1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቱርክ እና የሩስያ ዉዝግብ

Merga Yonas Bulaሐሙስ፣ ኅዳር 16 2008

ቱርክ ከትናንት በስቲያ አንድ የሩስያ የጦር ጄት ከጣለች ወዲህ በሁለቱ አገሮች መሃል ያለዉ ግኑኝነት እየተካረረ መጥቶዋል። የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የቱርክ መንግሥት ሆን ብሎ ሞስኮና አንካራ መሃል ያለዉን ግንኙነት ለማበላሸት ጥረት እያደረገ ነዉ በሚል ቱርክን ወቅሰዋል።

https://p.dw.com/p/1HDB4
Putin bei Erdogan 01.12.2014
ምስል Reuters/U. Bektas

[No title]

ለድርጊቱም ቱርክ ይቅርታ አለመጠየቋ ግራ የሚያጋባ ነዉ ቢሉም የቱርክ ፕሬዝደንት ራሲብ ጣሂብ ኤርዶኻን በፋንታቸዉ ሀገራቸዉ የሩሲያ አዉሮፕላንን መምታቷን ቢያምኑም ይቅርታ እንደማይጠይቁ ዛሬ የመንግሥታቸዉን አቋም ገልፀዋል።

የቱርክ መንግስት ይህን የጦር ጄት ለመምታት የተገደደዉ 10 ግዜ ለጄት አብራሪው ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ መሆኑንም በመግለፅም የሩስያ የጦር ጄት የአየር ክልሌን በመጣሱ ሩስያ ይቅርታ መጠየቅ እንደሚኖርባት ነዉ ያመለከተዉ።


የሩስዉ የዉጭ ጉዳይ ሚንስቴር የጦር ጄቱ መመታቱ ተደርጎ የማይታወቂ ክስተት መሆኑን በመጥቀሰ ርምጃዉ ከቱርክ ጋር ባለዉ ግንኙነት ላይ በተለያዩ መስኮች ተፅኖ እያሳረፈ መሆኑን አስገንዝቦዋል። በመቀጠልም የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን፣ በእንግሊዝኛ ምህጻሩ፣ ኔቶ በዚህ ጉዳይ ለይ አቋም ሊወስድ አለመቻሉ እና በአከባቢዉ እየተከሰቱ ያሉትን ቀዉሶች ለማብቃት በተቋቋመዉ የጦር ጥምረት ዉስጥ ያለዉን አለመቀናጀት እንደሚያሳይ ገልጾዋል። የሩስያ መንግስት ኔቶ የቱርክን እርምጃ እንዲያወግዝ ይጠብቃል። እንደ ሩስያ ዉጭ ጉዳይ ሚንስትር፣ ሴርጌ ላቭሮቭ አባባል የቱርክ ድርጊት ድንገተኛ አልነበረም፥

«ርምጃዉ ታቅዶ የተሰራ ጠብ ጫሪነት ይመስላል። ለዚህም ቀደም ሲል የተዘጋጁት በፎቶ የተደገፉት ዘገባዎች አሳማኝ ማስረጃዎች ናቸዉ። ይህ ቀደም ሲል የታቀደ መሆኑን የሚያሳዩ ሌሎች ማስረጃዎችም አሉ። እኛ ከቱርክ ጋር ጦርነት ዉስጥ ለመግባት እቅድ የለንም። ከቱርክ ሕዝብ ጋር ያለን ግንኙነት አሁንም አልተቀየረም። ጥያቄያችን ለቱርክ መንግሥት ነዉ።»


የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን አባል የሆነችዉ፣ ቱርክ፣ መንግስቷ የሩስሽያ ጦር ጄት ላይ የወሰደዉን እርምጃ ተከትሎ በሁለቱም ሀገራት መካከል ያለዉን ግኑኝነት እንዳይሻክረው የተለያዩ አገራት መሪዎች አስጠነቅቀዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ጉዳዩን አሰመልክቶ ስናገሩ፣

Russland Kampfjet Suchoi Su-24
ምስል Reuters/S. Zhumatov

«ቱርክ፣ እንደማንኛዉም አገር፣ የራሱን አገር ድንበር እና የአየር ክልሉን መብት የማስከበር መብት አላት። እኔ የማምነዉ፣ ባሁኑ ሰዓት በጣም አስፈላጊው ነገር ሩስ እና ቱርክ በዚህ ጉዳይ ላይ መነጋገራቸዉን እርግጠኛ መሆን አለብን፣ ሁለቱ ሃገራት በእርግጠኝነት የተፈጠረዉን ማረጋገጥ እና ይህ እየሻከረ የመጣው ግኑኝነት ይበልጡን እንዳይባባስ እርምጃ መዉሰድ አለባቸዉ።»

እንዲያም ሆኖ ዛሬም የሩሲያ የጦር ጀቶች በቱርክ ድንበር አካባቢ ድብደባ ማካሄዳቸዉን የአካባቢዉ ኗሪዎችን በእማኝነት የጠቀሰዉ ሮይተርስ ዘግቧል። በሁለቱ ጎረቤት ሃገራት መካከል የተፈጠረዉ መወዛገብ እንዲረግብ ግፊት ቢደረግም ሩሲያ ቱርክ የሚገኙ ዜጎቿ ወደሀገራቸዉ እንዲመለሱ በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት ጥሪ አስተላልፋለች።

መርጋ ዮናስ

አርያም ተክሌ