1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታው ውዝግቦች

ዓርብ፣ ነሐሴ 17 2011

የኢትዮጵያ መንግሥት በ1986 ዓ.ም. ገደማ ጀምሮ ሥራ ላይ የነበረውን የትምህርት ሥርዓት ላይ ማሻሻያዎች ለማድረግ የጀመረው ዝግጅት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/3OMUV
Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኢትዮጵያ መንግሥት ያዘጋጀው የትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታ በይፋ ሥራ ላይ ሲውል ተማሪዎች ትምህርታቸውን በሰባት አመታቸው ጀምረው በ18 አመታቸው ያጠናቅቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። ተማሪዎች በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ለስድስት አመታት፤ በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ለሁለት አመታት እንዲሁም በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ እንደ ቀድሞው የአራት አመታት ቆይታ ይኖራቸዋል። በ2013 ዓ.ም. ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ በሚጠበው የትምህርት ሥርዓት ማሻሻያ መሠረት የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ክልል አቀፍ ፈተና ይወስዳሉ። የስምንተኛ ክፍል ፈተና ብሔራዊ ለማድረግ የታቀደ ሲሆን ላለፉት 18 ገደማ አመታት ይሰጥ የነበረው የአስረኛ ክፍል አጠቃላይ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና እንዲቀር ያደርጋል።

ባለፈው ረቡዕ የትምህርት ምኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በጉዳዩ ላይ ረዘም ያለ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ማኅበራዊ ድረ-ገፆች የተለያዩ አስተያየቶች እና ውዝግቦች ታይቶባቸዋል።

ሰለሞን ሱንፐር የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ «ትውልድን መግደል በኛ ላይ ጀመረ። 1993 ዓ.ም.- አንድ ትውልድ መስዋዕት ሆነ- የጠፉም.... ያልጠፋም እንዳለ.... ሆኖ። ዛሬ ግን..... እግዚአብሔር ይመስገን ከ 18 አመት በኋላ ምኞታችን ሊሳካ ነው» ሲሉ በተደረገው ማሻሻያ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከመልዕክታቸው መረዳት እንደሚቻለው ሰለሞን በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ለውጥ ተደርጎ የአስረኛ ክፍል አጠቃላይ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ለመጀመሪያ ጊዜ ከተፈተኑ መካከል አንዱ ናቸው። በ1993 ዓ.ም. ይኸን ፈተና ተፈትነው የማለፊያ ነጥብ ያገኙ ተማሪዎች የመሰናዶ ትምህርት እንዲከታተሉ ተደርጓል። ሰላም ካስትሮ በዚያው በፌስቡክ «ለኛ ለከሸፍነው ትውልዶች አምላክ ይርዳን ...የማይሰራ መድሀኒት መሞከሪያ ስለነበርን» ሲሉ አስተያየታቸውን አጋርተዋል። አዱኛ ባይህ ደግሞ «ትክክለኛ የለውጥ ጅምር። ብዙዎቹ "ትውልድ ገዳይ "ብለውት ነበር በወቅቱ። እንዲህ በጥናት ላይ ተመሥርቶ የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው ለውጡ ውጤታማ ሚሆነው» የሚል አስተያየታቸውን አስፍረዋል።

ለመሆኑ የትምህርት ሥርዓቱ ስለምን «ትውልድ ገዳይ» እስከ መባል ደረሰ? የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በትምህርት ሥርዓቱ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መስፋፋታቸው እንደ ትልቅ ስኬት ይቆጥራሉ። ከዚያ ባሻገር የከፍተኛ የትምህርት ተደራሽነት ፍትኃዊ በማድረግ በርካቶችን በማስመረቁ የትምህርት ሥርዓቱ ውጤታማ ሆኗል ባይ ናቸው። የጥራት ጉዳይ ላይ ግን ውስብስብ ችግሮች እንደነበሩ አይሸሽጉም። የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ሹማምንት እና የአገሪቱ ባለሥልጣናት በዚሁ ሳምንት በትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታው ይዘቶች ላይ ባደረጉት ውይይት ችግሮቹ ጥልቅ መሆናቸውን በቁጥር አስደግፈው አቅርበዋል።

የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ምኒስትር ድዔታው ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ.ር.) «በ4ኛ ክፍል የሒሳብ እና የእንግሊዘኛ ቋንቋ ችሎታ ሲመዘን 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ የሚያመጡት እንግሊዘኛን 27.4 ነው። ሒሳብ የተሻለ ነው። 8ኛ ክፍል ሲደርሱ ሒሳብ፣ ፊዚክስ፣ ባዮሎጂ እና ኬሚስትሪን ብናይ፤ ሒሳብ 18 በመቶው ብቻ ነው 50 ከመቶ በላይ የሚያመጣው። 10ኛ ክፍል ላይ አማካዩን ብናይ ከአጠቃላይ ተማሪ 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ የሚያመጣው 9 በመቶ ተማሪ ብቻ ነው። ወደ 12ኛ ክፍል ስንደርስ መሰናዶ ከሚያጠናቅቁት ውስጥ 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት የሚያስመዘግቡት 26 በመቶ ተማሪ ነው» ብለው ነበር።

አሊ ዘውዱ ታዲያ በፌስቡክ «ብታወርደው ብታቀናው የመምህርን ጥቅማ ጥቅም ሳታስተካክል ጠብ የሚል ነገር የለም» ሲሉ የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት የገጠሙትን ፈተናዎች መቅረፍ አዲስ ፍኖተ-ካርታ በማዘጋጀት ብቻ የሚቀየር እንዳልሆነ ሐሳባቸውን አካፍለዋል። ከልለው አበራ ደግሞ «ፍኖተ ካርታ እያሉ አደረጃጀት ቢቀያይሩት የትምህርት ጥራት ላይ ለውጥ አያመጣም ። ይልቁንስ ተማሪውን ማዳንም መግደልም የሚችለው ክፍል ውስጥ የሚውለው መምህሩ ስለሆነ መንግስት መምህሩ ላይ ትኩረት ቢሰጥበት የትምህርት ጥራት ለማምጣት እንዴት ይቀል ነበር!» ሲሉ ከዘውዱ ታደሰ ጋር የተስማማ አስተያየት አስፍረዋል።

አቡበከር ሰዲቅ አባባሊ ደግሞ «አሁን አላግባብ በጓሮ በር እየገቡ እንዳሸን ከፈሉ የግል ኮሌጆችና አንዳንድ በጥቅም የታወሩ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በለብለብ እስከ 2ኛ ድግሪ የተመረቁና ትውልዱን እያበላሹ ያሉ መምህራን ካልተበጠሩ ይሄን ለውጥ መሬት ማስነካት ከባድ ነው» ብለዋል።

እስክንድር ጊድቦሶ ደግሞ «ከትውልድ ገዳይ ወደ ትውልድ ጨራሽ ፖሊሲ እንዳንሸጋገር ባንድ ጀንበር ሳይሆን ቢያንስ የሙከራና የትግበራ ጊዜ ያስፈልገው ነበር። አሁን በትምህርት ላይ ያሉ ተማሪዎች በቀጥታ ወደ ዚህ መግባታቸው በምን መጽሀፍና በምን መመሪያ ሊማሩ ነው? የድሮን ከምንናፍቅ ያሁኑን ብሎም የወደፊቱን አስበን የተሻለ የምንሆንበት መንገድ ቢታሰብ ይሻል ነበር» ሲሉ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

Jahresrückblick 2010 - Verbraucherzentrale verklagt Facebook
ምስል picture alliance / dpa

 

ቃልኪዳን ነጋሽ ደግሞ «ትናንት እንከን የለሽ እና አይነኬ ነዉ እያሉ ሲያሞካሹት የነበረዉ የትምህርት ፓሊሲ ችግሮች እና የትምህርት ጥራት ጉዳይ ላይ ጥያቄ ያነሱ ምሁራንን ሲያሸማቅቁ የነበሩና የብቃት ችግር ያለባቸዉንና ከዕዉቀት የተጣሉ ምልምል ካድሬዎቻቸዉን የዩንቨርሲቲ መምህር አድርገዉ ሲያበቁ “በ 1 ለ 5 አደረጃጀት፤ በሰራዊት አግባብ የትምህርት ግቦችን እናሳካለን!” እያሉ ሲፎክሩ የነበሩ፤ ብቁ መምህራንን በካድሬዎቻቸዉ እያስገመገሙ ሲያሸማቅቁ የነበሩ እና የከፍተኛ ትምህርት ስታንዳርዶችን በጭንቅላታቸዉ ልክ አዉርደዉ ድግሪ ሲያድሉና ለራሳቸዉም ሲታደሉ የነበሩ ኢህአዴግ ጠፍጥፎ የሰራቸዉ የምሁር ለምድ የለበሱ ፖለቲከኞች ዛሬ ጭንብል ቀይረዉ ስለ ትምህርት ስርዓቱ ዉድቀት ይተነትናሉ፤ መፍትሄዉም በእጃችን ነዉ ብለዉ ለሌላ ዙር ጥፋት ይፈጥናሉ። አቤት የኛስ አበሳ!» ሲሉ ጉዳዩ እጅግ ውስብስብ እንደሆነ የሚጠቁም አስተያየት አስፍረዋል።

የትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታው በትምህርት ቤቶች ከሶስተኛ ክፍል ጀምሮ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት እንዲሰጥ ያቀረበው ሐሳብ የከረረ ተቃውሞ ቀስቅሷል። በፌስቡክ እና በትዊተር ገጾቹ ጉዳዩን አጥብቆ የተቸው ጃዋር መሐመድ በትናንትናው ዕለት ለኦሮሚያ ሚዲያ ኔወርክ በሰጠው ቃለ-መጠይቅ «ይኸን ፍኖተ-ካርታ ኦሮሚያ ውስጥ እናስተምራለን ብለው ባያስቡ ይሻላቸዋል። ምክንያቱም ይኸ ሕዝብ ለ50 አመት የታገለው እንዲህ አይነት የአድሃሪያን እና የአሀዳዊ ሥርዓትን እንዲቆለል» አይደለም ብሎ ነበር። የትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታው አዘገጃጀት ላይ ብርቱ ጥያቄ እንዳለው የገለጸው ጃዋር በፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው አጠር ያለ ፅሁፍ «ኦሮምኛን የስራ ቋንቋ አድርጉ ተብለው እምቢ ካላችሁ  አማርኛ በኦሮሚያ ትምህርት ቤቶች አይሰጥም» የሚል ጠበቅ ያለ አስተያየት ጽፏል። የጃዋር አስተያየት ጉዳዩን የበለጠ አወዛጋቢ አድርጎታል።

ጋዜጠኛ ኤልያስ አማን «ሕገ-መንግስቱ መንግስቱ አማርኛ ቋንቋን በግልጽ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ አድርጎ በአንቀጽ 5 ቁጥር 2 ደንግጎ አሥቀምጦታል። እንደ አብዛኛው የፌዴራልም ሆነ አሀዳዊ የፖለቲካ ሥርዓትን የሚከተሉ ሀገራት ዜጋው በሙሉ እንዲያውቀው፣እንዲማረው፣እንዲጠቀመው የሚደረግ የጋራ መግባቢያ ነው ማለት ነው! ይህ ማለት ግን ብሄራዊ ቋንቋ ነው ማለት አይደለም! ኢትዮጵያ ኦፊሺያል የሥራ ቋንቋ እንጂ ብሄራዊ ቋንቋ የላትም። ይህም የሆነው የቋንቋ ብዝኃነት ስላላት ይህም ስለሚከበር ነው። አሁንም ይህ ማለት ግን ሀገራት አንድ የሥራ ቋንቋ ብቻ ይኖራቸዋል ማለትም አይደለም! ከአንድ በላይ የሥራ ቋንቋዎች ሊኖራቸው ይችላል! ሌሎች ቋንቋዎችን የሥራ ቋንቋ ለማድረግና ሁሉም ዜጋ እንዲሁ ይማረው፣ያውቀው ዘንድ መታገል አንድ ነገር ነው! የቋንቋ ብዝኃነት ይጠቅማል እንጂ ማንንም አይጎዳም። ለዚህ ደግሞ ሕገ-መንግስቱም ሊሻሻል ግድ ነው ማለት ነው። አሁን በሕገ-መንግሥቱ የሀገሪቷ የሥራ ቋንቋ ተደርጎ የተደነገገን ቋንቋ ለምን በሥርዓተ ትምህርቱ ከታች ጀምሮ እንድንማረው ይደረጋል ማለት ግን ኢ-ሕገ መንግስታዊም ይመስለኛል» ብለዋል።

Symbolbild: Pinterest
ምስል picture alliance/X. Gs

አባቦራ በትዊተር «አማርኛ ቋንቋ በኦሮሚያ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እንደ አንድ የትምህርት አይነት ማስተማር ልጆቻችን የበለጠ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል እንጂ አይጎዳቸውም። አፋን ኦሮሞ የፌዴራል ስራ ቋንቋ ሲሆን ልጆቹ በሁለቱም ቋንቋ ተወዳድረው ስራ የማግኘት እድላቸውን ያሰፋላቸዋል» ብለዋል።

ሳሙኤል በዛብህ «ዛሬ በሀገር ደረጃ አማርኛ ቋንቋ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ይሰጣል ሲባል በድል አድራጊነት ስሜት ጮቤ የረገጠ ነገ ከነገ ወዲያ አፋን ኦሮሞ በመላው ሃገሪቱ የስራ ቋንቋ እንዲሆን ተወሰነ ሲባል ድብርት ውስጥ ሊገባ አይገባውም። ሰጥቶ መቀበልን ካለመድን ሁሉ ነገራችን የእምቧይ ካብ የሚሆነው» ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

የትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታው «አፍ መፍቻ ቋንቋ፣ ሁለተኛ ቋንቋ ለአገራዊ የጋራ መግባባቢያ፣ ሌላ ቋንቋ በክልል ውስጥ ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች፣ እንዲሁም ሦስተኛ ቋንቋ ለአለም አቀፍ መግባቢያ የያዘ የቋንቋ ፖሊሲ ማስተዋወቅ» የሚል ሐሳብ ይዟል። በኢትዮጵያ ባለፉት አመታት በታዩ ተቃውሞዎች የኦሮሞ ልሒቃን ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል ኦሮሚኛ የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ ይሁን የሚለው ይገኝበታል። ይኸ ግፊት አሁንም በተለያዩ መንገዶች ሲገለጽ ይታያል። የትምህርት ጉዳይ ተነስቶ ክርክር በበዛበት ቱሉ ሊባን ይኸንንው ሐሳብ ድጋሚ በፌስቡክ በኩል አቅርበዋል።

«አፋን ኦሮሞ አንድን ቋንቋ ሀገራዊ የሥራ ቋንቋ ለማድረግ የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን ሁሉ ያሟላል። እንዲያውም ከበቂ በላይ ያሟላል» የሚሉት ቱሉ ሊባን በግል የፌስቡክ ገጻቸው ስምንት ነጥቦች ዘርዝረዋል። ነጥቦቹ ቋንቋው ለምን የኢትዮጵያ የሥራ ቋንቋ መሆን እንዳለበት አስረጂ ያሏቸው ናቸው።

የመጀመሪያው ኦሮሚኛ «ወደ ግማሽ የሚጠጋ የሀገሪቱ ሕዝብ በአፍ መፍቻነት» የሚናገረው መሆኑ ነው።  ቱሉ ሊባን «ኩታገጠም ክልሎች በጋራ መግባቢያነት ይጠቀሙበታል፤ ክፍለ አህጉራዊ መግባቢያ ነው (በኬንያ፣ በሶማሊያ፣በጂቡቲ፣ በኢትዮጵያ ተናጋሪዎች አሉት)፤ የተደራጀ የጽሕፈት ሥርዓት አለው፤ በቢሮክራሲና በትምህርት፣ በእምነት በሥነጽሑፍና በሥነጥበብ ቋንቋነት እምርታዊ ዕድገት አሳይቷል» ይላሉ። «የተለያዩ መዛግብተ ቃላት ተዘጋጅተውለታል፤ ቋንቋው ሀገራዊ ህልውና ማግኘቱ አንድነትንና ፖለቲካዊ መረጋጋትን ያበረታታል፤ በሁሉም ዘንድ በሚባል ደረጃ ቋንቋው ፌዴራላዊ እንዲሆን ሀገራዊ መግባባት አለ» ሲሉ ፅፈዋል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ