1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ነዋሪዎች አስተያየት

ማክሰኞ፣ መስከረም 6 2012

የግብፅ ባለስልጣናት እንዳሉት ሥለ ግድቡ የዉኃ አሞላልና አሰራር ካይሮ ያቀረበችዉን ረቂቅ ደንብ ኢትዮጵያ ባለመቀበሏ ስብሰባዉ በሌላ ቀጠሮ ተበትኗል።ኢትዮጵያ ዉስጥ ደግሞ የአማራ ነዋሪዎች የግድቡ ግንባታ ተቀዛቅዟል የሚል ቅሬታ እያሰሙ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3PjbW
Nil Dammbau in Äthiopien Archiv 28.05.2013
ምስል William Lloyd-George/AFP/Getty Images

የሕዳሴ ግድብ ዉዝግብና ቅሬታ

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ በምታስገነባዉ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ሰበብ ከግብፅ ጋር የገጠመችዉን ዉዝግብ ለማስወገድ የሁለቱ ሐገራትና የሱዳን ሚንስትሮች ሰሞኑን ያደረጉት ስብሰባ ያለዉጤት አብቅቷል።የሰወስቱ ሐገራት የዉኃ ሚንስትሮች ከትናንት በስቲያና ትናንት ካይሮ ግብፅ ዉስጥ ሲነጋገሩ ነበር።የግብፅ ባለስልጣናት እንዳሉት ሥለ ግድቡ የዉኃ አሞላልና አሰራር ካይሮ ያቀረበችዉን ረቂቅ ደንብ ኢትዮጵያ ባለመቀበሏ ስብሰባዉ በሌላ ቀጠሮ ተበትኗል።ኢትዮጵያ ዉስጥ ደግሞ የአማራ ነዋሪዎች የግድቡ ግንባታ ተቀዛቅዟል የሚል ቅሬታ እያሰሙ ነዉ። በአማራ መስተዳድር የታላቁ ግድብ ማስተባበሪያ ፅሕፈት ቤት በበኩሉ፣ የክልሉ ሕዝብ ለግድቡ ማሰሪያ ባለፈዉ ዓመት ብቻ ከ1.6 ቢሊዮን በላይ ብር አዋጥቷል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ሥራ ሲጀመር መላው ህዝብ በከፍተኛ ወኔና ተነሳሽነት ሥራውን በራሱ ገንዘብ ለማስጀመርና ለማስጨረስ ከፍተኛ መነሳሳት ያሳየበት ነበር፡፡ የመንግስት ሰራተኛው ከደመወዙ እቀነሰ፣ ነጋዴው ከእለት ገቢው እቆረጠ ሌላውም ከሚያገኛት እያብቃቃ የቦንድ ግዥውን ፈጽሟል፡፡ መንግስት በበኩሉ ሂደቱን የሚያስተባብር ጽ/ቤት በፌደራል ደረጃና በክልሎች በማደራጀት ለሥራው ከፍተኛ ትኩረት ሰትቶ ተንቀሳቅሷል፡፡ ሆኖም የቀድሞው የግድቡ ሥራ አሰኪያጅ ከተገደሉ በኋላና ከግንባታ ሂደቱ ጋር ተከስተው ከነበሩ ጉዳዮች በኋላ የነበረው ግለትና ተነሳሽነት መቀዛቀዙን ያነጋገርናቸው የአማራ ክልል ነዋሪዎች አመልክተዋል፡፡
አቶ ዓለሙ ገረመው የመንግስት ሰራተኛ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ግድቡ ስላለበት ሁኔታ ዝርዝር መረጃ አይሰማም፣ ግድቡን ለማስቀጠል የገንዘብ ማሰባሰብ ስራውም የለም ነው ያሉት፡፡
አቶ አንዷለም ጸጋዬ በንግድ ስራ የሚተዳደሩ ሲሆን ቀደም ባሉት ጊዚት በንግድ ዘርፍ ማህበራት በኩል ለግድቡ መዋጮ ያደርጉ እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን ስለግድቡ ምንም የሚወራ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በዞን ደረጃ መዋቅር እንደሌለው የሚናገሩት የደብረ ማርቆስ ነዋሪ አቶ ጋሻዬ ጌታሁን ቀደም ሲል እርሳቸው የሚመሩት የህዝብና ሚዲያ ግንኙነት ጽ/ቤት ስራውን በተደራቢነት ሲሰራው እንደነበር ጠቁመው አሁን ግን እቅድም ሆነ የሥራ ትዕዛዝ ከሚመለከተው አካል እየወረደ አይደለም፣ የቅስቀሳ ስራውም ሙሉ በሙሉ ቆሟል ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል የታላቁ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ህዝባዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ተናኜ አበበ አንዳሉት ከህብረተሰቡ የተለያዩ ሀሳቦች እንደሚሰሙ አመልክተው ሆኖም ግን ህብረተሰቡ ባለፈው በጀት ዓመት አንድ ቢሊዮን 600 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡
በያዝነው ዓመት የቅስቀሳ ስልቱን በመቀየር ህብረተሰቡ ለግድቡ ያለውን የባለቤትነት ስሜት ለማስቀተል መታቀዱን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ ሚኒስትሮች በግድቡ የውሀ አሞላልና አለቃቅ ዙሪ በግብፅ ካይሮ የሶስትዮሽ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ፋና ብሮድካስት ኮርፖሬሽን መስከረም 4/2012 ዓ ም እንደዘገበው ውይይቱ ሶስቱም አገሮች አሸናፊ የሚሆኑበት እንደሚሆን የግብፁ የውሀ ሚኒስትር ዶ/ር ሞሀመድ አብዱል አቲ መናገራቸውን ዘገቧል፡፡


ዓለምነው መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ