1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቱኒዚያ ምርጫ ዉጤት

ረቡዕ፣ ጥቅምት 15 2004

«በሕዝባዊዉ አብዮት ቱኒዞች የመጀመሪያዎቹ ነበሩ።በምርጫዉም የመጀመሪያዎቹ ናቸዉ።ሒደቱ በአብዛኛዉ ሙሉ በሙሉ አዎንታዊ ነበር።በየሐገራቸዉ ዲሞክራሲና ነፃነት ለማስረፅ የሚሹ ለሌሎቹ የአረብ ሐገራት ሕዝቦች ይሕንን እንደምሳሌ ቢወስዱት ይጠቅማቸዋል ብዬ አምናለሁ።ገቢራዊ ሊሆን እንደሚችል አሁን በትክክል ታይቷል።»

https://p.dw.com/p/RtBF
የድምፅ ቆጠራምስል AP/dapd

ባለፈዉ ዕሁድ ቱኒዚያ ዉስጥ የተደረገዉ የሕገ-መንግሥት አርቃቂ ምክር ቤት ምርጫ የመጀመሪያ ደረጃ ዉጤት እየተነገረ ነዉ።አጠቃላዩ ዉጤት ግን ገና በይፋ አልተገለጠም።ከየድምፅ መስጪያ ጣቢዎች እስከ ዛሬ አመሻሽ ድረስ በተነገረዉ ዉጤት መሠረት አነሕዳሕ የተሰኘዉ እስላማዊዉ ፓርቲ አብላጫዉን ድምፅ ማግኘቱ አላጠራጠረም።ዉጤቱ አንዳድ የቱኒዚያ ፖለቲከኞችን ቅር ቢያሰኝም የአዉሮጳ ሕብረትን ጨምሮ የምርጫዉን ሒደት የታዘቡ ወገኖች እንደመሰከሩት የምርጫዉ ሒደት ነፃና ትክክለኛ ነበር።ነጋሽ መሐመድ ከዜና መልዕክቶችየሚከተለዉን ዘገባ አሰባስቧል።

የምርጫዉ ሙሉ ዉጤት በይፋ አልተገለፀም።በራባት-ሞሮኮ የዶቸ ቬለ ዘጋቢ ማርክ ዱገ እንደታዘበዉ ግን እስላማዊዉ ፓርቲ ማሸነፉ አላጠራጠረም።ዝቢ ሐረካት አን-ነሕዳሕ-የትንሳቄ ንቅናቄ ፓርቲ ወይም ባጭሩ አነሕዳሕ-ትንሳኤ።የፓርቲዉ የምርጫ ዘመቻ ሥራ አስኪያጅ አብደልሐሚድ ጀለሲዪ እንዳስታወቁት ከ217ቱ የምክር ቤት መቀመጫዎች ፓርቲያቸዉ አርባ በመቶ ያሕሉን ይይዛል።

የምርጫዉ ዉጤት ቅር ያሰኘዉ፥ ያስከፋቸዉም ብዙ ነዉ።እንዲያዉም የዶቸ ቬለዉ ዘጋቢ ማርክ ዱገ የመጀመሪያ ስሙን፥ ሥራ እና ሐላፊነቱን ያልጠቀሰዉ ረሺድ አነሕዳሕ ምርጫዉን አጭብርብሯል በማለት እስከ መወንጀል ደርሷል።ረሺድ እንደሚለዉ ሰሜን ምሥራቂዊቱን የወደብ ከተማ አርያናሕን የሚቆጣጠሩት የአነሕዳሕ ሰዎች ናቸዉ።

«አርያናሕ ዉስጥ የቢሮ ሐላፊዎች፥ የምርጫ ታዛቢዎችም በሙሉ አነሕዳዎች ናቸዉ።ፓርቲዉ በሕገ-ወጥ መንገድ በመረጮች ላይ ተፅእኖ አድርጓል።ይሕ ቧልት ነዉ።የቀድሞዉን ዓይነት ሥርዓት የሚመልስ አብዮት አላካሔድንም።»

Wahlen Anhänger der Ennahda-Partei in Tunesien
የአነሕዳሕ ደጋፊዎችምስል picture-alliance/dpa

ረሺድ ባለፈዉ ሰኞ የአደባባይ ሠልፍ እንዲደረግ ጠይቆም ነበር።የግራ-ፖለቲከኞችም የረሽድን ቅሬታ ይጋራሉ።የአደባባይ ሠልፍ ጥሪዉን ግን እስካሁን የሰማዉ እንጂ የተቀበለዉ የለም።ብዙዎቹ ከአነሕዳሕ ጋር መስራት ይቻላል ብለዉ ያምናሉ።የምርጫዉ ዉጤትም ተዓማኒ ነዉ።የአዉሮጳ ሕብረት የታዛቢዎች ቡድን መሪ ሚሻኤል ጋሕለር እንደሚሉት ደግሞ የቱኒዚያዎች የምርጫ ሥርዓት እንደ ሕዝባዊ አብዮታቸዉ ሁሉ ለሌሎችም አብነታዊ ነዉ።

«በሕዝባዊዉ አብዮት ቱኒዞች የመጀመሪያዎቹ ነበሩ።በምርጫዉም የመጀመሪያዎቹ ናቸዉ።ሒደቱ በአብዛኛዉ ሙሉ በሙሉ አዎንታዊ ነበር።በየሐገራቸዉ ዲሞክራሲና ነፃነት ለማስረፅ የሚሹ ለሌሎቹ የአረብ ሐገራት ሕዝቦች ይሕንን እንደምሳሌ ቢወስዱት ይጠቅማቸዋል ብዬ አምናለሁ።ገቢራዊ ሊሆን እንደሚችል አሁን በትክክል ታይቷል።»

በጋሕለር አገላለፅ አብነታዊዉ ምርጫና ሒደቱ በቱኒዚያ ታሪክ የመጀመሪያዉ ነፃ ምርጫ ነዉ።ዉጤቱ ለአንጋፋዉ የፖለቲካ ፓርቲ ለአነሕዳሕ የመጀመሪያዉ ድል።ለፓርቲዉ መሪ ለረሺድ ጋኑቺ በሕዝብ ዘንድ ያላቸዉ ተቀባይነት ከፍተኛ ለመሆኑ ዋቢ፥ለልጃቸዉ ፍትሐዊ ድል።

«በምርጫ ዘመቻዉ ወቅትም ሆነ በዕሁዱ የድምፅ አሰጣጥ የጣስነዉ ሕግ የለም።ጉዳዩን በበላይነት ከሚመራዉ አስመራጭ ኮሚሽን የደረሰን አንዳችም ቅሬታ የለምም።እንደምናምነዉ የተሰራጩት ቅሬታዎች አሉባልታዎች ናቸዉ፥መሰረተ-ቢሶች።ማንኛዉም ፓርቲ ከሕግ በላይ ሊሆን አይችልም።እና ፍትሕ ሒደቱን ይቀጥላል።»

ዮስራ ጋኑቺ።አነሕዳሕ የቱኒዚያ አብዮት ቤን-ዓሊን ከሥልጣን እስካሰወገደበት ጊዜ ድረስ-ሕገ ወጥ፥ መሪ መስራቾቹም ስደተኞች ነበሩ።ለአብዮቱ ያደረጉት አስተዋፅኦም እምብዛም ነዉ።ግን አሸነፉ። የማሸነፋቸዉ ሰበብ ታዛቢዎች እንደሚሉት ብዙ ነዉ።ፓርቲ መሪዎቹ ለረጅም ዘመን-መገፋት-መሰቃየታቸዉ-የሕዝቡን ልብ አራርቶላቸዋል-አንድ።ደግሞ በተቃራኒዉ በሕዝቡ ዘንድ ሰርፆ የገባ-አንጋፋ ፓርቲ ነዉ፥ ሁለት።መሪዎቹ ቱርክን ለተከታታይ ዓመታት የሚመራዉን እስላማዊ ፓርቲ መርሕ እንደ አብነት እንከተላለን ማለታቸዉ-ደግሞ የሐይማኖተኛዉንም የለዘብተኛዉን መራጭ ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል።

የፓርቲዉ መሪዎች ብቻቸዉን ጊዚያዊ መንግሥት መመሥረት የሚያስችለዉን አብላጭ መቀመጫ እናገኛለን የሚል እምነት የላቸዉም።በዚሕም ምክንያት መሪዎቹ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ለመቀናጀት እየተደራደሩ ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ