1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቱርክ ምርጫ

ዓርብ፣ ሰኔ 3 2003

የፊታችን ዕሁድ የሚካሄደው የቱርክ ምርጫ ለሀገሪቱ ቀጣይ ጉዞ ወሳኝ እንደሆነ እየተነገረ ነው። ይህም ከሆነ ፓርቲው ህገመንግስቱ ላይ ለውጥ የማድረግ አቅም ይኖረዋል ማለት ነው።

https://p.dw.com/p/RSx6
ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርዶሀንምስል AP

እስላማዊ መሰረት ላይ የቆመው ገዢው ወግአጥባቂ ፓርቲ ኤኬፒ ለሶስተኛ ዙር በቀላሉ ሊያሸንፍ ይችላል የሚል ግምት ከወዲሁ ተሰጥቷል። የህዝብ አስተያየት መለኪያዎች የሚያሳዩትም ገዢው ፓርቲ በፍጹም አብላጫ ድምጽ እንደሚያሸንፍ ነው። የፓርቲው መሪ ሪቼፕ ጣይብ ኤርዶሀን አዲስ ህገመንግስትና ፕሬዝዳንታዊ መዋቅር እንደሚኖር ቃል ገብተዋል። ይሁንና ፓርቲው እንደተገመተው በሰፊ አብላጫ ድምጽ ካሸነፈ፤ ቱርክ ወደ አንድ መሪና አንድ ፓርቲ ስርዓት ታመራለች የሚል ትችት እየተሰነዘረ ነው። የዶቸቬሌ የቱርክ ክፍል ባልደረባ አይሃን ሲምሴክ ያጠናቀረውን መሳይ መኮንን ያቀርበዋል።

ኢዳላይት ቪ ካሊኪንማ ፓርቲዚ በምህጻረ ቃል አጠራሩ ኤኬፒ በእርግጥ የዕሁዱን ምርጫ ስለማሸነፉ የሚጠራጠሩት በጣም ጥቂቶች ናቸው። የህዝብ አስተያየት መለኪያዎች እንደሚያሳዩት ኤኬፒ ከ42 እስከ 50 በመቶ ድጋፍ አለው። ይህም በፍጹም አብላጫ ውጤት ድል እንደሚያደርግ ያመላክታል ተብሏል። ተቺዎች ይህ ሁኔታ ያማራቸው አይመስሉም። ውጤቱ እንደተገመተው ከሆነ የፓርቲው መሪ ሪቼፕ ጣይብ ኤርዶሀን ስልጣናቸውን ጠበቅ የማድረግ፤ ብሎም የአንድ ፓርቲ ስርዓት የመዘርጋት እድላቸው የሰፋ ይሆናል ተብሎ ተሰግቷል። ይህም የነጻነትንና የዲሞክራሲያዊ መብቶችን ወደመጣስ ሊወስድ ፤ በተቃዋሚዎችና በኩርድ ቡድኖች ላይ ቁንጥጫውን ሊያባብስ የሚችል እንደሚሆን ነው ታዛቢዎች የሚገልጹት። ኢዳላይት ቪ ካሊኪንማ ፓርቲዚ ኤኬፒ ግን ትችቶችን ሁሉ መሰረተ ቢስ ይላቸዋል። አዲስ ህገመንግስት ለማርቀቅ ቃል የገባ ፓርቲ ይህ ዓይነቱ ትችት ሊቀርበበት አይገባም ነው የሚሉት የፓርቲው መሪዎች። በምክርቤት የገዢው ፓርቲ ኤኬፒ ምክትል ዕጩ ቮልካን ቦዝኪር እንደሚሉት ቱርክ ወደ አንድ ፓርቲ ስርዓት እያመራች ነው ማለት ተራ አስተያየት ነው።

«በወደፊት የቱርክ ዲሞክራሲያዊ ሂደት ላይ ያለው ፍርሃት መሰረተ ቢስ ነው። ኤኬፒ ብቸኛ ፓርቲ ሆኖ ላለፉት 8 ዓመታት ተኩል በመንግስት ስልጣን ላይ ቆይቷል። ቱርክ ወደ ተሻለ ዲሞክራሲ፤ ነጻ አስተሳሰብ፤ ነጻነትና ነጻ ተቋማት በጣም የቀረበች ሆናለች። በኤኬፒ አመራር ቱርክ በታሪኳ ጠንካራ አቅም ላይ ትገኛለች። የኢኮኖሚያዊ፤ ዲሞክራሲያዊ እና ፖለቲካዊ መረጋጋትዋ ፤ ከጎረቤቶቿ ጋር ካላት መልካም ግንኙነት ጋር ተዳምሮ ቱርክ በዓለም ፖለቲካ ላይ የመሪነት ሚና የምትጫወት ሀገር ሆናለች።»

ኤኬፒ ቱርክን መምራት ከጀመረበት እ.ኤ.አ ከ2002 ወዲህ ሀገሪቱ ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ግንባር ቀደሙን ስፍራ መያዝ ችላለች። በዓለም ፖለቲካ ላይ ያላትም ተሰሚነት በከፍተኛ ደረጃ ቸምሯል። ቱርክ የአከባቢው ወሳኝ ሃይል መሆኗ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ ዕውቅና እየተሰጣት ሲመጣ በአንጻሩ በነጻነትና ዲሞክራሲ መብቶች በኩል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ስሟ በበጎ የሚነሳ አልሆነም። ፍሪደም ሀውስ በቅርርቡ ባወጣው ሪፖርት ቱርክን በከፊል ነጻ ሀገር ሲል ነው ያስቀመጣት። በሌላ በኩል የአውሮፓ የደህንነትና ትብብር ድርጅት ቱርክ 57 ጋዜጠኞችን ማሰሯን በመግለጽ ተችቷታል። በኢንተርኔት ላይ በምታደርገው ቁጥጥርና መንግስቷ ለነጻ ሀሳቦች መስተናገድ ትዕግስት ማጣቱ እያስወቀሳት ይገኛል። የቱርክ ጋዜጠኞች ማህበር ቃል አቀባይ ዶሀን ቲሊሽ እንደሚለው መንግስት በጋዜጠኞች ላይ ጫናውን ይበልጥ አጠናክሯል።

መሳይ መኮንን

ነጋሽ መሀመድ

ተክሌ የኋላ