1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተፈጥሮ አደጋዎች በ2013

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 22 2006

የጎርጎሪዮሳዊዉ የዘመን ቀመር 2013 የተለያዩ የተፈጥሮ ቁጣና አደጋዎችን አስተናግዷል። የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ኃያል ማዕበልና ሞገዶች፤ ጎርፍና ድርቅ።

https://p.dw.com/p/1Ajot
ምስል picture-alliance/dpa

በተሰናባቹ 2013ዓ,ም በዓለማችን ከደረሱ ከፍተኛ የተፈጥሮ ቁጣዎችና አደጋዎች በኅዳር ወር መባቻ ፊሊፒንስን የመታዉ የባህር ሞገድ የተቀላቀለበት አዉሎ ነፋስ ባደረሰዉ ጉዳት ብቻ ሳይሆን በጠንካራነቱ ከሚታወሱት መካከል ግንባር ቀደሙ ነዉ። ዎርልድ ቪዥን የተሰኘዉ ግብረሠናይ ድርጅት ባሰፈረዉ መሠረት ሃያን የ6,000 ሰዎችን ሕይወት ሲያጠፋ፤ ከ3,6 ሚሊዮን በላይ የሆኑትን ደግሞ ከመኖሪያ አካባቢያቸዉና ቤት ንብረታቸዉ አፈናቅሏል። ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ደግሞ ከአንድ ሺ በላይ የገቡበት አልታወቀም። በባህሩ ጠረፍ አቅራቢያ ትኖር የነበረችዉ ሊልያን ጎልፋን በንፋስና ጎርፍ የተንኮታኮተ ቤቷ የነበረበትን አካባቢ እያየች ስለተከሰተዉ የተፈጥሮ ቁጣ እንዲህ አለች፤

«የባህር ማዕበል እንዲህ ያለ ጥንካሬ ኖሮት መኖሪያ ቤቴን እንዲህ ድምጥማጡን ያጠፋል ብዬ በፍፁም አስቤ አላዉቅም። አሁን ምን ማድረግ እንደሚኖርብኝ ምንም አላዉቅም።»

እሷ ብቻ አይደለችም የሃያን ሰለባ፤ በርካቶች ከፈራረሰዉ የቤታቸዉ አካባቢ መሄድ ተስኗቸዉ የሆነዉ በማመንና ባለማመን ቅዠት ዉስጥ ሆነዉ አንዳንዶች ሰዓታት ሌሎቹ ቀናት አስቆጥረዋል።

የመሬት መናድን ያስከተለዉ 13 ጫማ ከፍታ የነበረዉ ወጀብ በሰዓት 315 ኪሎ ሜትር በሚምዘገዘግ አዉሎ ነፋስ ታግዞ የፊሊፒኖዎቹን የባህር ጠረፍ ግዛቶች በመጠራረግ፤ የአካባቢዉን መሠረተ ልማት እንዳልነበረ አዉድሟል። መንገዶች፤ የዉሃና የመጸዳጃ ስልቶችን እንዲሁም የቴሌኮሙኒኬሽን መስመሮችንም ከጥቅም ዉጭ አድርጓል። 30,6 ቢሊዮን ፔሶ ማለትም 711,62 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የእርሻ ምርትም አበላሽቷል። በሁኔታዉ የተደናገጠዉ መንግስት በወቅት ከአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ዉጭ ለሃያን ሰለባዎች ተገቢዉን ለማቅረብ አቅም እንደሌለዉ ሲያሳዉቅ የተመድ በበኩሉ ለተጎጂዎቹ የሚያስፈልግ ብዙ ነገር መኖሩን በመጠቆም የእርዳታ እጅ እንዲዘረጋ ጥሪ አቅርቧል።

Philippinen nach Taifun Haiyan 23.11.2013
ምስል picture-alliance/dpa

የፊሊፒንስ መንግስት የሀገር ዉስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማክስ ሮዛስ ሃያን ያደረሰዉን የጉዳት መጠን ለመግዘርዘር እንዳዳገታቸዉ እንዲህ ነበር የገለፁት፤

«የደረሰዉ ጥፋት አስከፊ ነዉ፤ ያን ለመግለፅ ትክክለኛዉ ቃል የለኝም። ኤሌክትሪክ ተቋርጧል፤ መብራት የለም፤ በጨለማ ተዉጦ ከብርዱም ሆነ ከነፋሱ ለመከላከል መጠጊያ ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ነዉ።»

ለአንድ ወር በቆየዉ የተፈጥሮ አደጋ 150 ሺህ ለሚሆኑት ተጎጂዎች ምግብ፣ መጠለያ፣ ህክምናና ሌሎች ተፈላጊ ርዳታዎችን ማቅረቡንዎርልድቪዥን ይገልፃል። የተመ የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ፅህፈት ቤት OCHA በምስራቅና ማዕከላዊ ፊሊፒንስ ሃያን አዉሎነፋስ ያጠፋዉን መልሶ ለማስተካከል ተጨማሪ ርዳታ ያስፈልገኛል ሲል ለለጋሾች ተማፅኖዉን አቅርቧል። በዚሁ ዓመት ከደረሱት የተፈጥሮ አደጋዎች በሁለተኛ ደረጃ የተመዘገበዉ በጥቅምት ወር ህንድን የመታዉ ፋይላን የተሰኘዉ ማዕበል ነዉ። በሰሜናዊ ምስራቅ ህንድ ከ13 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝብ ኑሮ ያናጋዉ ፋይላን ከ14ዓመታት ወዲህ ሕንድን የገረፈ ጠንካራ ወጀብ እንደሆነ ተመዝግቧል። እንዲያም ሆኖ ከ50 የማይበልጥ የሰዉ ህይወት ብቻ ማጥፋቱ ነዉ የተነገረዉ። በሰዓት 150 ኪሎ ሜትር የተወነጨፈዉ ንፋስና ከባዱ ዝናብ በተጠቀሰዉ አካባቢ ሊያደርስ ይችል የነበረዉን ጉዳት አስቀድሞ በመገመት በባህር ዳርቻ ለእልቂት ይዳረጉ የነበሩትን አንድ ሚሊዮን ኗሪዎች ከአካባቢዉ በማራቅ ጉዳቱ በንብረት ብቻ እንዲገታ በማድረጋቸዉ የህንድ መንግስትና ግብረሰናይ ድርጅቶች ተመስግነዋል።

ከማዕበል ጋ በተገናኘ ተጎጂዎችን በመርዳት የተሰማሩ ወገኖች ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የመዘገቡለት ሜክሲኮን መስከረም ላይ ያጥለቀለቁት ማንዌልና ኢንግሪድ የተሰኘ ስያሜ የተሰጣቸዉ ማዕበሎች ናቸዉ። ማዕበሎቹ በጣምራ ያስከተሉት ጎርፍና የመሩት መናድ ጉሬሮ በአንድ አካባቢ ብቻ ከ200 ሺህ ሰዎች በላይ ለጉዳት ዳርጓል። አካፑልኮ ላይ አምስት ጫማ ከፍታ የነበረዉ የጭቃ ደለል ተሽከርካሪዎችን ሲዉጥ፤ በርካታ ቤቶችን አፈራርሷል።

Mexiko Unwetter Hurrikan Acapulco
ምስል Reuters

በአራተኛ ደረጃ በ2013ዓ,ም ከደረሱ የተፈጥሮ አደጋዎች የተፈረጀዉ ሃያን አዉሎ ንፋስ ከመነሳቱ ሶስት ሳምንታት በፊት የፊሊፒንሷን ቪሳያሳ ማዕከላዊ ግዛት የመታዉ በሬሽተር መለኪያ 7,2 የደረሰዉ የመሬት መንቀጥቀጥ ነዉ። የመሬት ነዉጡ በወቅቱ የ222 ሰዎች ህይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሲሆን 350 ሺህ ሰዎችንም አፈናቅሏል። 73 ሺህ ሕንፃዎችን ለጉዳትና ዉድመት ዳርጓል።

ከዚህ ቀደም ብሎ ባለፈዉ ግንቦት ወር የአሜሪካኗ ኦክላሃማ ከተማ በሰዓት 200 ኪሎ ሜትር የመወርወር ፍጥነት በነበረዉ አዉሎ ነፋስ የተመታች ሲሆን፤ አደጋዉ በተሰናባቹ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ከደረሱት የከፉ የተፈጥሮ አደጋዎች አምስተኛ ደረጃን ይዟል። ይህ ኃያል አዉሎ ነፋስ ለ24 ሰዎች መሞት ምክንያት ሲሆን፤ ከ15 ሺህ በላይ ሰዎችንም ከመኖሪያቸዉ አፈናቅሏል። ከዚህም ሌላ ሁለት የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶችና በርካታ መኖሪያ ቤቶችን ከጥቅም ዉጭ አድጓል። ኦክላሃማ በአዉሎነፋስ ከመመታቷ አስቀድሞም ወደአስር የተገመቱ ጠንካራ አዉሎነፋሶች ሰሜናዊ ቴክሳስን መትተዉ ለስድስት ሰዎች ህልፈተ ህይወት ምክንያት ሆነዋል።

ከእነዚህ አምስት ዐበይት የተፈጥሮ አደጋዎች በተጨማሪም ሌሎችም በዚሁ ዓመት በተለያዩ አካባቢዎች ጉዳት አድርሰዋል። ለማስታወስም ባለፈዉ የካቲት ወር የሰሎሞን ደሴቶች በመሬት መንቀጥቀጥና በሱናሚ ማዕበል፤ ሚያዝያ ላይ ጣይና የቻይናዋ ሲቹዋን ግዛት በመሬት ነዉጥ፤ ግንቦት ላይ ደቡባዊ አፍሪቃ በድርቅ፤ ሰኔ ላይ ደግሞ ህንድ በጎርፍ፤ በመስከረም ወር የአሜሪካዋ ኮሎራዶ ግዛትም እንዲሁ በጎርፍ፤ ጥቅምት ላይ ደቡባዊ እስያ በዉሃ ተጥለቅልቀዋል። ስለፊሊፒንሱ ሃያን ማዕበል እና ስላደረሰዉ ጉዳት በሚነገርበት ወቅትም በቅርቡ ራስ ገዝ መሆኗን ያወጀችዉ የሶማሊያዋ ፑንትላንድ ከባህር በተነሳ ማዕበል ተመታለች። በዚህም ቢያንስ እስካሁን ወደ300 የሚደርሱ ሰዎች ህይወት ሳይጠፋ እንዳልቀረ መንግስት አመልክቷል። ግብረሰናይ ድርጅቶች እንደሚሉትም አንድ መቶ ሺህ የሚሆኑ ሰዎች አስቸኳይ ንፁህ የመጠጥ ዉሃና ምግብ እንደሚያስፈልጋቸዉ ሰሞኑን አመልክተዋል።

Taifun Haiyan Satellitenbild Philippinen 06.11.2013
ምስል Reuters/NOAA

የ2013ዓ,ም የሰሜን ንፍቀ ክበብ የክረምት ወራት በተለይ በማዕከላዊና ምዕራብ አዉሮጳ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ከዜሮ በታች ሳይወርድ በረዶም ሳያስከትል እስካሁን ቆይቷል። ጠንካራ ንፋስ የሚገፋዉ ዝናብ አልፎ አልፎ ቢታይም በተቃራኒዉ ከባድ ቅዝቃዜና በረዶዉ ወደመካከለኛዉ ምስራቅ የተሻገረ መስሏል። በዚህም ባለፉት ሳምንታት ኢራቅ፤ ግብፅ፤ ሶርያን ጨምሮ ሌሎች የመካከለኛዉ ምስራቅ ሃገራት ከዚህ ቀደም ያልተለመደ የበረዶ ክምር፤ ዝናብና ጎርፍ ከባድ ቅዝቃዜ አስከትሎባቸዋል። የረድኤት ሠራተኞች ከሶርያዉ የእርስ በርስ ጦርነት ሸሽተዉ ሊባኖስ የተጠለሉ 1,4 ሚሊዮን የሚሆኑ ሶርያዉያንን የሚገኙበት ሁኔታ ከቅዝቃዜዉ ጋ ተዳምሮ እንዳሰጋቸዉ ሲገልፁ ቆይተዋል። የአየር ንብረቱ መለዋወጥ ያሳሰባቸዉ ወገኖች የአየር ጠባይ ለዉጥ ከወዲሁ መከሰቱን ማመላከት መጀመሩን ቢናገሩም በሰሜን አሜሪካ የተለያዩ አካባቢዎች የተጠናከረዉ የበረዶ ዉሽንፍር አሁንም ወቅቱ አልተዛባም እንዲሉ ያበረታታቸዉ አልጠፉም። እንዲያም ሆኖ ግን በሃገራት መካከል የአየር ንብረት ለዉጥን የሚያጠናዉ ዓለም ዓቀፍ ኮሚቴ በምዕተዓመቱ ማለቂያ አዉሮጳ እጅግ ሞቃት ክፍለ ዓለም ትሆናለች የሚል ጥናቱን ሰሞኑን ይፋ አድርጓል።

ተሰናባቹ 2013ዓ,ም ከፍተኛ ጥፋት በሰዉና በንብረት ላይ ያስከተሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን ቢያስተናግድም፤ በጤናና በምርምሩ ረገድ በተለይ በርካቶች እንደዋዛ ህይወታቸዉን ለሚያጡበት የወባ በሽታ መፍትሄ ሊሆን የሚችል የመከላከያ ክትባት መገኘቱ የተበሰረበትም ዓመት ነዉ። ባለፈዉ ጥቅምት ወር ደቡብ አፍሪቃ ላይ ወባን አስመልክቶ በተካሄደዉ ጉባኤ የቀረቡ የጥናትና የምርምር ዉጤቶች የተገኘዉ ክትባት ትንሿ ትንኝ በየሰዓቱ በየቀኑና በየዓመቱ የምትቀጥፈዉን የህፃናትና አዋቂዎች ነፍስ ለማትረፍ አንድ ርምጃ የሚያስኬድ እንደሆነ አመላክተዋል። ግላስኮስሚዝ ክላይን የተሰኘዉ የእንግሊዝ የመድሃኒት ኩባንያ ከአዉሮጳ ኅብረት የመድሃኒቶች መቆጣጠሪያ ዘርፍ ፈቃድ ካገኘ ከአንድ ዓመት በኋላ ለ18 ወራት ሙከራ ያደረገበትንና በወባ የመያዝ እድል በግማሽ ይቀንሳል ያለዉን ክትባት ለገበያ ለማቅረብ ተዘጋጅቷል።

«ከሰላሳ ዓመታት ምርምር በኋላ የሰዉን ሰዉነት ከትንኟ አደገኛ ተህዋሲ የሚከላከል አንድ መድሃኒት ተቀምሟል። የብሪታንያዉ ግዙፍ የመድሃኒት ኩባንያ ግላስኮ ስሚዝ ክላይን የምርምር ዉጤቱ የሆነዉ ክትባት በጎርጎሪዮሳዊዉ 2015ዓ,ም በሁሉም ቦታ ለጥቅም ይዉላል ብሎ ተስፋ ያደርጋል።»

Tornado in US-Bundesland Oklahoma
ምስል Reuters

በእርግጥም ይህ ክትባት ከ5 እስከ 17 ወራት በሆናቸዉ ጨቅላ ሕፃናት ላይ ተሞክሮ ግማሽ ያህሉን ከወባ የመከላከል ብቃቱን አሳይቷል። የዓለም የጤና ድርጅትን አዎንታዊ ማበረታቻ ያገኘዉ ይህ የምርምር ዉጤት ግን በየመድሃኒት ቤቱ የሚሰራጭ ሳይሆን በተለያዩና በሽታዉን ለማጥፋት በሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አማካኝነት የሚከፋፈል እንደሚሆን ነዉ የተጠቆመዉ። ይህ ዜናም የሃኪም ቤት ክፍሎቻቸዉ በወባ በሽተኞች መጨናነቃቸዉን ያመለከቱት የቡርኪናፋሶ ባለስልጣናትን ተስፋ አጠናክሯል። የተገኘዉ ክትባት ምርምር አካል ባልደረባ የሆኑት ሃሊዶ ቲንቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የወባ በሽተኞች በአጎበርና በሌሎች ስልቶች ብቻ እየተረዱ እንደሚገኙ በማመልከትም ክትባቱ እንደልብ የሚገኝበትን ቀን እንደሚናፍቁ ገልጸዋል። በዚሁ ዓመት ነዉ በወባ ክፉኛ ከሚጠቃዉ እና በወባ ምክንያት ከሚጠፋዉ ህይወት አብዛኛዉን ከሚወስደዉ አፍሪቃ አህጉር፤ ደቡብ አፍሪቃ በሽታዉን ፈፅሜ ለማጥፋት ተቃርቤያለሁ የሚል መልካም ዜና ይፋ ያደረገችዉ። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር አሮን ማጾአሊዲ የወባ ትንኝን ለማጥፋት ዲዲቲን እየተጠቀመች መሆኗ የሚነገርላት ሀገራቸዉ ከወባ ነፃ የምትሆንበትን ጎዳና እያመቻቸች እንደምትገኝ ተናግረዋል። እንደእነሱ ግምትም እስከመጪዉ የጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2018 ይህ እዉን ይሆናል። በዓለም ደረጃ በየዓመቱ ወባ 660 ሺህ ህዝብ ትፈጃለች፤ ከዚህ መካከል 90 በመቶዉ አፍሪቃ ዉስጥ ሲሆን አብዛኞቹ ደግሞ ሕፃናት ናቸዉ። አፍሪቃ ዉስጥ ናይጀሪያ፤ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ እና፣ታንዛኒያ እና ሞዛምቢክ በወባ ክፉኛ ከሚጠቁት ሃገራት ዋነኞቹ ናቸዉ።

በዚሁ ዓመትም ነዉ የHIV ቫይረስ ስርጭት ካለፉት ዓመታት የመቀነስ አዝማሚያ ማሳየቱ የተነገረዉ። በAIDS የሚሞቱ ወገኖችም ቁጥር እንዲሁ ዝቅ ማለቱ ቢታይም አሁንም ራስን መግዛትና የባህሪ ለዉጥን አክሎ የተጠናከረ የመከላከል ርምጃ መቀጠል እንዳለበት ተገልጿል።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ