1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተፈናቃዮች ሁኔታ በኦሮሚያ 

Merga Yonas Bula
ማክሰኞ፣ ግንቦት 14 2010

ከኦሮሚያ ክልልና ከኢትዮጵያ ሶማሌና አዋሳኝ ድንበር አካባቢ በተፈጠረዉ ግጭት የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ 857,000 ይጠጋሉ።

https://p.dw.com/p/2y84b
Äthiopien Somalia Vertriebene Menschen
ምስል DW/B. Girma

The Saga of Displaced people in Oromia - MP3-Stereo

ከተጠቀሰው ቁጥር ከ120 ሺህ በላይ ተፈናቃዮችን እስከ ግንቦት ወር 2010 ዓ/ም መጨረሻ ድረስ በኦሮሚያ ልዩ ዞን በ11 ከተሞች ዉስጥ የማስፈር ዝግጅት መኖሩን የተፈናቃዮች ድጋፍ አስተባባሪና መልሶ ማቋቋም ኮሚቴ አባል ቀሲስ በላይ መኮንን ለዶይቼ ቬሌ ገልፀዋል።

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብና በምሥራቅ ሐረርጌ ዉስጥና አካባቢ፣ ማለትም በደደር፣ በጭሮ፤ በሐማሬሳና በድሬ ዳዋ የነበሩት መጠለያዎች እንደተዘጉም ቀሲስ በላይ ይናገራሉ። በድሬ ዳዋ የነበረዉ መጠለያ ትናንት መዘጋቱን ይፋ ያደረገዉ የኦሮሚያ ክልል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በመጠለያዉ የነበሩ 2,776 በኦሮሚያ ልዩ ዞን እንዳሰፈራቸዉም ገልፀዋል።

ተፈናቃዮቹ የመጠለያ ቦታ ቢያገኙም አሁንም የተፈጥሮና ሰዉ ሠራሽ ችግሮች እያጋጠማቸዉ እንደሆነ ለዶይቼ ቬሌ ገልፀዋል። ለምሳሌ ባለፈዉ ሐሙስ ኃይለኛ ንፋስ ቀላቅሎ የወረደው ዝናብ በኦሮሚያ ልዩ ዞን በዱከምና በገላን ከተሞች የተገነቡት መጠለያ ቤቶችና ሰዎች ላይ አደጋ ማድረሱ ቀሲስ በላይ ለዶይቼ ቬሌ ገልፀዋል። በክልሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የወጣ መረጃ እንደሚመለክተዉ ዝናቡ የ314 ቤቶች ቆርቆሮ ሙሉ በሙሉ በማፍረስ ወደ 4,7 ሚሊዮን ብር ንብረት አውድሟል።

Äthiopien Somalia Vertriebene Menschen
ተፈናቃዮች በሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ዉስጥ ምስል DW/B. Girma

ከጅግጅጋ መፈናቀሉን የሚናገረዉ ደረጀ ጌታቸዉ በበኩሉ አሁን በአዲስ አበባ የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ በጎታራ ቅርንጫፍ ግቢዉ ዉስጥ እንዲሰፍሩ ከተደረጉት ከ2000 አባዋራዎች ዉስጥ 600ው በግቢዉ እንደሚገኙና ቀሪዎቹ ደግሞ ከተማው ዉስጥ በየዘመዶቻቸው ዘንድ መጠለላቸውን ገልጿል። ብራሃኑ ግርማ የተባለዉ ሌላ ተፈናቃይ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጠለያ ቦታ እንደሚገነባ ቃል  ቢገባም እስካሁን እንዳልፈፀመው ይጠቅሳል።

የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጠባብ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ብርሃኑ የክረምቱን ዝናብ ለመቋቋም ያሉትን ድንኳኖች የዝናብ ሸራ ገዝተው እንዳለበሱ፤ ግን ደግሞ ሰዉ በሚተኛበት ጊዜ ዝናቡ ከስር እየገባ አስቸጋሪ መሆኑን አክሎበታል። ከክልሉ ባለስልጣኖች በኩል የበለጠ መረጃ ለማግኘት ያደርግነዉ ሙከራ አልተሳካም።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሰ