃው ግን ዛሬም ብዙ ይቀረዋል። ኮቪድ 19 በወርሽኝነቱ ዓለምን ባስደነገጠበት በጎርጎሪዮሳዊው 2020 ዓ,ም የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት በበርካታ ሃገራት በተደነገገው የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት መጠነኛ የብክለት ቅነሳ ታይቶ እንደነበር አይዘነጋም።  ፕሮፌሰር ጌታቸው እንደሚሉት ግን በአጭር ጊዜ ያን ያህል ለውጥ ይመጣል ብሎ መጠበቅ አይቻልም።

Überschwemmung Bangladesch
ጎርፍ በባንግላዴሽምስል Fatima-Tuj Johora/picture alliance/ZUMAPRESS.com

ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመትም ሆነ ዘንድሮ የታዩት የተፈጥሮ አደጋዎች በኢንዱስትሪ የበለጸጉት ሃገራት የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪ አካላት የሚወስዱትን የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ቅነሳ እንዲያጤኑት ግድ ሳይላቸው የቀረ አይመስልም። ምናልባት በመጪው ጥቅምት ወር ማለቂያ ግላስጎው እንግሊዝ ላይ በሚካሄደው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ ወደ ተግባራዊ ርምጃ እንዲሸጋገሩ ገፊ ምክንያት ይኾን?  «ተስፋ መቼም አይቋረጥም፤ ግን አያደርጉም ብዬ ነው የምሰጋው። ደጋግመን እንደምንለው አሁንም እንዳልነው፤ የሳይንሱ ዓለም ድርሻው መረዳት እና መለካት ላይ ነው፤ እናም የተወሰነ ድጋፍ ካገኘ ደግሞ ከፖለቲከኞች መከወን ነው። በተግባር ያንን መግለጽ።»

USA Hurricane Ida Wirbelsturm New York
ጎርፍ ኒዉዮርክ ዩናይትድ ስቴትስምስል Ed Jones/AFP/Getty Images

በዚህ መሀልም ከፓሪሱ የብክለት ቅነሳ ስምምነት በቀድሞ ፕሬዝደንቷ ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ የወጣችው ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ስምምነቱ እንደምትመለስ እየተጠበቀ ነው። በኢንዱስትሪ የበለጸጉትም ሆነ ወደዚያው እየተጓዙ የሚገኙት ሃገራት በሚያካሂዱት የኤኮኖሚ እና ፖለቲካ ሽኩቻም ለብክለቱ እጅግም አስተዋጽኦ የማያደርጉ ሃገራት ሕዝቦች ዕዳ ከፋይ መሆናቸውንም አጽንኦት ሰጥተዋል። በከባቢ አየር በካይነት ቻይና ግንባር ቀደሟ ስትሆን፤ ከእሷ የምትከተለው ዩናይትድ ስቴትስ ናት። የአውሮጳ ሃገራት ብሪታያን ጨምሮ፤ ሕንድ፣ ሩሲያ እና ጃፓንም ከቀዳሚዎቹ እና ዋነኞቹ ተርታ ተሰላፊዎች ናቸው። የአየር ጠባይ ይዞታው ከዓመት ዓመት ድርቅ እና ሰደድ እሳት፤ በሌላ ጎኑ ደግሞ ከባድ ዝናብና ጎርፍ እያፈራረቀ ነው። በቀጣይ ክረምቱስ እንዴት ይኾን የሚለው ስጋትም አለ። የዘርፉ ተመራማሪ ፕሬፌሰር ጌታቸው እንደገለጹን የዓለምን የሙቀት ሚዛን የሚያስጠብቁ ዋና ዋና የሚባሉ የተፈጥሮ ሞተሮች ያሏቸው ይዞታዎች እየተዳከሙ እና እየተሸረሸሩ መሄድ ከተፈጥሮ አደጋዎች ስጋት እፎይታ ሊያመጣ የሚችለውን የመሬትን የሙቀት መጠን ቅነሳ ከሚፈለገው ግብ ለመድረስ የተቀናጀ እና ዘላቂነት ያለው ጥረት ይጠይቃል። ለዚህም ለዚህ ደግሞ ታሪካዊ እና አሁናዊ ኃላፊነት ያለባቸው በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያደጉ ሃገራት ጉልህ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል። ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ ፕሮፌሰር ጌታቸው አሰፋን እናመሰግናለን።

USA Hurricane Ida Wirbelsturm Louisiana
ሉዊዚያና የአይዳ ማዕበል ሰለባዎችምስል Adrees Latif/REUTERS

ሸዋዬ ለገሠ 

ነጋሽ መሐመድ