1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻድ ጦርነትና የአለም አቀፉ ማሕበረሰብ አቋም

ማክሰኞ፣ ጥር 27 2000

የቻድ ነገ-ሁኔታ እንደ ዛሬዉ የተዋጊ ሐይሎቿ አባባል እዉነት ሐሰትነት ሁሉ አለየም።

https://p.dw.com/p/E0Ze
ኢንጃሚና፣ እድለኞቹ ጥለዋት ወጡ
ኢንጃሚና፣ እድለኞቹ ጥለዋት ወጡምስል AP

ፕሬዝዳት ኢድሪስ ዴቢ የሚመሩትን የቻድ መንግሥት ለማስወገድ የሚፋለሙት አማፂያን የተኩስ አቁም ሥምምነት እንዲደግ የቀረበላቸዉን ጥያቄ ተቀበሉት።የአፍሪቃ ሕብረት፤ የአለም ሙስሊም ሐገራት ጉባኤና የቻድ አገራባች ሐገራት ተፋላሚ ሐይላት ዉጊያ አቁመዉ እንዲደራደሩ እየጠየቁ ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ግን የዉጪ ጦር አማፂያኑን እንዲወጋ መፍቀዱ ርዕሠ-ከተማ ኢንጃሚናን ያመሰቃቀለዉን ጦርነት በሰላም ለማስቆም የሚደረገዉን ጥረት ሳያጉለዉ አልቀረም።ሥለ ቻድ ሁኔታ ነጋሽ መሐመድ የዜና መልዕክቶች አሰባስቧል።

እድሜ ለፈቀደለት የኢንጃሚና ነዋሪ የርዕሠ-ከተማይቱ ግፅታ የዛሬ ሃያ-ዘጠኝ አመቱን ዘግናኝ ትዝታ፣ ለወጣቱ ደግሞ የዛሬ አስራ-ዘጠኝ አመቱን አስፈሪ ገጠመኝ ቀስቃሽ ነዉ።አዉራ መንገደችዋ እሬሳ ተሰጥቶባቸል፣ጥቁር-እስፋልቷ-በደም-ቀልቶ-ቡናማ መስሏል።ሕንፃዎችዋ ፈራሰዋል፣ ተቦዳድሰዋል፣ ይጤሳሉም፤ መደብሮች፤ መስሪያ ቤቶች፤ ሌሎች ተቋማት እንደተከረቸሙ-ነዉ።ዛሬ አራተኛ ቀናቸዉ።

ኢንጃሚና የሞት ጥላ ሲያንዣብባት አርብ የቀድሞዉ የቻድ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ እዚያ የሚኖሩ የዉጪ ዜጎች አስወጣች።ወደ ጋቦን ከተሻገሩት የዉጪ ዜጎች አንዱ ጀርመናዊ እድለኞች ነን ይላሉ።

«በብረት ለበስ ተሽከርካሪ ተሳፍረን ወደ አዉሮፕላን ማረፊያዉ ተወሰድን።በየመንገዱ ከባድ ተኩስ ነበር።ግን እኛ እድለኞች ነን።በተኩሱ መሐል አልፈን ከፈረንሳዮች ጦር ሰፈር ደረንና ከዚያ ወደዚሕ ተጓዝን።»

ያልታደለዉ የኢንጃሚና ሕዝብ እድል ፍለጋ በእግሩ፣ በመኪም እየተግተለተለ ወደ ካሜሩን ይጎርፍ ገባ።የአለም የስደተኞች መርጃ ድርጅት እንዳስታወቀዉ እስከ ዛሬ ድረስ ከአስራ-አምስት እስከ ሐያ ሺሕ የሚደርስ የቻድ ሕዝብ ካሜሩን ገብቷል።ከስድት እስከ ስምንት ሺሕ የሚደርስ የኢንጃሚና ነዋሪ ደግሞ ከቻድ ወደ ካሚሩን በሚያጉዘዉ መንገድ ላይ በየቀበሌዉ ሠፍሯል።

በካሜሩን የአለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ ተጠሪ ወይዘሮ ማሪያ ቴሬሳ ጋርዲዮ እንደሚሉት እዚያዉ እንጀሚና የቀሩት-ደካሞች፤ የቆሰሉትን፣ እና በየአዉራ መንገዱ የወደቀዉን ሬሳ ለማንሳት ኮሚቴያቸዉ እየጣረ ነዉ።

«የአለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ ከቻድ ቀይመስቀል ማሕበረሰብ ጋር በመተባበር እየሰራ ነዉ።የቻድ ቀይ መስቀል ማሕበረሰብ ባልደረቦች ከተማይቱን የሚያብጠዉ ዉጊያ ጋብ ካለበት ጊዜ ጀምሮ የደከሙ፤ የቆሰሉ ሰዎችን ለመርዳት፤ በየመንገዱ የወደቁ አስከሬኖችን ለመስብሰብ በሳምንቱ ማብቂያ በሙሉ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነዉ።»


ኢንጃሚና የቻድ አምባገነን መሪ ፍራንሲስ ቶምብሌዬ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር በ1977 በተወገዱ፤ በተገደሉበት፣ ወቅት ልክ እንዳሁኑ ነበረች።በሁለተኛ አመቱ ሒስኒ ሐብሬ ሥልጣን ሲይዙም ልክ እንዳሁኑ። ሒብሬን ታማኝ ጄኔራላቸዉ ኢድሪስ ዴቢ በ1987 ካስወገዷቸዉ ወዲሕ ግን ሰላም የሰፈነባት መስላ ነበር።ዴቢ የያኔዉን የሒብሬን እጣ፣ መሐመድ ኑሬ የጄናል የዴቢን እድል ለመያዝ የተቃረቡ ሲመስሉባት አሁን ለሐያ አመት የመሰለዉ ሁሉ በምሰል ቀረ።

ዉጊያ ጦርነቱ ለሚያጠፋ፤ የሚያሰድደዉ የቻድ ሕዝብ ዛሬ ከዉጪ የሰማዉ የበጎ፣ መጥፎ ቅይጥ ዜና መሆኑ ደግሞ የአበሳዉን ፍፃሜ ሳያርቀዉ አልቀረም።የአማፂዉ ቡድን ሊቢያና እና ቡርኪናፋሶ ያቀረቡት ጊዚያዉ የተኩስ አቁም ሐሳብ እንደሚቀበለዉ አስታዉቋል።የአለም ሙስሊም ሐገራት ጉባኤ ተፋላሚ ሐይሎች ዉጊያ አቁመዉ እንዲደራደሩ ጠይቋል።የአፍሪቃ ሕብረት የመልዕክተኞች ጓድ ሠላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ ዛሬ ኢንጃሚና ይገባል ተብሏል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ግን አማፂዉን ቡድን አዉግዟል።

ፈረንሳይና ሌሎች ሐገሮችን ከኢድሪስ ደቢ ጦር ጋር ወግነዉ አማፂዎቹን እንዲወጉም ምክር ቤቱ የድጋፍ ፍንጭ ሰጥቷል።ይሕ ነዉ ለመከረኛዉ ሕዝብ ተጨማሪዉ መከራ።የአማፂዉ ቡድን ቃል አቀባይ አብዱረሕማን ኩወልሙልሕ እንደሚሉት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉሳኔ፣ በተለይ የፈረሳይ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት አሳዛኝ-አሳሳቢም ነዉ።


ኢንጃሚና ዛሬ ካልፎ-አልፎ ከሚሰማ የጠመንጃ ተኩስ በስተቀር ሠላም ነች።ወይም መስላለች።የመንግሥት ጦር እንደሚለዉ «የሥላሙ» መሠረት ጠላቶቹን መትቶ ከከተማይቱ በማሰወጣቱ ነዉ።የአማፂዉ ቡድን መሪ መሐመድ ኑር ግን፣ የመንግሥት ጦርን አባባል ሐሰት ይሉታል።

«ተዋጊዎቹ ከተማይቱን በሙሉ ለቀዉ አልወጡም።በርካታ ቁጥር ያላቸዉ ተዋጊዎች አሁንም የከተማይቱን ብዙ ክፍሎች እንደተቆጣጠሩ ነዉ።ጠላት በአዉሮፕላንና በከባድ ጦር መሳሪያ በሕዝብ ላይ የሚያደርሰዉን ድብደባ ለመቀነስ ሥንል የተወሰኑ የከተማይቱ አካባቢዎች አፈግፍገናል።ከዚሕ ዉጪ ከተማይቱን ለቀን አልወጣንም።ትናንት ራሱ የመንግሥትን ጦር መተናል።መጠነ-ሰፊ ጥቃትም አቅደናል።ባጭር ጊዜ ዉስጥ።አላማችን የኢድሪስ ዴቢን መንግሥት ማስወገድና በቻድ ሠላምና ዲሞክራሲን ማስፈን ነዉ።»


የቻድ ነገ-ሁኔታ እንደ ዛሬዉ የተዋጊ ሐይሎቿ አባባል እዉነት ሐሰትነት ሁሉ አለየም።