1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የቲያንስ ኩባንያ አጠራጣሪ የሽያጭ እና ደንበኛ የመመልመል አሰራር

ረቡዕ፣ የካቲት 1 2009

ጂዳ እና ካርቱም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተው ቲያንስ ከተሰኘ የቻይና ኩባንያ ጋር የጀመሩት ሥራ እጣ ፈንታ አሳስቧቸዋል። ኢትዮጵያውያኑ ለኩባንያው ከ4,000-11,800 ብር ከፍለዋል። ኩባንያው የኢትዮጵያን ሕግጋት ጥሷል በሚል ፈቃዱ ተሰርዟል።

https://p.dw.com/p/2XBl4
Geldscheine
ምስል DW/E. Bekele Tekle

የቲያንስ ኩባንያ አጠራጣሪ የሽያጭ እና ደንበኛ የመመልመል አሰራር

ላለፉት አምስት አመታት በጅዳ የኖረው ሴይማን ሐቢብ በኢትዮጵያ ስለተጀመረው አዋጪ የንግድ ሐሳብ ሲሰማ እድሉን ከእጁ ለማስገባት አላመነታም። ወሬውን የሰማው አዲስ አበባ በሚኖር የቅርብ ዘመዱ በኩል ነበር።  ሴይማን ስለ ሥራው በግል ያረጋገጠው ነገር ባይኖርም «ለበርካታ አመታት ሰርቼበታለሁ» ያለውን ወዳጁን ግን አምኖታል። ሴይማን በመልማዩ በኩል ቲያንስ ኢትዮጵያ ቢዝነስ የንግድ ሥራን ነበር የተቀላቀለው። እንደ ጎርጎሮሳዊው የዘመን አቆጣጠር በ2006 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ቢሮውን የከፈተው ኩባንያ መቀመጫውን በቻይናዋ ቲያንጂን ከተማ ያደረገው የቲያንስ ግሎባል ተቀጥላ ነው።  በቻይና የሚቀመሙ ባሕላዊ መድሐኒቶችን መጠቀም እና ማከፋፈል የንግድ ሥርዓቱ ዋንኛ ምሰሶ ነው። ሴይማን ዛሬ ላይ ሆኖ እንደሚያስታውሰው ለበርካታ ዓመታት ሰርቼበታለሁ ያለው ዘመዱ ከነገረው ውጪ የሚያውቀው ነገር አልነበረም። የሰማውም አትራፊነቱን ብቻ ነበር። እናም 11,800 ብር ከፍሎ ተቀላቀለ።በሱዳን ካርቱም በምግብ አብሳይነት የሚያገለግለው ሙሉቀን በውቀቱ የ24 ዓመት ወጣት ነው። ሙሉቀንም እንደ ሴይማን ሁሉ ምክሩን የሚያሳካበት አዋጪ የንግድ ዕድል ከእጅህ ገብቷል ተብሎ ተሰብኳል። የሰበከችው ደግሞ የሚያውቃት የሰፈሩ ልጅ ነበረች።


ቲያንስ ኢትዮጵያ የተባለው ኩባንያ የሚከተለው የንግድ ሥርዓት የኢትዮጵያ ሕግጋትን ይጥሳል የሚል ጥያቄ ተነስቶበት ሕልውናው ጥያቄ ውስጥ ቢወድቅም ሴይማን እና ሙሉቀን ገንዘባቸውን የሚያስመልሱበት አሊያም የተባለውን ሥራ የሚቀጥሉበት መንገድ ምን እንደሆነ ዛሬም ድረስ አልገባቸውም። ፌስቡክ እና ዋትስአፕን በመሰሉ የመገናኛ ዘዴዎች የተሻለ የሥራ እድል እና ገቢ ፍለጋ ርቀው የተጓዙ ኢትዮጵያውያንን የሳበው ቲያንስ መጀመሪያ የሞቀው አገር ውስጥ ነበር። አዲስ አበባ ቄራ መብራት ኃይል አካባቢ በጋራዥ ሥራ ላይ የተሰማራው እንዳለ የጨበጠው ተስፋ ሕልም ከሆነባቸው መካከል አንዱ ነው።
ሴይማን፤ሙሉቀንም ሆነ እንዳለ መነሾውን ከወደ ቻይና ያደረገው ኩባንያ የሸጠላቸው አሊያም ወደፊት ደንበኞች እየመለመሉ እንዲሸጡ ያዘጋጀላቸው ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት አያውቁትም። 

የቲያንስ አከፋፋዮች ምርቶቹ ከኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒት እና የጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባሥልጣን ፈቃድ ማግኘታቸውን ለሚመለምሏቸው ይናገሩ ነበር። አንዴ መድኃኒት ሌላ ጊዜ ደግሞ ለሰውነት ጠቃሚ ግብዓቶች እንደሆኑ የሚነገርላቸው የቲያንስ ምርቶች ከኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒት እና የጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባሥልጣን «ተጨማሪ ምግብ» ተብለው ፈቃድ ማግኘታቸውን የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳምሶን አብርሐ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የቲያንስ ምርቶች አከፋፋዮች «ተፈወስን» ይበሉ እንጂ መድኃኒቶች አለመሆናቸውን አቶ ሳምሶን በአጽንዖት ተናግረዋል።


ኩባንያው የሚከተለው ሰንሰለታዊ የሽያጭ እና ምልመላ ሥርዓት የፒራሚድ ቅርፅ አለው።  የንግድ ሥራውን የሚጀምረው መስራች ሌሎች አባላት በመመልመል ከአናት ይቀመጣል። በመስራቹ የሚመለመል ሁለተኛ ሰው ወደ አሰራሩ ሲገባ ወጪ ያደረገውን ገንዘብ ለማስመለስ ሌሎች ምልምሎች ወደ ሰንሰለቱ ማስገባት ይጠበቅበታል። ሰንሰለቱን የሚቀላቀሉ ሁሉ ለመልማያቸው መክፈል የሚጠበቅባቸው ሲሆን ገንዘባቸውን ለማስመለስ ትርፋማም ለመሆን አዳዲስ ሰዎች ማስገባት አስፈላጊ ነው። ይኸንን አወቃቀር ቀረብ ብለው የፈተሹ የኤኮኖሚ ባለሙያዎች የማጭበርበሪያ ሥልት እንደሆነ ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ። በጎርጎሮሳዊው 1990ዎቹ በዩናይትድ ስቴትስ ሰንሰለታዊውን የሽያጭ እና ምልመላ ሥልት የሚከተሉ በርካታ ኩባንያዎች ተፈጥረዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ፌዴራል የንግድ ኮሚሽን ስልቱን የሚከተሉ ኩባንያዎችን እየተከታተለ በመርመር ክስ ይመሰርታል። ኩባንያዎቹንም እንዲዘጉ ያደርጋል። ከአራት አመታት በፊት የጀርመን አቃብያነ-ሕግ በተመሳሳይ የአሰራር ስልት የተሰማሩ ኩባንያዎችን በመመርመር ለፍርድ ቤት አቅርበዋል። የጀርመን፤ ብሪታንያ እና ዩናይትድ ስቴትስን የመሳሰሉ አገራት ሕግጋት ሰንሰለታማ አሰራር የሚከተሉ ኩባንያዎችን እየተከታተሉ ይከሳሉ፤ከሥራ ያግዳሉ። አዲስ አበባ የጀመረውን ሥራ ኬንያ ሊቀጥል ድንበር የተሻገረው አሕመድ አደም የኩባንያው አሰራር ሰንሰለታማ አይደለም ሲል ይከራከራል። 


ከስደት አገር ላይ መስራት ይሻላል የሚል ተስፋ ሰንቆ የነበረው ሴይማን ሐቢብ ከነ ቤተሰቦቹ ከ47,000 ብር በላይ ከስሯል። ቲያንስ ኢትዮጵያ የተሰኘው ድርጅት የኢትዮጵያ ንግድ ፈቃድ መሰረዙ ተሰምቷል። የድርጅቱ አከፋፋዮች ግን ከአገር ርቀው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ማነጣጠራቸው አልቀረም። ዛሬም ስራው አዋጪ ነው ሲል የሚከራከረው አሕመድ ኬንያ ከትሟል። የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ጥበቃ ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ገብረመድኅን ቢረጋ ከጅማሮው የጉዳዩን አሳሳቢነት አቤት ብለን ነበር ብለውኛል። 
ሴይማን፤ሙሉቀን እና እንዳለ ዛሬም ቁጭታቸው አልበረደም። በኢትዮጵያ እንዲሰራ ሕጋዊ ፈቃድ ተሰጥቶት «በደል ፈፅሞብናል» የሚሉትን ድርጅት የሚሞግቱበት መንገድ ስለመኖሩም እርግጠኛ አይደሉም። ሥራው ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ወዳጆቻቸውን ጭምር አሳጥቷቸዋል፤ከቤተሰብ አቃቅሯቸዋል። 
እሸቴ በቀለ 
ኂሩት መለሰ