1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተፈጥሮ ደንና የቡና ትስስር

ረቡዕ፣ ጥር 20 2007

ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚበቅለዉ የጫካ ቡና ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ማደጉ በዓለም ቡና ጠጭዎች ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፉ ይነገርለታል።

https://p.dw.com/p/1ERGP
Japan Äthiopien Kaffee Projekt
ምስል James Jeffrey

የቡናዉ አምራቾች ከዓለም የቡና ገበያ የልፋታቸዉን ተገቢ ዋጋ እንዲያገኙ የሚደረገዉ ጥረት በቂ ባይባልም ተጠናክሮ ቢቀጥል የተሻለ ዉጤት ማየት እንደሚቻል በቅርቡ በጅማ ዞን የተፈጥሮ ደንን በመጠበቅ የቡናዉን ጥራት ከፍ ለማድረግ የሚካሄደዉን ጥረት የቃኘዉ የዶቼ ቬለ ተባባሪ ዘጋቢ ጀምስ ጄፈሪ በላከዉ ዘገባ ዘርዝሯል። ቡና ፈላጊዉ ዓለም በተለይ በተፈጥሮ መንገድ ለሚያድገዉ የጫካ ቡና የሰጠዉ ትኩረት የኢትዮጵያን ደን ከዉድመት ይታደገዉ ይሆን?

በዓለማችን የጫካ ወይም ወፍ ዘራሽ ቡናን የሚያመርቱ ሃገራት ሶስት ብቻ ናቸዉ። ኢትዮጵያ፣ ብራዚል እና የመን። ከእነዚህ ሃገራት አንዷ ደግሞ በሀገር በቀል የተፈጥሮ ደን ዉስጥ ይህን ቡናዋን በማብቀል ትታወቃለች። ይህችዉም ቡናን በዉድ ዋጋ ለጠጪዎች ማቅረቡን የሚያዉቅበት ዓለም በኩራት ጠቀም ባለ ገንዘብ የሚቸበችበዉ አረቢካ የተሰኘዉ ቡና መገኛ ምድር ኢትዮጵያ ናት። ይሄ ሁሉ ዝናና ታሪክ ግን ተፈላጊዉን የጫካ ቡና ለሚያመርቱት የጅማዉ በለጠ ገራ የተፈጥሮ ደን የኢትዮጵያ ቡና አምራቾች የእዉቅናዉን ያህል ብዙም ጥቅም እንዳላስገኘላቸዉ አካባቢዉን ጎብኝቶ የሚመለከታቸዉን ያነጋገረዉ ጄምስ ጄፈሪ ይገልጻል። ለዚህም እሱ እንደሚለዉ የጥራት ቁጥጥር ዋነኛዉ ጉዳይ ነዉ። ካለፈዉ ሐምሌ ወር አንስቶ ለጥራቱ ማረጋገጫ የተሰጠዉ የጫካ ቡና ማምረትና ማሻሻጫ ፕሮጀክት የቡናዉን የጥራት ደረጃ ብቻ ሳይሆን የአምራቾቹን ገቢና የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል እንዲሁም 3,296 ሄክታር የተፈጥሮ የደን ይዞታ ለማስጠበቅ እየተንቀሳቀሰ ነዉ። እንደጄፈሪ የኢትዮጵያ ደን ተመናምኗል። 95 በመቶ የሚሆነዉ የተፈጥሮ ደን በእርሻ ሥራ ማስፋፊያ፣ በሰዎች መኖሪያና በሰፈራ እንቅስቃሴዎች እንዳልነበር ሆኗል። የደን መጨፍጨፍና ምንጠራዉ ተግባርም በፍጥነት እያደገ ከሚሄደዉ የሕዝብ ቁጥር ጋ ተዳምሮ አብዛኛዉ ቤተሰብ ለማገዶም ሆነ በተለያዩ መንገዶች ኑሮዉን ለመደገፍ ደኑን ከመመንጠር ሌላ በምንም አማራጭ እንደሌለዉ ያመለክታል። አብዛኞቹ ገበሬዎችም ከዚህ የተለየ አማራጭ እንደሌላቸዉ ያስረዳል። በአሁኑ ወቅት ካለዉ የደን ሀብት 70 በመቶዉ የሚገኘዉ በኦሮሚያ መስተዳድና አካባቢዉ ነዉ። ጄፍሪ ያነጋገራቸዉ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ተቋም አማካሪ እንደሚሉት አማራጭ አጥቶ እንጂ ሕብረተሰቡ የደን ሀብቱን በመንከባከብ ሊያገኝ የሚችለዉን ጥቅም አልዘነጋዉም። ቡናዉ በዓለም ገበያ እዉቅና አግኝቶለት ኑሮዉን የሚያሻሽልበት አማራጭ ሲቀርብለት መተባበሩም ይህንኑ አመላካች ነዉ። የደን ሀብቱ ሳይጎዳ ወፍ ዘራሹን ቡና በተፈጥሯዊ መንገድ ለፍሬ የሚያበቃለትን ምክር በመቀበሉም ተጠቃሚ ለመሆን የሚችልባቸዉ ስልቶች እየተቀየሱ መሆኑን የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አራርሳ ረጋሳ ያብራራሉ፤

Japan Äthiopien Kaffee Projekt
የቡና ጥራት ቅምሻዉምስል James Jeffrey
Japan Äthiopien Kaffee Projekt
ተወዳጁን ቡና ያቀፈዉ ደንምስል James Jeffrey

ዝናብ ጠገብ ደን ዉስጥ ቡናዉ ማደጉን የሚያረጋግጥ ሰርተፊኬት ነዉ የተጠቀሰዉ አካባቢ ያገኘዉ። ይህም ገበሬዎቹ ለዓለም ገበያ ለሚያቀርቡት ቡና ጥራት ትልቅ ዋስትና ነዉ። ዑሺማ ካፌ የተሰኘዉ የጃፓን የቡና አስመጪ ኩባንያ ከዚህ ስፍራ የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ወፍ ዘራሽ ቡና ለሀገሩ ቡና ጠጪዎች ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ሃገራት ጥራቱን በጠበቀ የተፈጥሮ ደን ዉስጥ እንደሚበቅል እያስተዋወቀ ነዉ። እንደዘገባዉ ጃፓኖች በፈጣን ባቡሮቻቸዉ ለሚጓዙ መንገደኞች ይህንን ከጅማ ዞን የተፈጥሮ ደን ዉስጥ የበቀለ ቡና ማቅረብ ከጀመሩ አራት ወራት ተቆጥረዋል። አነስተኛ ቡና አምራቾቹ የጥራት ደረጃዉን ጠብቀዉ ዓለም ዓቀፉን የምርጥ ቡና ምልክት ተቀዳጅተዉ ገበያዉን እንዲቆጣጠሩት ደግሞ የዉጭም ሆነ የሀገር ዉስጥ ድርጅቶችና መንግሥታትን ትኩረትና የተቀናጀ ትብብር እንደሚያስፈልጋቸዉም ያስገነዝባል። በዓለም ገበያ እጅግ ተፈላጊ የሆነዉ ወፍ ዘራሹ የጫካ ቡና ህልዉና እንዲቀጥልም የተፈጥሮ ደኑን መጠበቁ አማራጭ እንደሌለዉ ነዉ ግልፅ የሆነዉ። ይህንነዉ አቶ አራርሶ የሚያስረዱት፤

Japan Äthiopien Kaffee Projekt
የቡና አምራቾቹምስል James Jeffrey

ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉና ጄምስ ጄፍሬ ያነጋገራቸዉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከመነሻዉ በርካታ ገበሬዎች ለቡናቸዉ ጥራት ማረጋገጫ የማግኘቱን ርምጃ ብዙም ትኩረት አልሰጡትም ነበር። ሆኖም ከሽያጩ ያገኙት ከበፊቱ የተሻለ ገቢ ትርጉም ሳይኖረዉ የቀረ አይመስም። ምንም እንኳን አንዳንዶቹ አሁንም ያገኙት ገቢ የእነሱን ወገብ በጣሽ ልፋትና የፈሰሰ ላብ እንደማያካክስ በግልፅ ቢናገሩም። ሌላዉ አስተያየት ሰጪ በፕሮጀክቱ ተሳታፊ ከሆኑት ዋናዉ የጃፓን የቡና አስመጪ ኩባንያ አማካሪ እንደሚሉት ደግሞ እየተጀመረዉ መልካምነቱ ባያነጋግርም ዘላቂነቱን ለማረጋገጥም ሆነ ዋጋዉን ከፍ ለማድረግ ግን ትርጉም ያለዉ ጥረት ይጠይቃል። በዚህ መልኩ እንቅስቃሴዉ ተጠናክሮ የኢትዮጵያ የጫካ ቡና ልዩ ሆኖ በዓለም ገበያ ሲቀርብም ደንን ከመራቆት መታደግ መቻሉም ትልቅ ግምት ይሰጠዋል።

አቶ አራርሳም እንደገለፁት አሳታፊዉ የደን ይዞታ በእርግጥም ለጅማ ዞኑ በለጠ ገራ ደን የቡና አምራች ገበሬዎቹን ምርት ወደጃፓን የቡና ገበያ ያሻገረ ስልት ነዉ። ይህ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደመምታት የሚቆጠረዉ የተፈጥሮ ደኑን እየጠበቁ ወፍ ዘራሹን ቡና የማምረቱ ስልት አጀማመሩ በአንድ አካባቢ ይሁን እንጂ ወደሌላዉም የኦሮሚያ የደን አካባቢ እየተዳረሰ እንደሆነም ገልጸዋል።

Japan Äthiopien Kaffee Projekt
ምስል James Jeffrey

ለቡናዉ ተፈጥሯዊ አስተዳደግ አስፈላጊ የሆነዉን የደን ሀብት የቡናዉ ገበሬዎች የሚንከባከቡት የኦሮሚያ ደንና ዱር አራዊት ጥበቃ ተቋሙና ኅብረተሰቡ በጋራ በአሳታፊዉ የደን ክብካቤ ስልት እንደመሆኑ ኅብረተሰቡ ለግል ፍጆታዉ የሚሆነዉን ዛፍ እየተከለ እንዲጠቀም አሠራሩ በመግባባት መመቻቸቱን አራርሳ ያስረዳሉ፤

የደኑን ህልዉና ለማስቀጠል የኅብረተሰቡ የአኗኗር ሁኔታ መለወጥ እንደሚኖርበት ያመላከቱ ወገኖች አልጠፉም። ተመሳሳይ ሃሳብ የሰነዘሩት የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አራርሳ ረጋሳም የተፈጥሮ ደኑ እንዲጠበቅ የኅብረተሰቡ ኑሮ መለወጥ ወሳኝ እንደሆነ ነዉ አፅንኦት የሰጡት። ማብራሪያ በመስጠት የተባበሩንን የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አራርሳ ረጋሳን ከልብ እናመሰግናለን።

James Jeffrey /ጀምስ ጄፈሪ /ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ