1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተፈጥሮ አካባቢ ይዞታ

ረቡዕ፣ ኅዳር 24 2001

«የባንኮችን ክሥረት ለማካካስ መንግሥታት ወዲያው በቢልዮንና ትሪሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሲመድቡ፣ ጥፋት የተደቀነባትን ፕላኔታችንን ለመታደግ ግን፣ አንዳች እርምጃ አይወሰድም » ራጀንደራ ፓቾሪ፣

https://p.dw.com/p/G8jH
«ግሪን ፒስ» ፕላኔታችን ጥፋት እንዳንዣበበባት ለማሳሰብ ፣በዐራራት ተራራ የገነባው ተምሳሌታዊው መርከብ፣ምስል picture-alliance/ dpa

በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን ፣ ይበልጥ የምናተኩረው ፣ ከሚታሰበውና ከሚነገረው በላይ አሥጊ ሁኔታ ላይ በሚገኘው የዓለም የአየር ንብረትም ሆነ የተፈጥሮ አካባቢ ይዞታ ላይ ይሆናል። በቅድሚያ ግን የኅዋን ጉዞም ሆነ ቱሪዝም የሚመለከት ዜና እናስቀድማለን።

እንደ የብስና አየር የማጓጓዣ አገልግሎት ውድድር ፣ የኅዋውም ተጫራቾችም ሆኑ ተወዳዳሪዎች ገጠሙት። ዜናው ለተጓዦች እሰየው!የሚያሰኝ ሆኗል። Xcor Aerospace Incየተባለ በካሊፎርኒያ የሚገኝ የ Virgin Galactic ተፎካካሪ የሆነ ኩባንያ ወደፊት ወደ ኅዋ የሚጓዙ ሰዎችን በ 95,000 ዶላር ክፍያ ከመሬት 61 ኪሎ ሜትር ፈንጠር ብሎ በአመዛኙ የምድር ስበት ከሌለበት ቦታ አድርሶ እንደሚመልስ አስታወቀ። Lynx በሚሰኝ ልዩ አኤሮፕላንም ሆነ መንኮራኩር 30 ደቂቃ በሚወስደው የአንድ ጊዜ ደርሶ-መልስ በረራ፣ ከአብራሪው ጋር አንድ ቱሪስት ብቻ ነው የሚጓዘው። ይህም የጉዞ መርኀ-ግብር፣ ከካሊፎርኒያ ሞጄቭ በረሃ ምሽግ የሚጀመረው ፣ እ ጎ አ በ 2010 ዓ ም ሲሆን ፣ ቀዳሚውን ዕድል በማግኘት የተመዘገቡት የኅዋ ቱሪስት Per Wimmer የተባሉ ደንማርካዊ የባንክ ኀላፊ ናቸው። አብራሪው፣ ጡረታ የወጡት የአየር ኃይል ኮሎኔልና ከ NASA እ ጎ አ በ 1998 ዓም ከመልቀቃቸው በፊት 3 ጊዜ ወደ ኅዋ የተጓዙት ጠፈርተኛ Richard Searfoss ናቸው። በሌላ በኩል፣ ቨርጂን ጋላክቲክ የተሰኘው የኅዋ ቱሪዝም ጀማሪው ድርጅት፣ 200,000 ዶላር በመክፈል ወደ ኅዋ ለመጓዝ መፈለጋቸውን ያስታወቁና ፣ አስቀድመው 20,000 ዶላር ቀብድ የከፈሉ ከ 200 በላይ ደንበኞችን መመዝገቡን አስታውቋል። በብሪታንያው ከበርቴ የሚመራው ቨርጅን ጋላክቲክ ደንበኞቹን ከመሬት 110 ኪሎሜትር ርቀት ስበት ምንም ከሌለበት (0 ከሆነበት) ቦታ አድርሶ፣ አንድ ደቂቃ ከመንኮራኩር ውጭ እንዲንሳፈፉ፣ ምድርንም ከኅዋ እንዲመለከቱ አድርጎ እንደሚመልሳቸው ነው ያስታወቀው። ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ በሚጀመረው መርኀ-ግብር ፣ ቨርጂን ጋላክቲክ Space Ship Two የተሰኘ 8 ሰዎችን የሚያሣፍር መንኮራኩር ነው የሚያዘጋጀው። ፍጥነቱ ከድምፅ ፍጥንት 5 እጥፍ ይበልጣል ነው የተባለው። «ዲስካቨሪ» የተሰኘችው የአሜሪካ መንኮራኩር ለምሳሌ ያህል 25 እጥፍ መምጠቅ መቻሏ ነው የተጠቀሰው። Lynx መንኮራኩር ፣ ማምጠቂያ ሮኬት የማያስፈልገው፣ በቀጥታ እንደ አኤሮፕላን ተንኮብኩቦ የሚነሣና ተመልሶ የሚያርፍ ነው። የሚያስፈልገው 3,033 ሜትር ርዝማኔ ያለው መንኮብኮቢያ ጣቢያ ብቻ ነው።

ስለኅዋ ጉዞ ካነሣን ፣ ጠፈርተኞች እንደሚያደረጉት ሁሉ፣ የኅዋ ቱሪስቶችም ጠቅላላ ሰውነታቸውን የሚሸፍን ልዩ ልብስ እንደሚያስፈልጋቸው የታወቀ ነው። ግን ለምን?

ጠፈርተኞች ለምን ከአግር ጥፍራቸው እስከ ራስ ፀጉራቸው የሚሸፍናቸውን ልዩና ወፈር ያለ ልብስ ይለብሳሉ። በኅዋ የመከላከያ ልብስ የሌለው ጠፈርተኛ ሳምባውን አየር አጣብቆ፣ ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ ስለሚሆንበት፣ ለመተንፈስ ይቸገራል። በሠራ አካላቱ የሚገኝ ውሃ ይፈላል፣ ኅዋሳቱ፣ ከአካል ግድግዳ ተመንጥቆ መውጣት ነው የሚቃጣቸው። የጠፈርተኛ ልብስ የሌለው ፣ እጅግ ኃይለኛ በሆነ ቅዝቃዜ ድርቅ-ኩምትር ነው የሚለው። ተፈራራቂ ሙቀትም፣ ክፉኛ ይጠብሰዋል። ለምሳሌ ያህል፤ የፀሐይ ብርሃን በሚያገኘው የጨረቃ ክፍል የሚገኝ ጠፈርተኛ 120 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በሆነ ሙቀት ነው የሚጠበሰው። ማታ፣ ፀሐይ በማታበራበት ክፍል ከሆነ ደግሞ፣ ከዜሮ በታች 140 ዶግሪ ሴንቲግሬድ ገደማ በሚደርስ ቅዝቃዜ፣ ዕጣው፣ እንደ እንጨት መድረቅም ሆነ መኮማተር ነው የሚሆነው። ይህን ከመሰለው መጠን የለሽ የሙቀትና የቀዝቃዜ መፈራረቅ፣ እንዲሁም ለጤነነት እጅግ አደገኛ ከሆኑ ከኅዋ ከሚፈነጥቁ ጨረሮች ራስን ለመከላከል የጠፈርተኛ ልዩ ልብስ የግድ አስፈላጊ ነው።

ከዚያው ከኅዋ ታሪክ ሳንወጣ፣ ስለኅዋ ፣ ከ-እስከ---ርቀት-- ግዝፈት ለመግልጽ ቃላት እንደማይገኙ የታወቀ ነው። ስለዚህ ጠልቆ ማሰቡ፣ ምናልባት ናላ ያዞር ፣ ወይም እንቅልፍ ያስወስድ ይሆናል። የሆነው ሆኖ፣ ርቀቱ፣ ግዝፈቱ እንደተባለው በመሆኑ፣ ለርቀቱ መለኪያ ኪሎሜትር ወይም ማይልስ ሳይሆን የብርሃን ዓመት ነው ለመለኪያነት የሚውለው። ብርሃን በዐይን የማይታይ አየርም ሆን ግዝፍ ያለው ነገረ ሳያግደው በባዶ ቦታ (Vacuum) በሴኮንድ 299,792,458 ሜትር(ከሞላ ጎደል በሴኮንድ 300ሺ ሜትር ) እንደሚመጥቅ የታወቅ ነው። በደቂቃ፣ በሰዓት ፣ በቀን፣ በዓመት ምን ያህል እንደሚጓዝ ማስላቱ አይከብድም። አንድ የብርሃን ዓመት እንግዲህ፣ ብርሃን አንድ ዓመት ሙሉ የሚጓዘው ርቀት 9,4 ቢልዮን ኪሎሜትር ነው። አንድ ሰው፣ ይህን ርቀት በአግር ጉዞ ለማገባደድ ምን ያህል ጊዜ ይወስድበታል? በመጀመሪያ፣ ሰው ምን ያህል ዘመን ይኖራልና ነው እንዲህ ዓይነት ጥያቄ የሚጠየቀው? የማትሉ አትታጡም!። እኛም በነባቤ ቃልነት ለነገሩያህል ነው ያወሳነው። እናም መልሱን ማቅረቡ አይግድም። አንድ ሰው፣ በእግር ጉዞ፣ አንድ የብርሃን ዓመት ለመጓዝ፣ እንበል ዘንድሮ እግቡ ድርሶ ጉዞውን ቢፈጽም፣ መንገድ የጀመረው ከ 225 ሚልዮን ዓመት በፊት ነበረ ማለት ነው። አንድ መጣቂ መንኮራኩር፣ አንድ የብርሃን ዓመት ለመጓዝ ፣ 95,000 ዓመት ነው የሚያስፍልገው!።

-----------------------------------------------------

ከባቢ አየርን ከብክለት የመከላከሉ ዓለም አቀፍ ጥረት ፣ አስፈላጊነቱ ፣ በዓለም ዙሪያ ፣ በተለያዩ ዐበይት ከተሞች፣ እስካሁን ሲካሄዱ በቆዩ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች ቢመክርበትም ፣ አጠቃላይ ከሆነ የጋራ ስምምነት ላይ ለመድረስ ባለመቻሉ፣ አደጋው ፣ ከዕለት ወደ ዕለት ከዓመት ወደ ዓመት አየተባባሰ በመሄድ ላይ ይገኛል። IPCC በሚል ምኅጻር የታወቀው በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚወያየው የበይነ-መንግሥታት የምክክር መድረክ፣ እንዲሁም Green Peace እና የመሳሰሉ መጠበቅ አጥብቀው የሚታገሉ ድርጅቶች በየጊዜው ቢያሳስቡም፣ እስካሁን ያን ያህል አመርቂ ተግባር ሲፈጸም አልታየም። የአየር ንብረት ለውጥ ፣ ሰው ያመጣው ጣጣ ነው። አምና የተሠራጨው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉዳይ ምክር ቤት 4ኛ ሪፖርትም ይህንኑ ነው ያረጋገጠው። በዓለም ዙሪያ በመከሠት ላይ ያለው የአየር ጠባይ ለውጥ፣ ከታሰበው በላይ አስፈሪ መልክ ይዟል። በአሁኑ ጊዜ፣ ከከባቢ አየር ጋር የሚቀላቀለው የተቃጠለ አየር እ ጎ አ በ 1970 ዓ ም ከነበረው በአጥፍ ከፍ ያለ ነው። እ ጎ አ ከ 1750 ዓ ም አንስቶ ፣ ሰው ራሱ በተቃጠለ አየር፣ የምድራችንን ከባቢ አየር እየበከለ ያለበት ድርጊት ሳያቋርጥ አንደቀጠለ ነው። በርሊን አቅራቢያ ፖትስዳም የሚገኘው የአየር ንብረት ተቋም ኀላፊ ሃንስ ዮዐኺም ሸልንሁበር ---

«በአሁኑ ወቅት ሊተኮርበት የሚገባ ዓላማ ፣ የምድራችን የሙቀት መጠን ከ2 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ እንዳይጨምር መታገል ነው። ከዚያ በላይ ከተውጣጣ ግን፣ መመለስ በሚያዳግትበት የጥፋት ጎዳና መራመድ ግድ ይሆናል።»

የዓለም የአየር ንብረት ጉዳይ ምክር ቤት ባቀረበው ዘገባ የተሳተፉት ሌላው ባልደረባቸው ፣ የእርከናዊ ከባቢ አየር ተመራማሪ Wolfgang Lucht---በበኩላቸው እንዲህ ይላሉ።----

«የታወቀው የእንግሊዙ የአየር ንብረት ምርምር ማእከል፣ Hadley Centre በትክክል እንዳመላከተው በያዝነው በ 21ኛው ክፍለ-ዘመን ውስጥ በአማዘን የዝናሙ መጠን በጣም እየቀነሰ ይሄዳል። በገፍ ዝናም የሚያገኘው የአማዞን ጥቅጥቅ ያለ ደን ፣ ውሃ አጥቶ የሚጠፋበት ጊዜ ማጋጠሙ አይቀርም።»

በብዙው የአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም አካባቢና በሜድትራንያን የባህር አዋሳኝ አገሮች ድርቅ ይባባስ ካልሆነ በስተቀር የሚገታበት ምልክት አይታይም። ሌሎች አገሮችም በጎርፍ ማጥለቅለቅ ይጨነቃሉ። እስያ ውስጥ በሂማላያ ተራሮች ፣ በደቡብ አሚሪካ በኤንደስ ተራሮች፣ አውሮፓም ውስጥ በአልፕስ ተራሮች የረጋ በረዶ በአፋጣኝ እየቀለጠ የሚያስከትለው ጉዳት የአንድ ወቅት በቻ ሆኖ አይቀርም።

በሰሜን የምድር ዋልታና ባካባቢው በግሪንላንድ፣ እንዲሁም በደቡብ የምድር ዋልታ በአንታርክቲካ የበረዶ ቁልልም ሆነ የበረዶ ተራራ እየቀለጠ ያለበት ሂደት ፣ በተለይ በሰሜን የምድር ዋልታ የሚታየው፣ መዘዙ ቀላል አለመሆኑን የአየር ንብረት ጠበብት ከማስጠንቀቅ የቦዘኑበት ጊዜ የለም።

በአንታርክቲካና በግሪንላንድ የበረዶ ክምር መሟሟት ፣ የውቅያኖስ የባህር ልክ ከ 60 ሴንቲ ሜትር በላይ ከፍ እንዲል በማድረግ ለመገመት የሚያዳግት ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችልም ጠበብት እየጠቆሙ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጥበቃ ነክ መደረክ እንደገለጸው ሰዎች ለመግታት ሳይጥሩ ቀርተው እየተትጎለጎለ ከከባቢ አየር ጋር በሚቀላቀል የተቃጠለ አየር ሳቢያ፣ በዚህ ምዕተ-ዓመት ውስጥ የባህሮች ልክ ከ 18-59 ሴንቲሜትር ከፍ ማለቱ አይቀርም።

የኖቤል ተሸላሚ የሆነው የዓለም በይነ-መንግሥታት የአየር ንብረት ጥብቃ ነኩ የውይይት መድረክ ሊቀመንበር ህንዳዊው ራጀንደራ ፓቾሪ፣ በዓለም ዙሪያ የተፈጥሮ አካባቢን ለመንከባከብ ፣ ያን ያህል ከልብ ጥረት አይደረገም በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል። «የባንኮችን ክሥረት ለማካካስ መንግሥታት ወዲያው በቢልዮንና ትሪሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሲመድቡ፣ ጥፋት የተደቀነባትን ፕላኔታችንን ለመታደግ ግን፣ አንዳች እርምጃ አይወሰድም »ሊቁ በማዘን እንደገልጹት!።

ፖላንድ ውስጥ ከትናንት በስቲያ ተከፍቶ ለ 2 ሳምንታት የሚዘልቀው በ ተ መ ድ የበላይ ተጠባባቂነት በመካሄድ ላይ ያለው የአየር ንብረት ጥበቃ ነክ ጉባዔ ፣ እ ጎ አ ከ 2012 ዓ ም በኋላ ሰው ሰራሽ የተቃጠሉ ጋዚዞችን ለመግታት ውል ያለው እርምጃ መውሰድ ካልተቻለ፣ ቀጣዩ ዘመን ለፕላኔታችን ፣ ጥፋት የሚቀየስበት ይሆናል በማለት አስጠንቅቀዋል። በፖዝናን (ፖዘን) ፖላንድ በመካሄድ ላይ ያለው ጉባዔ በመጪው ዐመት በታህሳስ ወር ከፐንሀገን፣ ደንማርክ ውስጥ በሚከናወን ዐቢይ ጉባዔ በውል እንደሚታሠር ነው የሚጠበቀው። ለዚህ እጅግ ተፈላጊ እርምጃም ሆነ ውል አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር አዎንታዊ ተሳትፎ ያደርጋል የሚል ሙሉ ተስፋ ተጥሎበታል። ራሳቸው ራጀንድራ ፓቾሪ፣ ከአዲሱ የአሜሪካ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ባራክ ዖባማ ጋር ለ 10 ደቂቃ ያህል ተገናኝተው ለመነጋገርና መልእክታቸውን ለማስረዳት አጥብቀው እንደሚሹ ነው የገለጹት።