1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻድ ውግያ

ዓርብ፣ ኅዳር 1 1999
https://p.dw.com/p/E0hj

ቻድን ከሱዳንዋ የዳርፉር ግዛት ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ በተነሳው የጎሳ ግጭት ከሁለት መቶ የሚበልጡ ሰዎች ተገደሉ ። የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ መርጃ ድርጅት ትናንት እንዳስታወቀው ከግድያው በተጨማሪ ዘጠኝ መንደሮችም ተዘርፈዋል ። ድርጅቱ ወደ አካባቢው የላከው አጣሪ ቡድን ከዓይን ምስክሮች እንደሰማው ሰዎቹን የገደሉትና ንብረት የዘረፉት ታጣቂዎች ቤቶችንም አቃጥለዋል ። የቻድ መንግስት በበኩሉ ጥቃቱን በሁለት ጎሳዎች መካከል የተካሄደ አነስተኛ ግጭት ነበር ያለው ። ቻድ የዳርፉሩ ብጥብጥ ድንበር እየተሻገረም ነው ስትል ተናግራለች ።ዳርፉርን በሚያዋስነው ምስራቃዊ ቻድ ውስጥ ሁለት መቶ አስራ ስምንት ሺህ የዳርፉር ስደተኞች ይገኛሉ ። ሰሞኑን የበርካታ ሰዎች ህይወት የጠፋውና ንብረትም የወደመው በዚህ የቻድ ግዛት ውስጥ ሲሆን ጥቃቱ የተፈፀመውም የዳርፉር ስደተኞች ከተጠለሉበት መንደር በጥቂት ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ነበር ። የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ሄሌነ ካውክስ እንዳሉት ምስራቅ ቻድ ውስጥ ኬርሲ በተባለው አካባቢ ጥቃቱ ከተፈፀመባቸው መንደሮች ነዋሪዎች የተገኘኙት መረጃዎች በሰሞኑ ጥቃት ቢያንስ ሀለት መቶ ሀያ ሰዎች መገደላቸውን ጠቁመዋል ። ብዙዎችም እንደቆሰሉ ። ድርጅቱ የላከው አጣሪ ቡድን አባላት ከትናንት በስተያ በጎበኙት ድጆሮሎ በተባለው መንደር ሰላሳ ስድስት ሰዎች መገደላቸውንና ሀያ ሁለት መቁሰላቸውን አረጋግጠዋል ። በዚሁ መንደር የተፈፀመው አሰቃቂ ግድያና ርህራሄ የጎደለው የንብረት ጥፋት የመንደሮቹን ነዋሪዎች ረብሿል ። አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ጎጆዎቻቸው ሲቃጡሉ በዓይናቸው እያዩ ስለሁኔታው ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደገለፁት ቅዳሜ የተጀመረው ጥቃት እስከ ረቡዕ ድረስ ዘልቋል ። አጥቂዎቹም ቁጥራቸው ወደ ሁለት መቶ እንደሚጠጋ ሲነገር የቻድ ወታደሮችን የመለያ ልብስ የለበሱ መሆናቸውን ቃል አቀባዋ የየመንደሮቹን ነዋሪዎች ዋቢ አድርገው ተናግረዋል ። እንደ ቃል አቀባይ ካውክስ ከነዋሪዎቹ የተገኙት መረጃዎች ጥቃቱ በተቀናጀ መንገድ ተፈፅሟል ወደ ሚል አስተሳሰም መርቷቸዋል ። የቻድ መንግስት በበኩሉ ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ በቻድ ምስራቃዊ ግዛት ሀገሪቱን ከዳርፉር ጋር በሚያዋስናት አካባቢ በተቀሰቀሰ ግጭት አንድ መቶ ሰዎች ተገድለዋል ሲል ነበር ያስታወቀው ። መንግስት በዚሁ መግለጫው የግጭት መንስኤ ምን እንደሆነ አልተናገረም ። የኢንጃሚና መንግስት ቃል አቀባይ እና የመገናኛ ሚኒስትር ሆርማድጂ ሙሳ ዱምጎር በሰጡት መግለጫ ከጥቅምት ሀያ አምስት አንስቶ በአካባቢው የጎሳ ግጭት እንዳለ አስታውቀዋል ። ስለሰሞኑ የቻድ ግድያ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር አንቶኒዮ ጉተሬስ ከጄኔቭ ባወጡት መግለጫ ድርጅታቸው የዳርፉር ብጥብጥ የአካባቢውን አገራት ሰላም ማናጋቱ እንደማይቀር ከወራት በፊት ማሳሰባቸውን ነበር ያስታወሱት ። ጉተርስ አክለውም ዓለም ዓቀፍ ኃይል በምስራቅ ቻድ እንዲሰማራ እንዲሁም የአካባቢውን ፀጥታ ለማስጠበቅም ከቻድ በኩል የተጠናከረ ጥረት እንዲደረግ የቀረበውን ጥሪ እንደሚደግፉ አስታውቀውል ። ባለፈው ወር በቻድ አማፂያን ቡድንና በመንግስት ጦር መካከል በዚሁ አካባቢ በተካሄደ ውጊያ ከአማፅያኑ በኩል አንድ መቶ ከመንግስት ወታደሮች ወገን ደግሞ ሁለት መቶ ከተገደሉ በኃላ ነው የጎሳ ግጭቶች የተከተሉት ። በግጭቱ ሰበብም ወደ አንድ ሺህ ሰዎች አካባቢውን ለቀው ሸሽተዋል ። ቻድ ለዚህ ሁሉ ብጥብጥ ተጠያቂ የምታደርገው የካርቱምን መንግስት ነው ። ቻድ እንደምትለው ሱዳን በምስራቅ ቻድ የአማፅያንን ዕንቅስቃሴ ትደግፋለች ። ካለፈው ወር አንስቶ ምስራቅ ቻድ ውስጥ የዲሞክራሲና የልማት ሀይሎች በሚል መጠሪያ ግንባር የፈጠሩት የቻድ ዓማፅያን ሀይሎች ምስራቃዊ ቻድ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ከተሞችን ይዘዋል ለግችቱም ተጠያቂ የሚያደርጉት የቻዱን ፕሬዝዳንት የኢድሪስ ዴቢን መንግስት ነው ። የግንባሩ መሪ ከትናንት በስተያ ለአዦንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደተናገሩት ጥቃት ፈፃሚዎቹን ሚሊሽያዎች ያደራጀው የሱዳን መንግስት ነው ።