1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትራምፕ መልዕክት

ሰኞ፣ ግንቦት 14 2009

ሳዑዲ አረቢያ ድሮም ቢሆን በየዓመቱ 82 ቢሊዮን ዶላር ለጦር መሳሪያ ትከሰክሳለች።ኢራን 25 ቢሊዮን።ሳዑዲ አረቢያ አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢ 745 ቢሊዮን ነዉ።የኢራን 566 ቢሊዮን።የኢራን ሕዝብ 81 ሚሊዮን ነዉ፤ ሳዑዲ አረቢያ 32 ሚሊዮን።ሪያድ-ዋሽግተኖች ብብት ስር ተወሽቃ፤ ቴሕራን-ሞስኮን ተተግና ይዛዛታሉ።ባግዳድን ይሆኑ-ይሆን? ማናቸዉ?

https://p.dw.com/p/2dOqu
Saudi Arabien Gruppenfoto Präsident Trump und Führer der arabischen Staaten
ምስል Reuters/J. Ernst

የትራምፕ ጉብኝት እና መልዕክት

በ2014 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።) አዱኛ የሠገደችላቸዉ ቱጃር እንጂ ፕሬዝደንትም፤ ቢያንስ በይፋ ፖለቲከኛም አልነበሩ።ቲዊት ግን ያደርጉ ነበር።ዶናልድ ትራምፕ።«ለሳዑዲ አረቢያ እና ለብጤዎቻቸዉ ንገሯቸዉ» ፃፉ በቲዊተር ገፃቸዉ-ያኔ።«ለአስር ዓመት ነዳጅ ዘይት በነፃ ካልሰጡን፤ የነሱን የግል ቦይንግ 747 አዉሮፕላን አንጠብቅም።ክፈሉ።» ዘንድሮ እንደ ፕሬዝደንት ሳዑዲ አረቢያን ጎበኙ።እንደ ነጋዴ የ350 ቢሊዮን ዶላር ሸቀጥ ለመሸጥ ተስማሙ።«ገንዘቡ ለብዙ አሜሪካኖች ስራ ይፈጥራል አሉ» ቲዊት አደረጉ።ሥራ፤ ሥራ፤ሥራ።ሪያድ ላይ ለሰበሰቧቸዉ መሪዎች ግን መመሪያ ሰጡ አሸባሪዎችን መንጥሩ፤ ኢራንን ተዋጉ እያሉ።ለአሜሪካኖች ሥራ-ለሳዑዲዎች ጠመንጃ። የዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።

 ሪያድ ሁዳድ ላይ እንደ ጥንት የጦር አዛዦች ፈረስ ተጫነላቸዉ።የክብር ጦር አሠለፉ።እንደ ጦረኛ ጎረዴ ይዘዉ ጨፈሩ-አስጨሩም።የሪያዱ ወኪላችን ስለሺ ሽብሩ።ትንሽ ያክልበት።እርግጥ ነዉ ዶናልድ ትራምፕ ከሰወስት ዓመት በፊት እንደ ነጋዴ የተመኙት የሳዑዲ አረቢያ ነዳጅ ዘይትን በነፃ አላገኙም።ለአረቦች ከሚችሉት በላይ ጦር መሳሪያ አሸክመዉ ግን፤ ሐገራቸዉ መዛቅ የምትችለዉን ያክል ዶላር አንቆረቆሩላት።በፌስታ ጭፈራ የተጀመረዉ ጉብኝት በሸቀጥ-ሽያጭ ግዢ ቀጠለ።

ቅዳሜ በተፈረመዉ ሥምምነት መሠረት ሳዑዲ  አረቢያ ከዩናይትድ ስቴትስ የ350 ቢሊዮን ዶላር ሸቀጥ እና የጦር መሳሪያ ትሸምታለች።110 ቢሊዮኑ ለጦር መሳሪያ መግዢያ ነዉ የሚዉለዉ።ሳዑዲ አረቢያ ባንዴ  በጦር መሳሪያ ገዢነት ከነቻይና  ተርታ ተሰለፈች።ከዓለም ሰወስተኛ።ዩናይትድ ስቴትስ ለአንድ ሐገር ባንድ ጊዜ ይሕን ያሕል ዶላር የሚያወጣ ጦር መሳሪያ ስትሸጥ ያሁኑ የመጀመሪያዋ ነዉ።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከስምምነቱ መፈረም በኋላ እንዳሉት መንግሥታቸዉ ከሸቀጥ ይሁን ከጦር መሳሪያ ሽያጭ በሚያገኘዉ ገንዘብ ለዜጎቹ ሥራ ይፈጥራል።የፖለቲካ ተንታኝ የሱፍ ያሲን «ሚስጥሩ መመፃደቂያ ሲሆን» ይሉታል።                                   

USA Saudi Arabien Donald Trump mit König Salman bin Abdulazi
ምስል Imago/ZUMA Press/S. Craighead

ሳዑዲ አረቢያ በርግጥ ሐብታም ናት።ሰፊ፤ የ32 ሚሊዮኖች ሐገር።ግን ከዜጎቿ  አስራ-አምስት በመቶ ያክሉ ማይማን ናቸዉ።አብዛኞቹ የሐገሪቱ ሴቶች የቤት እመቤት ናቸዉ።ዘንድሮ ይፋ የሆነ ጥናት እንደሚያመለክተዉ መሥራት ከሚችለዉ ወንድ የሐገሪቱ ዜጋ ስድስት በመቶ ያክሉ ሥራ አጥ ነዉ።

ከ2011 ጀምሮ የተቀሰቀሰዉን ሕዝባዊ አመፅ ለማፈን፤ የሶሪያ ተቃዋሚዎችን ለመርዳት፤ ከ2015 ጀምሮ ደግሞ ለየመኑ ጦርነት በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እየከሰከሰች ነዉ።የወጪዉ መደራረብ ከነዳጅ ዘይት ዋጋ መቀነስ ጋር ተዳምሮ ሐገሪቱ አይታዉ ከማታዉቀዉ የምጣኔ ሐብት ቀዉስ ዶሏታል።

የሪያድ ገዢዎች ችግሩን ለማቃለል ያጭር ጊዜ መፍትሔ ያደረጉት «ሕገ ወጥ» ያሏቸዉን ችግረኛ የዉጪ ዜጎች ከሐገር ማባረር አንዱ ነዉ።ሕጋዊ በሚሏቸዉ ላይ ደግሞ ሚስት-ልጅ እያሉ የሚያስከፍሉትን ግብር መጨመር-ሁለተኛዉ።ቅዳሜ የተፈራረሙት ሥምምነት ለዜጎቻቸዉ የትምሕርት እና የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚረዳ አይደለም።በዉጪ ዜጎች ላይ የጫኑትን ችግርም አያቃልልም።ስለሺ ሽብሩ ሌላም አለ ባይ ነዉ።

Israel Ankunft Donald Trump
ምስል Reuters/A. Cohen

             

እና የጦር መሳሪያ በገፍ ሸመቱ።መሳሪያዉ፤ ከሐፓቺ ሔሊኮብተር መገጣጠሚያ እስከ ጨረር መራሽ ሚሳዬል የሚደርሱ ዘመናይ የጦር መሳሪዎችን ይጨምራል።መሳሪያዉ፤ የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሬክስ ቲለርሰን  በግልፅ እንዳሉት በኢራን ላይ ያነጣጥራል።«የመከላከያ መሳሪያ እና አገልግሎቱ የሳዑዲ አረቢያ እና የፋርስ ባሕረ-ሠላጤ አካባቢ ሐገራትን የረጅም ጊዜ ፀጥታን ያስከብራል።ይሕ በተለይ ከኢራን እና ከኢራን ጋር ከወገኑ ኃይላት የሚሰነዘሩ ሥጋቶችን ለመቋቋም ያለመ ነዉ።»

ከ1948 ጀምሮ የዓረብ አንደኛ ጠላት ተብላ የምትጠራዉ እስራኤል ነበረች።በ1950ዎቹ የያኔዉ የኢራን ንጉስ (ሻሕ) መሐመድ ሬዛ-ፓሕሌቪ ለእስራኤል የመንግሥትነት ዕዉቅና መስጠታቸዉ ከሁለቱ ትላልቅ  ሙስሊም ሐገራት የልዩነት ምክንያቶች አንዱ ተደርጎ ነበር።ዛሬ-ተገላቢጦሹ ነዉ-ሐቁ።ንጉስ ሠልማን በቀደም እንዳሉት የሳዑዲ አረቢያ አንደኛ ጠላት እስራኤል ሳትሆን ኢራን ናት።

የቀድሞዉ የሳዑዲ አረቢያ ንጉስ ፈይሰል በ1966 ቴሕራንን በጎበኙ ማግሥት የዓለም ሙስሊሞችን በማሕበራት ማደራጀት ሲጀምሩ ዋና ደጋፊ፤ አማካሪያቸዉም የኢራኑ አቻቸዉ መሐመድ ሬዛ ፓሕሌቪ ነበሩ።ፈይሰል በኢራኑ ንጉስ ድጋፍ ትብብር የዓለም እስላማዊ ጉባኤ ድርጅት፤ የእስልምና ዓለም ሊግ፤ እስላማዊ ጉባኤ የተሰኙትን ዓለም አቀፍ ተቋምት በተከታታይ መሠረቱ።

ፕሬዝደንት ትራምፕ፤ በኢራኖች ትብብር የተመሠረቱት ማሕበራት የሚያስተናብሯቸዉን የሐምሳ-አምስት ሙስሊም ሐገራት መሪዎች እና ባለሥልጣናትን በቀደም ሪያድ ላይ ሰብስበዉ ኢራንን አስወገዙ፤ በአሸባሪነት ወነጀሉም።«ለብዙ አስርታት ኢራን የሐምኖታዊ ሐራጥቃ ግጭቶችን እና የሽብርን እሳት አቀጣጥላለች።ጅምላ ግድያን በግልፅ የሚናገር፤ እስራኤልን ለማጥፋት የሚዝት፤ ሞት ለአሜሪካ እያለ የሚፎክር መንግሥት ነዉ።እዚሕ አዳሽ ዉስጥ ለተሰባሰባችሁን በርካታ መሪዎች እና ሐገራት ጥፋት የሚመኝ ነዉ።ከኢራን የጥፋት ጣልቃ ገብነት አንዱ የሶሪያ ጥፋት መሆኑን አይታችኋል።»

Karikatur Trumps Reisen nach Saudi Arabien von Sergey Elkin

 

ትራም ሪያድ ላይ መሳሪያ ሲቸበችቡ፤ ሙስሊም ሐገራትን በሙስሊማይቱ ኢራን ላይ ሲያሳድሙ ካቡል አፍቃኒስታን ዉስጥ አዉሮጳዉያን ይገደሉ፤ ይቆስሉ፤ የታደሉት ይሸሹ ነበር።ከሶሪያ እስከ ሊቢያ፤ ከሶማሊያ እስከ ፍልስጤም፤ ከየመን እስከ ኢራቅ መቶዎች ይገደሉ፤ ሺዎች ይሰደዱ፤ ሚሊዮኖች ይራቡ ነበር።ዛሬም ያዉ ነዉ።ምናልባት ነገም።

ለአፍቃኒስታን ጥፋት አሸባሪዎች ወይም ታሊባኖች ተጠያቂዎች ናቸዉ።አስራ-ሰባተኛ ዓመቱን የደፈነዉን ጦርነት ለኳሽ-ቆስቋሻ ግን አሜሪካ ናት።ለፍልስጤም፤ ሶማሊያ፤ ለኢራቅ፤ ለሶሪያ፤ለሊቢያ ይሁን ለየመን መጥፋት የየሐገሩ ታጣቂዎች፤ ዓለም አቀፍ አሸባሪዎች ወይም አሸባሪዎች ተጠያቂዎች ናቸዉ።በሁሉም ግጭት ጦርነቶች ግን የዩናይትድ ስቴትስና የተባባሪዎችዋ ተሳትፎ አሳንሶ መመልከት በርግጥ ክሕደት ነዉ።ሸፍጥ።

                         

አሁንም ትራምፕ ሰላም እናዉርድ አላሉም።ተፋላሚዎችን እናስታርቅ አላሉም።ሪያድ ለሰበሰቧቸዉ የሙስሊም ሐገራት መሪዎች የመጣሁት እናንተን ላስተምር፤ ገለፃ ወይም ሌክቸር ላደርግ አይደለም ማለታቸዉ ግን ሐቅ ነዉ።በርግጥም ገለፃ አላደረጉም።ኢራንን አዉጉዙ፤ አሸባሪዎችን አጥፉ እያሉ አዘዙ እንጂ።«መጪዉ ዘመን የተሻለ የሚሆነዉ ሐገሮቻችሁ አሸባሪዎችን ሥታጠፉ ብቻ ነዉ።ፅንፈኞችን ስታጠፉ ነዉ።አጥፏቸዉ።ከቤተ-አምልኳችሁ አስወጧቸዉ።ከማሕበረሰባችሁ አስወጧቸዉ።ከቅድስ ስፍራዎቻችሁ አስወጧቸዉ።ከምደረ-ገፅ አጥፏቸዉ።»

ሰማኒያ ዓመት ግድም ያስቆጠረዉን የአረብ-እስራኤሎች ጠብ ለማርገብ፤ ትራምፕ፤ ከእሳቸዉ በፊት የተፈራረቁት የአሜሪካ መሪዎች የሚሉትን ያክል እንኳን አላሉም።ዛሬ ግን የእስራኤልና የፍልስጤምን መሪዎች ያነጋግራሉ ነዉ የተባለዉ።አንድ የየሩሳሌም ነዋሪ እንዳሉት ትራም የእስራኤል እና የፍልስጤም መሪዎችን ማነጋገራቸዉ የሁለቱን ወገኞች ጠብ ለማርገብ የሚፈይደዉ የለም።ለራሳቸዉ ለትራምፕ ግን ጥሩ ጥቅም አለዉ።

«የመካከለኛዉ ምሥራቅ ግጭትን ከልባቸዉ የሚከታተሉ በማስመሰል ሐገር ዉስጥ የገጠማቸዉን ፖለቲካዊ ቀዉስ ለጊዜዉ ያዘናጉበታል።(ግጭቱን) ማስወግድ ግን አይችሉም።»ኢራን ለዩናይትድ ስቴትስ እና ለእስራኤል፤ አሁን ደግሞ ለሳዑዲ አረቢያ አሸባሪዎን የምትረዳ፤ የምታዘምት መጥፋት-ያለባት የጥፋተኞች ሐገር ናት።ለቴሕራኖች ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ትልቅ ሰይጣን፤ እስራኤል መጥፎ-ጠላት፤ ሳዑዲ አረቢያ ደግሞ ያሸባሪዎች መፍለቂያ ናት።

Israel Ankunft Donald Trump
ምስል Reuters/A. Cohen

ትራምፕ ለሳዑዲ አረቢያ የጦር መሳሪያ ከሸጡ በኋላ አሸባሪዎችን አጥፉ-እናጥፋ እያሉ መዛታቸዉን አንድ የቴሕራን አስተያየት ሰጪ የቃል-ድርጊት ተቃርኖ አድርጎ ነዉ ያየዉ-ስለሺ እንደነገረን።አሁን ኢራንን ለመምታት የ110 ቢሊዮን ዶላር ጦር መሳሪያ የሸመተችዉ ሳዑዲ አረቢያ ድሮም ቢሆን በየዓመቱ 82 ቢሊዮን ዶላር ለጦር መሳሪያ ትከሰክሳለች።ኢራን 25 ቢሊዮን።ሳዑዲ አረቢያ አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢ 745 ቢሊዮን ነዉ።የኢራን 566 ቢሊዮን።የኢራን ሕዝብ 81 ሚሊዮን ነዉ፤ ሳዑዲ አረቢያ 32 ሚሊዮን።ሪያድ-ዋሽግተኖች ብብት ስር ተወሽቃ፤ ቴሕራን-ሞስኮን ተተግና ይዛዛታሉ።ባግዳድን ይሆኑ-ይሆን? ማናቸዉ?

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ