1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻይና ኩባንያዎች መስፋፋት በጀርመን

ረቡዕ፣ መስከረም 24 2004

ቀድሞ የጀርመን ኩባንያዎች ነበሩ በቻይና በመስፈር የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት የሚየደርጉት። ዛሬ ግን ጊዜው ተለውጦ ወደ አውሮፓ የሚመጡት የቻይና ኩባንያዎች ቁጥር በየጊዜው እያደገ በመሄድ ላይ ይገኛል።

https://p.dw.com/p/Rp1b

የቻይና መዋዕለ-ነዋይ አቅራቢዎች ቁጥር በተለይም በዚህ በጀርመን በሰፊው እየጨመረ ሲሆን ማዕከላዊ አውሮፓይቱ አገር በሩቅ ምሥራቅ ኩባንያዎች ዘንድ ይበልጥ አመቺ ሆና መታየቷ አልቀረም። በተፋጠነ ዕድገት ስትገሰግስ የቆየችው ቻይና የጥሬ ሃብት ፍላጎቷን ለማሟላትም ሆነ በገፍ የምታመርተውን ሸቀጥ የምታራግፍበት ገበያ በመሻት በተለይ አዳጊ እየተባለ የሚጠራውን ዓለም ከዳር እስከ ዳር ማዳረሷ ለማንም የተሰወረ ነገር አይደለም። አሁን ደግሞ ዓለም ከቅርቡ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ተጽዕኖ ገና ጨርሶ ባላገገመት ወቅት አብዛኛውን የገንዘብ ተቀማጭ የያዘችው የቻይና ሚና በአውሮፓና በአሜሪካም እየጠነከረ በመሄድ ላይ ነው። ቻይና ዛሬ ችግር በተፈጠረበት ቦታ ሁሉ ለመርዳት ዝግጁ ነኝ፤ ገንዘብ ላቅርብ ባይ ናት።
እርግጥ ይህ ያላንዳች ቅድመ-ግዴታ አይደለም። ቻይና በኤውሮው ምንዛሪ ሃገራት በኤውሮ-ዞን ውስጥ በበጀት ቀውስ የተወጠረችውን ግሪክን በገንዘብ በመርዳት፤ ወይም እንበል የመንግሥቱን የተወሰነ ዕዳ በመግዛት በልዋጩ ወደብ ተቆጣጥራለች። በሚቀጥለው ዓመት የአውሮፓን እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ከኡክራኒያ ጋር በምታስተናግደው በፖላንድ ትልቁን አውራ-ጎዳና የሚያንጹት ዛሬ የታወቁት የአውሮፓ ኩባንያዎች ሣይሆን የቻይና ነው። ይህ እስከ ቅርቡ ሊታሰብ የሚችል ነገር አልነበረም።

ዛሬ በጀርመን መቆናጠጥ ከያዙት የቻይና ኩባንያዎች መካከል ሁዋዋይ፣ ሃየር፣ ዪንግሊ ወይም ሣኒ የተሰኙት ይገኙበታል። እነዚህ ኩባንያዎች እርግጥ በውጭው ዓለም ገና ብዙም የታወቁ አይደሉም። ሆኖም በዚህ በጀርመን በታላቋ ፌደራል ክፍለ-ሐገር በኖርድራይን-ዌስትፋሊያ የሰፈሩት የቻይና ኩባንያዎች 700 ገደማ ይጠጋሉ። በመሠረቱ ይሄው ክፍለ-ሐገር በተለይም ከ 60ኛዎቹ ዓመታት ወዲህ የጃፓን ኩባንያዎች ዋነኛ ማዕከል ሆኖ ነው የኖረው። በአካባቢው ከ 500 የሚበልጡ የጃፓን የኤሌክትሮኒክ፣ የአውቶሞቢል ወዘተ. ኩባንያዎች ሰፍረው የቆዩ ሲሆን ለሰላሣ ሺህ ሰዎች የሥራ መስክ የከፈቱም ናቸው።
እንግዲህ አሁን ከኋላ የመጣችው ቻይና ምናልባትም ብርቱ ተፎካካሪ ልትሆንባቸው ነው። የሆነው ሆኖ የሩቅ ምሥራቁ ኩባንያዎች ጀርመንን መስፈሪያ አድርገው መሻታቸው ያለ ምክንያት አይደለም። አገሪቱ እጅግ የተስፋፋ መዋቅር ሲኖራት ማዕከላዊ አቀማመጧም የአውሮፓ መገናኛ ዕምብርት ያደርጋታል። በዚህ በኖርድራይን-ዌስትፋሊያ ክፍለ-ሐገር የውጭ ኩባንያዎችን በሰፈራ ጥረት የሚያማክረው NRW Invest የተሰኘ የጀርመን ተቋም ሥራ አስኪያጅ ፔትራ ቫስነር እንደሚሉት በዚሁ የተነሣም ዕድገቱ ጎልቶ የሚታይ ነው።

“መዋዕለ-ነዋይ አቅርቦቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስደናቂ እየሆነ መሄዱን እንታዘባለን። ማለት ጥራቱም እየጨመረ ነው። በመጀመሪያ በውክልና የተወሰኑ የነበሩት ኩባንያዎች ዛሬ እየተስፋፉና በምርት ላይ ሣይቀር በሰፊው መዋዕለ-ነዋይ እያደረጉ ይገኛሉ”

በቅርቡ በዚህ በጀርመን በሁለቱ ሃገራት ኩባንያዎች ንግግር ላይ ተገኝተው የነበሩት የቻይና ምክትል የንግድ ሚኒስትር ቼን ጂያንም በግንኙነቱ መስፋፋት እርካታ የተሰማቸው መሆኑን ነው የገለጹት። የግንኙነቱ ሚዛን እየተስተካከለ እንደሚሄድም ያምናሉ።

“እኛ ገና በጅምር ላይ ነን ያለነው። ጀርመን በአንጻሩ ቻይና ውስጥ የምታደርገው መዋዕለ-ነዋይ በወቅቱ 1,8 ሚሊያርድ ኤውሮ ይደርሳል። የቻይና ግን በ 900 ሚሊዮን የተወሰነ ነው። እርግጥ ይህ ወደፊት የሚያድግ ይሆናል”

እርግጥ ግንኙነቱ ጥርጣሬና ባሕላዊ ልዩነት የሚፈጠረው ችግር የተለየውም አይደለም። የቻይና መዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች ከጀርመን ኩባንያዎች በሚገናኙበት ጊዜ የቋንቋ ችግር ለምሳሌ አዘውትሮ መሰናክል መሆኑ አልቀረም። አብዛኞቹ የቻይና ኩባንያ ወኪሎች እንግሊዝኛ ቋንቋን በሚገባ የሚያውቁ አይደሉም፤ የጀርመናውያኑ የቻይና ቋንቋ ችሎታ ደግሞ እንዲያው ባይነሣ ነው የሚሻለው። ከዚሁ የቋንቋ ችግር ባሻገር የባሕላዊ ልዩነት ችግርም አለ። በጀርመናውያኑ በኩል ዕውቀት እንዳይሻገርና የሥራ ቦታዎች እየጠፉ እንዳይሄዱ ያለው ፍርሃቻም ትልቅ ነው።

“በቻይና መዋዕለ ነዋይ ባለቤቶች ላይ ለረጅም ጊዜ ቁጥብነት ሰፍኖ ቆይቷል። በተለይም የአገሪቱን ኩባንያዎች በቻይና ኩባንያዎች መያዝ በተመለከተ! ይሁንና በዚሁ ረገድ ስኬታማ ምሳሌዎችም በማየታችን በወቅቱ ስሜታችን የተረጋጋ እየሆነ ነው”

ለምሳሌ SGSB በመባል የሚታወቀው የቻይና መዋዕለ-ነዋይ አቅራቢ ስብስብ ቡድን ከስድሥት ዓመታት በፊት የጀርመኑን የኢንዱስትሪ ስፌት መኪናዎች አምራቹን የዱር-ኮፕ አድለር አክሢዮን ማሕበርን 95 በመቶ ድርሻ መጠቅለሉ ይታወሣል። የአክሢዮን ማሕበሩ ነገረ-ፈጅ ራይንሃርድ ኮትማን መለስ ብለው እንደሚያስታውሱት በጊዜው በሻንግሃዩ ታላቅ ባለ አክሢዮን ላይ ከኩባንያውና ከባንኮች አኳያ የተፈጠረው የአመኔታ እጦትና ጥርጣሬ ቀላል አልነበረም።

“እኔ በበኩሌ ያሰብኩት ለውጡ በዱር-ኮፕ አድለር ኩባንያ ታሪክ ውስጥ ስር-ነቀል እንደሆነ አድርጌ ነበር። በኩባንያው ውስጥ ሰላሣ ዓመታት ከቆየሁ በኋላ የቻይና ትልቅ ባለ አክሢዮን በመምጣቱ በመጀመሪያ ደረጃ ስለሚከተለው ሁኔታ ጉጉት ሳያድርብኝም አልቀረም”

ኩባንያው ቀደም ሲል ከአንድ የደቡብ ጀርመን ድርጅት ጋር ለአርባ ዓመታት ሲተባበር ነበር የቆየው። እናም በመጀመሪያ በአዲሱ የቻይና ባለ ድርሻና በጀርመናውያኑ መካከል የምርቶችን ጥራትና የአሠራር ሂደትን በተመለከተ ችግር መፈጠሩ አልቀረም። ግን በአሁኑ ጊዜ በቻይናውያኑ ተባባሪዎች ላይ የነበረው ጥርጣሬ አየተወገደ ሄዷል። ሁለቱ ወገኖች እየተቀራረቡና እየተግባቡ ዛሬ ክፉና ደጉን ሁሉ መጋራት የቻሉ ናቸው።

“በትብብራችን ሂደት የቻይናው ባለድርሻ ለኩባንያችን የሚበጅ መሆኑን ለመማር ችለናል። በተለይም ኩባንያችን ዱርኮፕ አድለር በዓለምአቀፉ የፊናንና የኤኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ 60 በመቶ የገቢ ማቆልቆል ሲደርስበት ወዲያው ነው ገንዘብ ያቀረበልን። ያለዚህ ድጋፍ ኩባንያው የፊናንሱን ቀውስ ምናልባት ሕያው ሆኖ ሊያልፍ ባለቻለም ነበር”

በአጠቃላይ የቻይና ኩባንያዎች ጀርመን ውስጥ በሚያደርጉት መዋዕለ-ነዋይ ሁለቱም ወገን ተጠቃሚዎች መሆናቸው ነው የሚታመነው። የቻይና ኩባንያዎች በዚህ በሮርድራይን-ዌስትፋሊያ ክፍለ-ሕገር በወቅቱ የሚያሰሯቸው ተቀጣሪዎች አምሥት ሺህ ይጠጋሉ። እርግጥ ስራው ማራኪ ቢሆንም በቂ የጀርመንኛና የቻይና ቋንቋ ችሎታ ያላቸው ሁለቱንም ሕብረተሰብ የሚያውቁ ሠራተኞች እጥረት ገና ከፍተኛ ነው። ይህም ሆኖ ለቻይናው የንግድ ባለሥልጣን ለቼን ጂያን ግን ጉዳዩ ያን ያህል አሳሳቢ አይደለም።

“ይህ ትልቅ ችግር ይሆናል ብዬ የላስብም”

እንደ ጂያን ዕምነት ሂደቱ የጀርመንና የቻይና ኩባንያዎች በጋራ ሊቋቋሙት የሚችሉት ነው። የቻይና አካሄድ ከቤይጂንግ መንግሥት ፖሊሲ አንጻር በስልታዊ ስሌት ላይም የተመሠረተ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጂያባዎ ከጥቂት ወራት በፊት አገራቸው በአውሮፓ፤ በኤውሮ-ዞን አካባቢ የምታደርገውን መዋዕለ-ነዋይ እንደምታስፋፋ ሲገልጹ እርግጥ በዕዳ ቀውስ ላይ የሚገኙት ምዕራባውያን ሃገራትም ኤኮኖሚያቸውን አቅድ ማስያዝ እንዳለባቸው አስከንዝበው ነበር። አውሮፓውያኑ ታላቅ የገንዘብ ክምችት ያደረገችውን የቻይናን ድጋፍ መሻታቸው የማይቀር ሲሆን በአጸፋው ግን ለቤይጂንግ የገበያ ኤኮኖሚ ብቃት ከተመደበው ጊዜ ቀድመው ሙሉ ዕውቅና መስጠታቸው ግድ ነው የሚሆነው።

በዓለም ንግድ ድርጅት ደምቦች መሠረት ቻይና ሙሉ የገበያ ኤኮኖሚ ደረጃ ዕውቅና የምታገኘው በ 2016 ዓ.ም. ነው። ሆኖም አሁን የገንዘብ አቅሟን የቀደመ ዕውቅናን ለመግዛት ልትጠምበት ትችል ይሆናል። የአውሮፓ ሕብረት መሪዎች በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የቻይና ታላላቅ ኩባንያዎች የመንግሥት መሆናቸውንና አስተዳዳሪዎቹም በመንግሥት እንደሚሰየሙ በማመልከት ለዕውቅና አስፈላጊውን ሁኔታ አታሟላም ሲሉ ነው የቆዩት።
ሆኖም አሁን ከተፈጠተው የበጀት ቀውስ አንጻር በዚህ አቋም ጸንተው መቀጠላቸው ያጠያይቃል። ቻይና ዛሬ ከሶሥት ትሪሊዮን ዶላር የሚበልጥ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ያላት አገር ስትሆን ከወዲሁ በግሪክ፣ በስፓኝና በፖርቱጋል መዋዕለ-ነዋይ እያደረገች ነው። ይሄው የገንዘብ ክምችቷ እንግዲህ ገና ብዙ በሮችን ሊከፍትላት ይችል ይሆናል። ከዚህ አንጻር የቻይና ኩባንያዎች በአውሮፓ ይበልጥ እየተስፋፉ የሚሄዱ ለመሆናቸው አንድና ሁለት የለውም። ጥያቄው የማን ጥቅም ያመዝናል ነው።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ