1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻይናና ታይዋን ፕሬዝዳንቶች ውይይት

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 27 2008

የቻይና እና ታይዋን ፕሬዝዳንቶች ከበርካታ አመታት እሰጥ አገባ በኋላ ተገናኙ። የፕሬዝዳንቶቹ ግንኙነት ሁለቱ አገሮች ከተለያዩበት የጎርጎሮሳዊው 1949 ዓ.ም. በኋላ የመጀመሪያው በመሆኑ ታሪካዊ ነው ተብሏል።

https://p.dw.com/p/1H1gr
Taiwan Singapur Treffen Ma Ying-jeou und Xi Jinping
ምስል picture-alliance/AP Photo/W. Maye-E

የቻይናው ዢ ዢንፒንግ እና የታይዋኑ ማ ይንግ ዢው በሲንጋፖር ተገናኝተው እጅ የተጨባበጡበት ቅጽበት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ፈጽሞ የሚታሰብም አልነበረም።የቻይናው ፕሬዝዳንት «አጥንቶቻችን ቢሰበሩም በስጋ የምንገናኝ ወንድማማቾች ነን። ከውሃ የወፈረ ደምም ያዛምደናል።» ሲሉ ለታይዋኑ አቻቸው ነግረዋቸዋል። ቻይናና ታይዋን አንዳቸው ለሌላው በይፋ እውቅና ባለመስጠታቸው ታሪካዊ በተባለው የፕሬዝዳንቶች ውይይት አንዳችም ስምምነት ይፋ አልተደረገም። የታይዋኑ ፕሬዝዳንት ከቻይናው አቻቸው ጋር ያደረጉት ግንኙነትና ለአንድ ሰዓት የዘለቀ ውይይት ግን በተቃዋሚዎቻቸው ዘንድ ነቀፌታ እንዲሰነዘርባቸው አድርጓል። «ውጥረት የነገሰበት የስድስት አስርት አመታት ግንኙነት አሳልፈናል።» ያሉት የታይዋኑ ፕሬዝዳንት አሁን ግን ወደ ንግግርና ውይይት ሊቀየር እንደሚገባ አሳስበዋል።በመጪው ጥር በሚካሄደው ምርጫ የፕሬዝዳንቱ ፓርቲ ሽንፈት ሊገጥመው ይችላል የሚል ቅድመ-ትንበያ ከወደ ታይዋን በመሰማቱ የሁለቱ አገሮች አዲስ ግንኙነት ዘላቂ ለመሆኑ ጥርጣሬ እንዳላቸው ተንታኞች ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ