1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻይና ጠቅላይ ሚንስትር የበርሊን ጉብኝት

ሐሙስ፣ ጥር 21 2001

የቻይና ጠቅላይ ሚንስትርዌን ዢባው በአውሮጳ በጀመሩት ጉዞዋቸው ዛሬ በበርሊን ከጀርመን መራሂተመንግስት አንጌላ ሜርክል ጋር ተገናኙ።

https://p.dw.com/p/GjPn
ሜርክል ዢባውን ሲቀበሉ
ሜርክል ዢባውን ሲቀበሉምስል AP

ይኸው የቻይናዊው ጠቅላይ ሚንስትር ጉብኝት የጀርመን መራሂተ መንግስት እአአ በ 2007 ዓም በግዞት የሚኖሩትን የቲቤት መንፈሳዊ መሪ ዳላይ ላማን በተቀበሉበት ድርጊት ሽክረት ታይቶበት የነበረውን የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት እንዳዲስ እንደሚያነቃቃ እና ጠንካራ የኤኮኖሚ ትብብር እንደሚያስገኝም ተስፋ ተደርጎዋል። ሜርክልና ዢባው በዓለም የፊናንሱ ቀውስ ከተከሰተ ወዲህ ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ጀርመናዊትዋ መራሂተ መንግስትና ቻይናዊው ጠቅላይ ሚንስትር ዛሬ ማርፈጃው ላይ ባደረጉት ውይይት ላይ ለፊናንሱ ቀውስ በጋራ ሊገኝ በሚችል የመፍትሄ ሀሳብ ላይ መክረዋል። በግዙፉ የውጭ ንግድ ላይ ያተኮረ ኤኮኖሚ ያላቸው ሁለቱ ሀገሮች በኤኮኖሚውና በንግዱ ዘርፍ በቅርብ ተባብረው ለመስራት እንደሚፈልጉ አጉልተዋል። ትናንት ማምሻቸውን በዳቮስ ስዊትዘርላንድ በተከፈተው የኤኮኒሚ ጉባዔ የተገኙት ዢባው የፊናንሱ ቀውስ በሀገራቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉን ቢገልጹም፡ ሀገራቸው ዘንድሮም አምና ያስመዘገበችውን ዕድገት ለማስገኘት እንደምትችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የፊናንሱ ቀውስ በቻይናና በጀርመን ንግድ ግንኙነት ላይ ስለሚኖረው ተጽዕኖ በጀርመን ኤኮኖሚ ሚንስቴር የእስያ ፓሲፊክ ኮሚቴ ሊቀ መንበርና የቻይና ተጠሪ ዩርገን ሄሩስ ሲያስረዱ፡

« በአስር ከመቶ ያደገው የቻይና ጠቅላላ ብሄራዊ ገቢ - በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከሀያ እስከ ሀያ ሰባት ከመቶ ው በግማሽ ይቀንሳል። ይህ ለኛ ኤክስፖርት መጥፎ ነው፡ ማህበራዊ ውጥረት ሊያስነሳ ስለሚችልም ለቻይናም መጥፎ ነው። ሆኖም ማንም ሀገር ራሱን ለመርዳት ሲል የንግድ ማከላከያ ርምጃ ሊወስድ እንደማይገባ ከማስጠንቀቅ አልቦዘኑም። »

ዌን ዢባው ሀገራቸው ከጀርመን ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነትን ዘንድሮም ምንም እንኳን የፊናንሱ ቀውስ ቢከሰትም አምና በነበረው ደረጃ ለመጠበቅ እንደምትጥር አስታውቀዋል። የጀርመንና የቻይና የንግድ ግንኙነት አምና 115 ሚልያርድ ዩኤስ ዶላር ፡ ይህም ቻይና ከአውሮጳ ጋር ካደረገችው በአንድ ሩብ እንደሚበለጠ ገልጸዋል። ዢባው ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ የጀርመን ምርትና ስነ ቴክኒክን የሚገዛ አንድ የሀገራቸውን የኤኮኖሚ ቡድን እንደሚመልኩ ገልጸዋል።

ጀርመንና ቻይና በርካታ ውሎች እንደሚፈረሙ ተገልጾዋል። ጀርመንና ቻይና በአየር ጸባይ ከለላም ላይ ተባብረው ለመስራት ባላቸው ፍላጎት መሰረት፡ የጀርመን ተፈጥሮ አካባቢ ሚንስትር ዚግማር ጋብርየል እና ቻይናዊው አቻቸው ዣንግ ፒንግ ዛሬ በመራሂአንግስትዋ ጽህፈት ቤት አንድ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ሜርክል አስቸጋሪዎቹን የቻይና ሰብዓዊ መብት እና የቲቤት ፖለቲካ ጥያቄዎችን ከቻይናዊው አቻቸው ጋር አንስተው ተወያይተዋል። ጀርመናውያኑ ባለስልጣናት ከዢባው ጋር በሚያደርጉት ውይይት ላይ ስለአሳሳቢው የፕሬስ ነጻነት ሁኔታ፡ የታሰሩ ጋዜጠኞችና በኢንተርኔት የተቃውሞ አስተያየት ያሰፈሩ ግለሰቦች እንዲፈቱ ለጋኡኤጠኞች መብት የሚሟገተው ድንበር የማይገድበው ድርክት አስታውቋል። የፍሪ ቲቤት ዘመቻ የተሰኘ አንድ የጀርመናውያን ቡድን ተጠሪ ካይ ሚውለርም ተመሳሳዩን የሰብዓዊ መብት ይዞታ ጥያቄ አሰምተዋል።

« የሰብዓዊ መብት እና ቻይና የምትከተለውን የቲቤት ፖለቲካን የሚመለከቱ ጥያቄዎች በንዲህ ዓይነቱ አዳጋች ጊዜ በውይይቱ አጀንዳ ሊነሱ ይገባል። አንድ ዘላቂ የውጭ እና የሰብዓዊ መብት ፖለቲካ ይህንን ማስደረግ መቻል ይገባዋል። » የዢባውን የበርሊን ግንኙነት ምክንያት በማድረግ፡ ለሀይማኖትና ለቲቤት ነጻነት የሚሟቱ ሰዎች በመራሂተ መንግስትዋ ጽህፈት ቤት ደጃፍ ተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል።

DPA, AP

AA,Tekle Yewhala