1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቱርክ እና የጀርመን ውዝግብ  

ማክሰኞ፣ የካቲት 28 2009

የቱርክ ፖሊተከኞች ጀርመን ውስጥ ሊያካሂዱ ካቀዷቸው የድጋፍ ማሰባሰቢያ ዘመቻዎች አብዛኛዎቹ መሰረዛቸው በቱርክ እና በጀርመን መካከል የተፈጠረውን ውጥረት አባብሷል ። ቱርክ በአምባገነንትዋ ከገፋችና እና ጀርመንንም የአሸባሪዎች ዋሻ ማለትዋን ከቀጠለች ውጥረቱ እየተባባሰ መሄዱ አይቀርም ። ሆኖም ውዝግቡን ለመቆጣጠር መሞከራቸው አይቀርም ።

https://p.dw.com/p/2YkSe
Türkei Erdogan wirft Deutschland «Nazi-Praktiken» vor
ምስል Reuters/M. Sezer

የቱርክ እና የጀርመን ውዝግብ  

ቱርክ እና ጀርመን ተራርቀው ቢገኙም በብዙ መስኮች ተባብረው የሚሰሩ አንዳቸው ለሌላኛው አስፈላጊ የሆኑ ሀገራት ናቸው ።  የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ አባል የሆኑት ሁለቱ ሀገራት ፣ የንግድ ሸሪኮች ናቸው ። ጀርመን የበርካታ ቱርኮች መኖሪያ ናት ። ስደተኞች ወደ አውሮጳ እንዳይሻገሩ ለማገድ ቱርክ ከአውሮጳ ህብረት ጋር የተስማማችው ውል የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ካጠናከሩት የቅርብ ጊዜዎቹ እርምጃዎች አንዱ ነው ። ይሁን እና  በቱርክ ከተካሄደው ካለፈው ዓመቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ የቱርክ መንግሥት በዜጎቹ ላይ የወሰዳቸው እርምጃዎች በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ላይ ጥላ እንዳጠላ ነው  ።ይልቁንም ውጥረቱ እንዲከር አድርጓል። የአንካራ መንግሥት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ጠንሳሽ ተባባሪ እና ደጋፊ ያላቸውን በርካታ ዜጎች ማሰሩን ጀርመን ተቃውማለች ። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰበብ በቱርክ ጋዜጠኞች ፣ ምሁራን እና በርካታ የመንግሥት ሠራተኞች መታሰራቸው መንገላታታቸው ተቀባይነት እንደሌለው  ስትወተውት ብትከርምም ቱርክ የጀርመን ዜግነት ያለውን ቱርካዊ ጋዜጠኛ ከሦስት ሳምንት በፊት በአሸባሪነት እና በሰላይነት ወንጅላ ማሰሯ ውዝግቡን አባብሷል ። ይህን ተከትሎም በመጪው ሚያዚያ በቱርክ ለሚካሄደው የህገ መንግሥት ማሻሻያ ህዝበ ውሳኔ የቱርክ ፖለቲከኞች ጀርመን ውስጥ ሊያካሄዱ ካቀዷቸው የድጋፍ ማሰባሰቢያ ዘመቻዎች አብዛኛዎቹ መሰረዛቸው የቱርክ ባለስልጣናትን በእጅጉ አስቆጥቷል ። ቁጣው ጠንካራ ዘለፋዎችንም እስከመሰንዘር አድርሷል ። 
« ጀርመኖች አዳምጡኝ ! ምግባራችሁ ፣ ከዴሞክራሲ ጋር ምንም  የሚያገኛኘው ነገር የለም ። አሁን የምታደርጉት ካለፉት የናዚ ልምዶች የሚለዩ አይደሉም ። »
የቱርክ ፕሬዝዳንት ታይፕ ሬቼፕ ኤርዶሀን እርምጃውን ኢዴሞክራሲያዊ እና ከናዚ ጀርመን ተግባር ጋር የሚመሳሰል ሲሉ ከትናንት በስተያ ያወገዙበት ንግግር ነበር ። የኤርዶሀንን ትችት ጀርመን ውድቅ አድርጋለች ። የጀርመን መንግሥት ቃል አቀባይ ትችቱን ሽቴፋን ዛይበርት አለቦታው የተሰነዘረ እና እውነታውን የሚያዛባ ሲሉ አጣጥለውታል ።
« በዴሞክራሲያዊት ጀርመን እና በናዚ ዘመን ፖሊሲዎች መካከል የሚደረግ ማንኛውንም ንፅፅር አጥብቀን እንቃወማለን።  እንደነዚህ ዓይነቶቹ ንፅፅሮች ሁሌም የማይረቡ እና አለቦታቸው የሚሰነዘሩ ናቸው፣ ምክንያቱም፣ በስብዕና አንፃር የተፈጸሙ ወንጀሎችን አሳንሶ ወደማየቱ ያመራሉ።» 
ኤርዶሀን ጀርመንን የዘለፉት የቱርክ የኤኮኖሚ ሚኒስትር በኮሎኝዋ ፖርትዝ ቀበሌ እና ከሎኝ አቅራቢያ በሚገኘው ፍሬሸን በተባለው ከተማ እንዲሁም የፍትህ ሚኒስትሩ ጋግገናዉ በተባለው ከተማው በመጪው ሚያዚያ ለሚካሄደው የህገ መንግሥት ማሻሻያ ህዝበ ውሳኔ ድጋፍ ለማሰባሰብ ሊያካሂዱ ያቀዷቸው መርሃ ግብሮች ከተሰረዙ በኋላ ነው ። ኤርዶሀን የበርሊንን እርምጃ ከናዚ ተግባር ጋር የሚመሳሰል እስከ ማለት መድረሳቸው ማነጋገሩ ቀጥሏል ። ኢስታንቡል የሚገኘው የዶቼቬለ ጋዜጠኛ ዶርያን ጆንስ ኤርዶሀን ይህን ለማለት የደፈሩት በሁለት ይጠቅሙኛል ብለው ባሰቧቸው  ምክንያቶች ነው ይላል ።
«አንደኛው በመጪው ሚያዚያ ጀርመን ውስጥ የሚገኙ 1.4 ሚሊዮን ድምፅ መስጠት የሚችሉ ቱርኮች የፕሬዝዳንቱን ሥልጣን ለማጠናከር ታስቦ በተዘጋጀው የህገ መንግሥት ማሻሻያ ላይ በሚሰጠው ህዝበ ውሳኔ ወሳኝ ናቸው ተብለው ነው የሚታዩት ።  ምክንያቱም ህዝበ ውሳኔውን የሚቃወሙ እና የሚደግፉት ቁጥር ተቀራራቢ ነው ተብሎ ነው የሚገመተው ። ሌላው ምክንያታቸው ደግሞ ከጀርመን ጋር መጋጨቱ በቱርክም ሆነ ጀርመን ውስጥ የወግ አጥባቂ እና ብሔረተኛ ድምፅ ሰጭዎችን ድጋፍ ሊያስገኝላቸው ይችላል ። ራሳቸውን እንደተበደለ እና ዒላማ እንደተደረገ ሰው አድርገው በማቅረብ ደጋፊዎቻቸው በሙሉ ድምጻቸውን እንደሚሰጧቸው እርግጠኛ ያልሆኑበትን ድጋፍ ለማጠናከር የተጠቀሙበት ስልት ነው ።»  
የጀርመን መንግሥት እርምጃ ተቃውሞ የገጠመው ከቱርክ መንግሥት በኩል ብቻ ሳይሆን ከሀገሪቱ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም ጭምር መሆኑን ጋዜጠኛ ዶርያን ጆንስ ገልጿል ። እርሱ  እንደሚለው በርካታ ቱርኮች ጀርመን በህዝበ ውሳኔው ላይ ገለልተኛ አቋም እንድትይዝ ነው የሚጠይቁት ።
«ታዋቂ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ሳይቀሩ የጀርመንን አቋም አውግዘዋል ። ይህን በመሰለ አስፈላጊ ጉዳይ ላይ ሁሉም ሰው መናገር የሚችልበት መድረክ ሊሰጠው ይገባል ባይ ናቸው ። ይህ በአጠቃላይ ቱርክ ውስጥ ያለ ስሜት ነው ። የፕሬዝዳንቱ ተቃዋሚዎች ስጋት መከልከሉ ፕሬዝዳንቱን ይጠቅማል የሚል ነው ። ጀርመኖች በዚህ ህዝበ ውሳኔ ጣልቃ መግባት የለባቸውም ፤ገለልተኛ አቋም መያዝ ነው ያለባቸው ነው የሚሉት ።» 
ኤርዶሀንን ጨምሮ የቱርክ ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም ጀርመን ውስጥ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ዘመቻዎች ሲያካሂዱ ነበር ።ይህ ልምድ ባለበት በጀርመን ቀደም ብለው የተያዙት እነዚህ መርሃ ግብሮች አሁን የመሰረዛቸው ምክንያቱ ምን ይሆን። የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል ይህ ከጀርመን እሴቶች ጋር የተያያዘ ነው ይላል ። 
በርሊን እና አንካራ የተወዛገቡት አሁን ብቻ አይደለም ። ከቱርክ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በፊትም ጀርመን ፣ቱርኮችን ያስቆጡ እና ቂም የያዙባቸውን  እርምጃዎችም ወስዳለች ።የጀርመን ፓርላማ የኦቶማን ቱርክ ከአንድ መቶ ዓመት በፊት በአርመኖች ላይ ያካሄደው ግድያ የዘር ማጥፋት ነው ሲል ውሳኔ ማሳለፉ ቱርክን ያስቆጣ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው ። ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ በርሊን፣ ጀርመን የሚገኙ የቱርክ ዳይስፖራዎችን  በመሰለል በተጠረጠሩ የቱርክ ኢማሞች እና መስጊዶች ላይ እርምጃዎችን ወስዳለች ። ቱርክም በቅርቡ በስለላ እና በሽብር ወንጀል የከሰሰችውን ቱርካዊ ጀርመናዊውን ጋዜጠኛ አስራለች ። እነዚህ የአፀፋ እርምጃዎች ቢወሰዱም ሁለቱም ወገኖች ውዝግቡን ለመቆጣጠር ሲጥሩ ቆይተዋል ይላል ጋዜጠኛ ዶርያን  ።
«ውጥረቱ የነበረ ቢሆንም ጉዳዩ እንዳይወጣ ተደርጓል ። ይህ የሆነበት ምክንያትም ሁለቱም ወገኖች ግንኙነታቸው እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘባቸው ተቆጣጥረውት ነበር ። ጀርመን ለቱርክ እጅግ አስፈላጊ የሆነች የንግድ አጋር እንደመሆንዋ ቱርክም ለጀርመን እጅግ ጠቃሚ የኤኮኖሚ አጋር ናት ።ከቱርክ ጋር ውል አላቸው ። ቱርክ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚፈልጉ ስደተኞችን ይዛ የምታቆይ የአውሮጳ በር ጠባቂ ሆናለች ። ከዚህ በተጨማሪ ከ3 ሚሊዮን በላይ ቱርኮች ጀርመን ውስጥ ስለሚኖሩ የሁለቱ ሀገራት ግንኑነት  በሁለቱም ወገኖች በኩል ጠቃሚ ተደርጎ ነው የሚታየው ። ይህ ነው ውዝግቡ እስካሁን ባለበት እንዲቆይ ያደረገው ። ቱርክ ህዝበ ውሳኔ  ፣ ጀርመን ደግሞ አገር አቀፍ ምርጫ ይጠብቃታል ። ምንም እንኳን ሁለቱም አሁን የተፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ለማርገብ ቢሞክሩም በሚቀጥሉት ሳምንታት ውዝግቡ ተባብሶ ሊቀጥል ይችላል ። »
በዶርያን እምነት ቱርክ በአምባገነንትዋ ከገፋችና እና ጀርመንንም የአሸባሪዎች ዋሻ ማለትዋን ከቀጠለች ውጥረቱ እየተባባሰ መሄዱ አይቀርም ።  ያም ሆኖ ግን ሁለቱም ተጠቃሚ ለሚሆኑባቸው ግንኙነታቸው ሲሉ ውዝግቡን ለመቆጣጠር መሞከራቸው አይቀርም  ። በይልማ አስተያየት ደግሞ  የውጥረቱ መባባስ ብዙ ስጋቶችን አሳድሯል ። ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ደግሞ ሁለቱም ወገኖች በጀመሯቸው ጥረቶች ቀጥለዋል ። 

Deutschland Demo für die Freilassung von Welt-Korrespondent Deniz Yücel
ምስል Reuters/A. Schmidt
Deutschland Steffen Seibert Bundespressekonferenz
ምስል picture-alliance/dpa/P. Zinken

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ