1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትራምፕ እርምጃና የቀዳሚዎቻቸዉ አብነት

ሰኞ፣ የካቲት 2 2012

የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አዉራሽ፣ ያመራር ሥልት አስኮራጃቸዉን ኒክሰንን ሳይሆን ጆንሰንን ወይም ክሊንተንን ሆኑ።ትራምፕ  ነፃ የመዉጣታቸዉን ድል፣ደስታ፣ ፌስታን ግን እንደ ጆንሰን ለእርጋታ፣ እንደ ክሊንተን ለምስጋና፣ ለዕርቀ ሠላም- ይቅርታ ሳይሆን ለልቅ ስድብ፣ማላጋጥ፣ ማንጓጠጥ ተጠቀሙበት።

https://p.dw.com/p/3XZPN
USA Präsident Trump Statement Amtsenhebungsverfahren
ምስል Reuters/J. Roberts

የትራምፕ ድል፣የብቀላ ጅምር እና የቀዳሚዎቻቸዉ አብነት


የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በተያዘባቸዉ የወንጀል ጭብጥ እንዳይቀጡ (ስልጣናቸዉን እንዳይለቁ) የሐገሪቱ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት) ባለፈዉ ሳምንት ሮብ ወሰነ።ነፃ ወጡ።የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አዉራሽ፣ ያመራር ሥልት አስኮራጃቸዉን ኒክሰንን ሳይሆን ጆንሰንን ወይም ክሊንተንን ሆኑ።ትራምፕ  ነፃ የመዉጣታቸዉን ድል፣ደስታ፣ ፌስታን ግን እንደ ጆንሰን ለእርጋታ፣ እንደ ክሊንተን ለምስጋና፣ ለዕርቀ ሠላም- ይቅርታ ሳይሆን ለልቅ ስድብ፣ማላጋጥ፣ ማንጓጠጥ ተጠቀሙበት። የየኒከሰንን ወግ አዝባቂ የፖለቲካ መርሕ በሚያቀነቅኑ የሪፐብሊካን ሴናተሮች ድጋፍ  «ከጡረታ» የዳነ ትልቅ ስልጣናቸዉን ለመግባባት ሳይሆን ለብቀላ፣ለአብነታዊ አመራር ሳይሆን-ለቂም መበቀያ ማዋላቸዉ ነዉ-እንደ ትልቅ ሐገር መሪ ምንም፣ ማንንም ያለመሆናቸዉ ድቀት።ከወራት በፊት ጠይቀን ነበር «ትራምፕ እንደማን ይሆኑ-ይሆን» ብለን።አሁን ተመልሷል።ላፍታ አብረን እንቃኘዉ።
የዩናይትድ ስቴትስን ደቡባዊ ግዛቶች ለመገንጠል ይዋጉ የነበሩትን ኃይላትን ድል አድርገዉ የዛሬዉን ልዕለ ኃያል ሐገር አንድነት በማስጠበቃቸዉ እንደ ጀግና፣ብልሕ፣ አርቆ አስተዋይ መሪ የሚደነቁት ፕሬዝደንት አብረሐም ሊንከን በሰዉ እጅ ተገደሉ።ሚያዚያ 14 1865 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።የሊንከን ድንገት መገደል አንድነትን ለሚፈልገዉ ለአብዛኛዉ አሜሪካዊ ታላቅ ድንጋጤ፣ ለፖለቲከኞቿ  የመከፋፈል ሥጋት ነበር።
የታላቁን መሪ ሥልጣን ለተረከቡት ለእስከያኔዉ ምክትል ፕሬዝደንት ለአንድሪዉ ጆንሰን ደግሞ ችግሩ ረቂቅ፣ ኃላፊነቱ ድርብ፣ አሰራሩ ዉስብስብ ነበር።ጆንሰን  ከርስበርስ ጦርነት በቅጡ ያላገገመችዉን ሐገር አንድነት ለማስጠበቅ፣ በድንጋጤ፣ ሥጋት የሚቆዝመዉን ሕዝብና ፖለቲከኛን ማረጋጋቱ ከሁሉም በላይ ሊንከንን የመተካት ብቃታቸዉን ማረጋገጡ፣ የአሜሪካ ታሪክ አጥኚዎች እንደሚሉት በርግጥም ፈታኝ ነበር።

ጆንሰን ፈታኙን  ኃላፊነት ለመወጣት ሲባትሉ ያኔ ከወግ አጥባቂ ፖለቲከኞችና አልፎ አልፎም ከጋዜጣ አታሚ ድርጅቶች ጋር ይጋጩ ገቡ። ከወግ አጥባቂ እንደራሴዎች ጋር የገጠሙት አተካራ በሁለተኛ ዓመቱ ንሮ በ1868 የሪፐብሊካን ፓርቲ እንደራሴዎች የሚበዙበት በሐገሪቱ ሕግ መምሪያ ምክር ቤት በ11 የወንጀል ጭብጦች ተከሰሱ-IMPEACH ተደረጉ።በሕግ መምሪያዉ ምክር ቤት በመከሰስ፣ ጥፈተኛ ተብሎ ሲወሰንባቸዉም የመጀመሪያዉ  የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆኑ።
የጆንሰን የፖለቲካ ፓርቲ እንደራሴዎች የሚበዙበት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት ግን) ፕሬዝደንቱ በተያዘባቸዉ የወንጀል ጭብጥ ተጠያቂ እንዳይሆኑ ወይም ስልጣን እንዳይለቁ በጠባብ የድምፅ ልዩነት ወሰነ።
ጆንሰን አለቃቸዉ አብረሕም ሊንከን በተገደሉበት ዕለት ከመገደል ያመለጡት፣ የተላከባቸዉ ገዳይ ሰክሮ እንቅልፍ ስለጣለዉ ለጥቂት ነበር።ሚያዚያ 14 1865።በሰወስተኛ ዓመቱ በአንድ የድምፅ ልዩነት ከስልጣን ከመባረር ለጥቂት ተረፉ።ጆንሰን ከመከሳሳቸዉ በፊት፣ በክሱ ሒደትም ሆነ ነፃ ከወጡ በኋላ «ደካማ» የሚሏቸዉ ጋዜጠኞችን ወቀሰና ትችትም ሆነ የተቀናቃኝ የሪፐብሊካን ፖለቲከኞችን ዉንጀላም እየመረራቸዉ ግን በጥንቃቄ ነበር ያለፉት።
ጆንሰን በተከሰሱ በመቶኛዉ ዓመት ግድም በወንጀል የተጠረጠሩት ሪፐብሊካኑ ፕሬዝደንት ሪቻርድ ኒክሰን ልክ እንደ ጆንሰን ሁሉ ባለስልጣን አባረዋል።የጋዜጠኞች ወቀሳና ትችትን ግን እንደ ጆንሰን በዘዴ ለማለፍ ትዕግስቱም፣ ዘዴዉም አልነበራቸዉም።ምናልባት ጊዜዉም አልረዳቸዉም።ከመገናኛ ዘዴዎች ጋር መነታረክ የጀመሩት ገና በወንጀል ሳይጠረጠሩ ነበር።
የሚያዉቁ እንደሚሉት ፕሬዝደንት ኒክሰን መገናኛ ዘዴ ወይም «ፕሬስ ጠላት» ነዉ ይሉም ይነበር ።
«ፕሬስ ጠላት ነዉ።ፕሬስ ጠላት ነዉ።ፕሬስ ጠላት ነዉ።»
ፕሬስ ለሳቸዉ በርግጥ ጠላት ባይሆን እንኳን ወዳጅ አልነበረም።ፕሬዝደንት ኒክሰን ስልጣን ከለቀቁ ከ43 ዓመታት በኋላ እንደ ኒክሰን ሁሉ በሪፐብሊካን ፓርቲ ካርድ ለፕሬዝደንትነት የበቁት ቱጃሩ ነጋዴ ዶናልድ ትራምፕ ገና ስልጣን እንደያዙ የሐገራቸዉ መገናኛ ዘዴዎችን ዉሸታሞች እያሉ ከኒክሰን በከፋ መንገድ ያበሻቅጡ ገቡ።2017።
«ከጥቂት ቀናት በፊት የሐሰት ዜና የሕዝብ ጠላቶች ናቸዉ ብዬ ነበር።ምክንያቱም ምንጭ የላቸዉም።»
በ1972 ወጣቱ የዋሽግተን ፖስት ዘጋቢ  ቦብ ዉድዋርድ ከባልደረባዉ ካርል ቤርንስታይን ጋር በመሆን ለንባብ ያበቁት ታሪክ «የወተርጌት ቅሌት» የተባለዉን ወንጀል ለሕዝብ ያጋለጠ የመጀመሪያዉ ዘገባ ነበር።ዉድዋርድ እና ቤርስታይን ያጋለጡት ሐቅ አጉዞ አጉዞ በሕግ-የሰለጠኑ፣ በፖለቲካ ዲፕሎማሲ 30 ዓመት የበሰሉትን አንጋፋ ፕሬዝደንት ከስልጣን አሽቀንጥሮ ጣለ።ነሐሴ 1974።
«ይሁንና እንደ ፕሬዝደንት የአሜሪካ ፍላጎትን ማስቀደም አለብኝ።አሜሪካ የሙሉ ጊዜ ፕሬዝደንት እና የሙሉ ጊዜ ምክር ቤት ያስፈልጋታል።---ሥለዚሕ ከነገ እኩለ ቀን ጀምሮ ፕሬዝደንታዊ ስልጣኔን እለቃለሁ።»
ኒከሰን ሥልጣን የለቀቁት የሐገሪቱ  ምር ክር ቤት በተያዘባቸዉ የወንጀል ጭብጥ በጥፋተኝነት ከመወሰኑ በፊት ነበር።በሳቸዉ አነጋገር የአሜሪካን ጥቅም ከሥልጣናቸዉም፤ ከሁሉም  በላይ በማስቀደም።
እንደ ኒክሰን ሁሉ «አሜሪካ ትቅደም» ይላሉ ዶናልድ ትራምፕ።የኒክሰንን አካዳሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እዉቀት ግን ሊኖራቸዉ ቀርቶ ኒክሰን እንዳላቸዉ ማወቃቸዉም አጠራጣሪ ነዉ።እንደ ኒክሰን ሁሉ የሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለዉ ተወዳደሩ፣ ከኒክሰን በላይ ወደ ቀኝ ተስፈንጥረዉ ፉክክር ሲጀምሩ ፖለቲካን አቀወቁ፣ አሸነፉ።የኒክሰንን ወንበር ያዙ።በቃ።This is America እንዲሉ አሜሪካኖች።
አንዳዴ አዉራጣታቸዉን እንደ ድል ምልክት መቀሰሩንም ከኒክሰን ወርሰዋል።የኒክሰንን ቅሌት አነፍንፎ፣ ያጋለጠዉን ዋሽግተን ፖስት ጋዜጣን ዶናልድ ትራምፕ ከምረጡኝ ዘመቻ ጊዚያቸዉ ጀምረዉ በግልፅ ይጠሉት ነበር። የዋሽግተን ፖስት ዘጋቢዎችን ትራምፕ በሚመሩት ዝግጅት፣ ንግግርና ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳይገኙ አገዱ።2016።ምክንያት
«ከዋሽግተን ፖስት ዘጋቢዎች በየሰዓቱ የስልክ ጥሪ ይደርሰናል።የማይረባ ጥያቄ ይጠይቁናል።ምንም አይነት መረጃ የላቸዉም።የማይረባ መረጃን ይገጣጥሙና መፅሐፍ ያሳትማሉ።መፅሐፉ ሙሉ በሙሉ በዉሸት የተሞላ ነዉ።ምክንያቱም ታሪኩ ሁሉ የተሳሳተ ነዉና።»
ባለፈዉ ሳምንት የእሳቸዉ የፖለቲካ ፓርቲ የሪፐብሊካን እንደራሴዎች የሚቆጣጠሩት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት) በተያዘባቸዉ የወንጀል ጭብጥ እንዳይወነጀሉ ወይም ስልጣን እንዳይለቁ ሲወስንላቸዉ ለድል ብስራት አደባባይ ይዘዉ የወጡት ግን ያንን ጋዜጣ ነበር።ዋሽግተን ፖስትን።
«የመጨረሻዉ ዉጤት ይኽ ነዉ።»አሉ የዋሽግተን ፓስታ ጋዜጣን ለተሰበሰቡት ደጋፊዎቻቸዉ እያሳዩ።ጋዜጣዉ በመጀመሪያ ገፁ የትራምፕን ትልቅ ፎቶ ለጥፏል።«ነፃ ተባሉ» ይላል ከትልቁ ፎቶ ግራፍ አናት ላይ በትላልቁ የተፃፈዉ ርዕሰ-ዜና።
«ይሕንን እቤታችን ይዘን እንገባለን።ፍቅሬ፤ ምናልባት በክብር መስተዋት ዉስጥ እናስቀምጠዋለን።» 
ቀጠሉ ፕሬዝደንቱ ጋዜጣዉን ለባለቤታቸዉ እየሰጡ።«ዋሽግተን ፖስት ላይ ያየሁት ብቸኛዉ ጥሩ የዜና አርዕስተ ዜና-ነዉ።»
ዶናልድ ትራምፕ እንደ ፖለቲካ መርሕ አዉራሻቸዉ፣ ወይም እንደ አመራር ስልት አስኮራጂያቸዉ ጋጠኞችን ለማኪኪያስ አልሰነፉም።አሜሪካ ፈርስስት ማለቱም አልቀረባቸዉም።የኒክሰን እዉቀት እንደሌላቸዉ ሁሉ ከመከሰሳቸዉ በፊት ስልጣን ለመልቀቅ የኒክሰንን ድፍረት አላገኙም።
ክሱ ከሕግ መምሪያዉ ምክር ቤት አልፎ ሕግ መወሰኛዉ ምክር ቤት እስኪደርስ ድረስ እንደ ዴሞክራቶቹ ጆንሰን እና ክሊንተን ጠበቁ።ሪፐብሊካኑንን ኒክሰን ሳይሆን ዴሞክራቶቹን  መሰሉ።
ሞኒካ ልዊንስኪ ከተባለች ተለማማጅ ኮረዳ ጋር ማግጠዋል በሚል በ1998 ማብቂያ የሕግ መምሪያዉ ምክር ቤት ጥፈተኛ ብሎ የወሰነባቸዉ ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተን ከመከሰሳቸዉ በፊት፣ በክሱ ሒደት፣ ከዉሳኔዉ በኋላም ከመገናኛ ዘዴዎች የሚደርስባቸዉ ትችትና ወቀሳን ልክ እንደ ጆንሰን በዘዴ አለፉት።
ዲሞክራቶች የሚበዙበት የሕግ መወሰኛዉ ምክር ቤት ከተወነጀሉበት ነፃ ሲያደርጋቸዉ ወይም ሥልጣን እንዳይለቁ ሲወስንላቸዉ የትልቂቱ ሐገር ትልቅ መሪ ከትልቁ ቤተ-መንግሥታቸዉ፣ ሮዝ ጋርደን ወደተባለዉ ቅጥር ግቢ ወጡ።እንደ ፕሬዝደንቶች ወግ እምቢልታ፣ ጡሩባ አልተነፋም።መዝሙር አልተዘመረም።ከጋዜጠኞች ሌላ የተጋበዘ እንግዳ፣ ያጀባቸዉ ሹምም የለም።ወጡ።አሉም።
«አሁን ሴኔቱ ይሕን ሒደት ከፍፃሜዉ በማድረስ ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ተወጥቷል።ለአሜሪካ ሕዝብ በድጋሚ ማለት የምፈልገዉ ባለፉት ዓመታት አሜሪካ ለገጠማት ነገር ሁሉ በጣም አዝኛለሁ፥ይቅርታ እንድታደርጉልኝ ነዉ።አሜሪካዉያንን የምጠይቀዉ፣ ይሕ መደረግ ያለበትም ነዉ፣ አሁን ለሁሉም አሜሪካዉያን ይሕ የእርቅ እና የተሐድሶ ጊዜ ነዉ።»
እንደ ትልቅ ሐገር ጨዋ መሪ ይቅርታ ጠየቁ።ዝቅ ብለዉ፣ ከፍ ያሉ መሆናቸዉን አረጋገጡ።የካቲት 12 1999።
ከ21 ዓመት በኋላ ዘንድሮም የካቲት ነበር።የካቲት ሰባት።ፕሬዝደንት ትራምፕ ለድል ብስራት ጡርምባ አስነፉ።አዘመሩ።አስጨበጨቡ።የስድብ ናዳቸዉን ያወርዱት ያዙም።

Bildkombo Gordon Sondland und Alexander Vindman
USA Amtsenthebungsverfahren | Abstimmung
ምስል AFP/US Senate TV
Bildkombo Johnson Nixon und Clinton
Bildkombo Johnson Clinton und Trump

«በዚሕ ሒደት ሰወስት ዓመት አስቆጥረናል።ሰይጣናዊ ነበር።ሙሰኛ ነበር።ቁሻሾች አሉ።ምስጢር አሹላኪዎች አሉ።ይሕ በሌላ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ላይ መድረስ የለበትም።ሌሎቹ ፕሬዝደንቶች ጉዳዩን እንዴት ይይዙት እንደነበር አላዉቅም።የተወሰኑ አይችሉትም ይላሉ።---በጣም አሳፋሪ ነዉ።ይሕ ነገር ፕሬዝደንት ኦባማ ላይ ደርሶ ቢሆን ኖሮ ብዙ ሰዎች ለብዙ አመታት ይታሰሩ ነበር።»
በስድብ እርግማን ዉግዘቱ ማግስት መስክረዉብኛል ያሏቸዉን ባለስልጣናት ከስልጣን ማበረሩን ቀጠሉ።ቀዳሚዎቹ በአዉሮጳ ሕብረት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ጎርደን ሶንደላንድ እና በዋይት ሐዉስ የፀጥታ ጉዳይ ባለስልጣን ሌትናት ኮሎኔል አሌክሳንደር ቪንድማን ናቸዉ።ቀጣዩን አናዉቅም።የሚታወቀዉ ትራምፕ  ሲሻቸዉ እንደ ኒክሰን፣ሲመቻቸዉ እንደ ክሊንተን እና ጆንሰን ከሁሉም በላይ እንደ ነጋዴነታቸዉ ልዕለ ኃያሊቱን ሐገር በጣም ሲያስ እከመጪዉ ጥር ይዘዉራሉ። ሲረዝም ለአምስት ዓመት።

ነጋሽ መሐመድ 

ሸዋዬ ለገሰ