1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትምህርት ጥራትን የተመለከተው ውይይት በባሕር ዳር

ሰኞ፣ ኅዳር 19 2015

እየታየ ላለው የትምህር ጥራት ውድቀት የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት አንዱ ምክንያት እንደሆነ ምሁራን አመለከቱ። የመምህራንና የትምህርት አመራር አካላት በሌላ ተጓዳኝ ተግባራት መሠማራት ደግሞ ሌላው ተጠቃሽ ምክንያት እንደሆነም ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/4KCAD
Äthiopien | Gipfel zur Bildungsqualität in der Region Amhara
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

«ለትምህርት ጥራት መውደቅ በርካታ ባለድርሻ አካላት ተጠያቂ መሆናቸው»


እየታየ ላለው የትምህር ጥራት ውድቀት የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት አንዱ ምክንያት እንደሆነ ምሁራን አመለከቱ። የመምህራንና የትምህርት አመራር አካላት በሌላ ተጓዳኝ ተግባራት መሠማራት ደግሞ ሌላው ተጠቃሽ ምክንያት እንደሆነም ተገልጿል። አማራ ክልል ላይ ከሰሞኑ በተካሄደው የክልሉን የትምህርት ይዞታ በተመለከተ ውይይት፤ የትምህርት ፖሊሲውም ለትምህርት ጥራት መውደቅ በዋናነት ተጠቅሷል። የ2014 ዓ ም የ12ኛ ክፍል ፈተናን አስመልክቶ በነበሩ ችግሮችና አጠቃላይ በትምህርት ጥራት ማሽቆልቆልን በተመለከተ ከትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር ሰሞኑን በባሕር ዳር ከተማ ውይይት ተካሂዷል። 
በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ፈተና በአንዳንድ የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች የተፈተኑ ተማሪዎች ያሳዩት «ያልተገባ» የተባለ ተግባር የትምህርቱ ስርዓት የደረሰበትን ውድቀት የሚያሳይ እንደሆነ ምሁራን ተናግረዋል፡፡ ክስተቱ አሳፋሪ ቢሆንም ይፋ መውጣቱ ግን በችግሩ ላይ ተነጋግሮ መፍትሔ ለማምጣት እንደሚያግዝ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ቢሻው አመልክተዋል፡፡
«አሁን ችግሩ ፈጥጦ ወጥቶ ልጆቻችን ለመፈተን ፍላጎት እስከማጣት እደረሱ ነው፣ ይህንን እንደጥሩ አጋጣሚ ተጠቅመን እንደ መንደርደሪያ ነው መውስድ ያለብን፣ ይህ ባይሆን ኖሮ ሁሉም ያገባናል የሚል አካል ለትምህርት የሚሰጠውን (ትኩረት) ላይሰጥ ይችል ነበር።» ብለዋል፡፡ አጠቃላይ ለትምህርት ጥራት መውደቅ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ነፃ የክፍል ዝውውርን የሚፈቅደው የትምህርት ፖሊሲ ዋናው የችግሮች ሁሉ «አውራ» እንደሆነም ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ተናግረዋል።በአማራ ክልል ውዝግብ ያስነሳዉ የተማሪዎች ውጤት
የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች መድረክ ሰብሳቢ ዶ/ር ታፈረ መላኩ በበኩላቸው ለትምህርት ስርዓቱ ብልሽት ምክንያቱ፣ «ትምህርት ወይም ፈተና የምንለው ነገር በየትኛውም ሀገር ፖለቲካ ወይም ብሔር ሆኖ አያውቅም፣ በእኛ አገር ግን የፖለቲካው ብልሽት ሄዶ ሄዶ ፈተናዎቹን ሁሉ የፖለቲካና የብሔር መልክ ሰጣቸው፣ ከዚያም ወረድ ሲል ደግሞ ፤ የእኔ ተማሪዎችን፤በሚል ወንዜነትን ተላበሰ፣ ስለዚህ ፤የእኛ ተማሪዎች፣ የእኛ ክልል ተማሪዎች ብዙ ቢያልፉ፤ እንዲህ የሚል ስሜት በጣም አደገኛ ነው… በደቦ ፈተና ተሰርቶ መልካም ትውልድ ሊፈጠር አይችልም፣በደቦ ፈተና ተሰርቶ መልካም ዜጎችን ማፍራት አይቻልም፣ በደቦ እየሠራህ መልካም ማኅበረሰብ መፍጠር አትችልም፣ አመራሩ ጭምር የተጋራበት፣ በሚያሳዝን መንገድ በየትኛውም አገር፣ በአፍሪካም ብንለውም ፈፅሞ የሌለ በእኛ አገር የተከሰተና በጣም አሳፋሪ የሆነ ነገር፣ ያ ነው መንስኤ ነው ብየ የማስበው፡» ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ማዕተብ ታፈረ በበኩላቸው፣ በትምህርት ዘርፉ ለተከሰቱ ውድቀቶች ከወላጆች ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተጠያቂ መሆናቸውን ጠቁመዋል፣ በተለይ አንዳንድ መምህራንና የትምህርት አመራሮች በሌሎች ሥራዎች መጠመድ ለትምህርቱ የተሰጠውን ትኩረት ወደ ኋላ ጎትቶታል ነው ያሉት፡፡
በዘርፉ ያለውን ጥራት ለማሻሻል ከሚወሰዱ እርምጃዎች መካከል ተመራቂ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ከዚህ ዓመት ጀምሮ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ከትምህርት ሚኒስቴር የተወከሉት አቶ ጌታቸው ተፈራ ተናግረዋል፡፡
«ትልቅ እርምጃ ነው ብየ የምወስደው የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ የሚሰጠው የመውጫ ፈተና (Exit Exams) ከተፈተነ በኋላ ነው፣ ይህ ለሁሉም መልዕክት ነው የሚሰጠው፣ እዚያ ላይ ሲወድቅ (ተማሪው) የሚወድቀው ተማሪው ብቻ አይደለም የሚወድቀው ተቋሙ ነው፣ የሚወድቀው መመህሩ ነው ፣ ስለዚህ ሁሉንም የሚነካካ ነው፣ ይህ ዘንድሮ ይጀመራል ተብሎ ሥራ እየተሠራ ነው» ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል ከ85 ከመቶ በላይ የሚሆኑት ከደረጃ በታች መሆናቸው ለትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል ሌለው ምክንያት እንደሆነ የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
ዓለምነው መኮንን

Äthiopien | Gipfel zur Bildungsqualität in der Region Amhara
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ