1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነሐሴ 18 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ነሐሴ 18 2012

የጀርመኑ ኃያል ባየር ሙይንሽን እንደተጠበቀው ሦስተኛ ዋንጫውን ትናንት በእጁ አስገብቷል። በአሰልጣኝ ዲተር ሐንስ ፍሊክ ከተመዘገቡ ድሎች መካከል የትናንቱ ቁንጮው ነው። በሺህዎች የሚቆጠሩ የፖሪስ ሳን ጄርማ ደጋፊዎች በቡድናቸው ሽንፈት በመበሳጨት በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ እና ማርሴይ ለአመጽ አደባባይ ወጥተዋል።

https://p.dw.com/p/3hQmq
Frankreich Randale in Paris nach Endspiel der Champions League
ምስል picture-alliance/dpa/AFP/S. Al-Doumy

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የጀርመኑ ኃያል ባየር ሙይንሽን እንደተጠበቀው ሦስተኛ ዋንጫውን ትናንት በእጁ አስገብቷል። አሰልጣኝ ዲተር ሐንስ ፍሊክ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ከያዙበት ጊዜ አንስቶ ከተመዘገቡ ድሎች መካከል የትናንቱ ቁንጮው ነው። በሺህዎች የሚቆጠሩ የፖሪስ ሳን ጄርማ ደጋፊዎች በቡድናቸው ሽንፈት በመበሳጨት በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ እና ማርሴይ ለአመጽ አደባባይ ወጥተዋል። ከፍተኛ ንብረትም አውድመዋል። በሳምንቱ መጨረሻ የአውሮጳ ሊግ ዋንጫን ያነሳው ሴቪያ የዛሬ ወር ለሱፐር ካፕ ዋንጫ ኃያሉ ባየር ሙይንሽንን ይገጥማል። በትናንቱ የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ በጀርመን ኹለተኛው ቴሌቪዥን ጣቢያ የቀጥታ ሥርጭት ታሪክ ከፍተኛው የተመልካች ቊጥር ተመዝግቧል።

የሻምፒዮንስ ሊግ

የትናንቱ የአውሮጳ ሻምፖዮንስ ሊግ የእግር ኳስ የፍጻሜ ግጥሚያ፦ የፓሪስ ሳንጄርማ ደጋፊዎችን ሕልም አምክኖ በንዴት አደባባይ ያስወጣ ውጤት ነበር። አምስት ሺህ ያኽል የፓሪስ ሳንጄርማ ደጋፊዎች ትናንት ምሽት አደባባይ ወጥተው በቊጣ መደብሮችን አውድመዋል፤ መስኮቶችንም ሰባብረዋል። ሌሊቱን ባጋመሰው ነውጥ አዘል ተቃውሞ የቡድኑ ደጋፊዎች በርካታ ተሽከርካሪዎችን በእሳት አንድደው ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል። ፖሊስ አስለቃሽ ጢስ እና የፕላስቲክ ጥይቶችን ቢተኩስም ነውጠኞቹን ግን በቀላሉ መበተን አልቻለም። 150 ያኽሉን ፖሊስ በቊጥጥር ስር ማዋሉንም ዐስታውቋል።

የፓሪስ ሳንጄርማ ደጋፊዎች በባየር ሙይንሽን ከተሸነፉ በኋላ ፓሪስ ውስጥ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል
የፓሪስ ሳንጄርማ ደጋፊዎች በባየር ሙይንሽን ከተሸነፉ በኋላ ፓሪስ ውስጥ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Euler

በዚህኛው በኩል ደግሞ፦ ባየር ሙይንሽኖች በዘመነ-ሐንሲ ፍሊክ ወሳኝ የተባሉ ሦስት ዋንጫዎችን የመሰብሰባቸው ማሳረጊያም ነበር የትናንት ምሽቱ ድል። የባየር ሙይንሽን ቡድን መቀመጫ ሙይንሽን ከተማ ምሽቱን በተሽከርካሪዎች ጥሩምባ ደምቃ ቆይታለች።

የትናንት ምሽቱን የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ግጥሚያ የጀርመኑ ኹለተኛው ቴሌቪዝን (ZDF) ከፖርቹጋል ሊዝቦን ከተማ ለጀርመን ተመልካቾች በቀጥታ ሲያስተላልፍ 12,79 ሚሊዮን ሰዎች ጨዋታውን በቀጥታ ተከታትለዋል። በዚህም የቴሌቪዥን ጣቢያው የቀጥታ ሥርጭት ከፍተኛ የተመልካች ቊጥር ተብሎ ተመዝግቧል።

ከዚህ ቀደም በቴሌቪዥን ጣቢያው የቀጥታ ሥርጭት ከፍተኛ የተመልካች ቊጥር የተመዘገበው እሑድ መጋቢት 13 ቀን ነበር። በእለቱ የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል የኮሮና ተሐዋሲ መስፋፋትን ለመግታት ይቻል ዘንድ ሰዎች ከቤተሰባቸው ውጪ ካሉ ሰዎች ጋር መገናኘት በጥብቅ መከልከሉን የገለጡበት ንግግራቸው ነበር።  በእለቱ 12, 4 ሚሊዮን ተመልካቾች የቀጥታ ንግግራቸውን በዚሁ ቴሌቪዥን ተከታትለዋል።

የዘንድሮ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ አሸናፊ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ተጨዋቾች በፍጻሜው ደስታቸውን ሲገልጡ
የዘንድሮ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ አሸናፊ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ተጨዋቾች በፍጻሜው ደስታቸውን ሲገልጡምስል Getty Images/AFP/M. Childs

የአውሮጳ ሊግ የፍጻሜ ግጥሚያን ደግሞ በ(ZDF) ቴሌቪዥን 3,53 ሚሊዮን ተመልካቾች በቀጥታ ተከታትለው ነበር። የትናንቱ የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ግጥሚያ የተመልካች ቊጥር ከአውሮጳ ሊጉ በአራት እጥፍ የሚልቅ ነበር።

ባየር ሙይንሽን ከፓሪስ ሳንጀርሜን ግጥሚያ ትንታኔ

በትናንቱ ግጥሚያ አሰልጣኝ ሐንስ ዲተር ፍሊክ ከግማሽ ፍጻሜው አንፃር የመጀመሪያ ተሰላፊ የቀየሩት በስተግራ ክንፍ በኩል ኢቫን ፔሪሲችን በቀድሞው የፓሪስ ሳንጄርማ ተሰላፊ ኪንግስሌይ ኮማንን ብቻ ነበር። ሌሎቹ በሙሉ ቀደም ባለው ግጥሚያ የተሰለፉ ነበሩ። ኪንግስሌይ ኮማን ባልተጠበቀ መልኩ የመጀመሪያ ተሰላፊ ስለኾነበት ምክንይታ አሰልጣኙ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ኪንግስሌይ ኮማ በፓሪስ ሳንጄርማ ቡድን ቀድሞ ይሰለፍበት የነበረውን ቦታ መስጠታቸው ይበልጥ ያነቃቃዋል በሚል ነው ብለዋል። በእርግጥም ፔሪሲችን አስቀምጠው ኮማን ማስገባታቸው ብቸኛዋን የማሸነፊያ ግብ በ59ኛው ደቂቃ በጭንቅላት ገጭቶ በድንቅ ኹኔታ ከመረብ እንዲያሳርፍ አስችሎታል።

 ኪንግስሌይ ኮማ  በቀድሞ ቡድኑ ፓሪስ ሳንጄርማ ላይ ብቸኛዋን ግብ ካስቆጠረ በኋላ ደስታውን ሲገልጥ
ኪንግስሌይ ኮማ በቀድሞ ቡድኑ ፓሪስ ሳንጄርማ ላይ ብቸኛዋን ግብ ካስቆጠረ በኋላ ደስታውን ሲገልጥምስል Imago Images/Panoramic

በቀኝ ተከላካይ ኦሎምፒክ ሊዮንን 3 ለ0 ባሸነፉበት ግጥሚያ ቀደም ሲል ከደረሰበት የእግር ጉዳቱ ያገገመው እና ለጥቂት ደቂቃ አማካዩ ግሮቴስካን ቀይሮ በገባው ቤንጃሚን ፓቫርድ ምትክ ያሰለፉት ዮሹዋ ኪሚሽን ነበር። ይኸው የቀኝ መስመር ተከላካይም ነበር ወደፊት ገፍቶ ግሩም በሚባል ኹኔታ ለኪንግስሌይ ኮማን በረዥሙ ኳስ በስተቀኝ ያሻማው እና ብቸኛዋ ግብ የተቆጠረችው።

18ኛው ደቂቃ ላይ ኔይማር ወደ ውጪ ልትወጣ የነበረችውን ኳስ አሻምቶ ማኑዌል ኖየር በቅልጥፍና ግብ ከመኾን ያዳናት አጋጣሚ ለባየር ሙይንሽን አስደንጋጭ ነበር፤ ለኔይማር ደግሞ አስቆጪ። 22ኛ ደቂቃ ላይ ሌቫንዶቭስኪ የፒኤስጂ ግብ ክልል ደርሶ ተጠማዞ የሞከራት ኳስ የግብ ማእዘኑን ገጭታ ወጥታለች። በ23ኛው ደቂቃ ዲ ማሪያ ከባየር ሙይንሽን ግብ አግዳሚ በላይ የላካት ኳስ ለፓሪስ ሳንጄርማ ደጋፊዎች የምታስቆጭ ናት።

45ኛ ደቂቃ ላይ ከኋላ በአላባ በተፈጠረ ከባድ ስህተት እምባፔ ዘሎ ገብቶ ኳሷን አግኝቶ ነበር፤ ግን ቀጥታ ለማኑዌል ኖየር ነበር ያሳቀፈው። በእዛው ቅጽበት የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ በጭማሪው 1 ደቂቃ ግናብሬ ወደ ግብ ደርሶ በቀኝ በኩል የመታትን ኳስ ግብ ጠባቂው ያዳነበት ከባድ ሙከራ ነበር።

የፓሪስ ሴንጄርማኑ ኔይማር በሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ በባየር ሙይንሽን 1 ለ0 ከተሸነፉ በኋላ በሐዘን ተውጦ ሲያለቅስ
የፓሪስ ሴንጄርማኑ ኔይማር በሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ በባየር ሙይንሽን 1 ለ0 ከተሸነፉ በኋላ በሐዘን ተውጦ ሲያለቅስምስል picture-alliance/dpa/Michael Regan/Getty Images via UEFA

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩት ደግሞ ኪንግስሌይ ኮማን ትከሻ ላይ የፓሪስ ሳንጀርማኑ ቲሎ ኬህረር እጁን ሲያሳርፍ ኪንግስሌይ ኮማን ፍጹም ቅጣት ክልል ውስጥ ወድቆ ነበር። የባየርን ተጨዋቾች ዳኛው ፍጹም ቅጣት ምት እንዲሰጣቸው ቢጠይቊም በቪዲዮ ረዳት እንቅስቃሴው ታይቶ ፍጹም ቅጣት ምቱ ግን አልተሰጠም። ይኽም ለባየር ሙይንሽን ሌላኛው ወሳኝ አጋጣሚ ነበር።

ወዲያው ፓሪስ ሳንጄርማ በመልሶ ማጥቃት ድንቅ ሙከራ አድርጎ ነበር። ከረፍት መልስ የግብ ሙከራዎቹ ተገትተው ተደጋጋሚ ጥፋቶች እየተከሰቱ ቢጫ ካርዶች በዳኛው ሲመዘዙ ነበር።

በእለቱ በርካታ ኳሶችን ግብ ከመኾን ያመከነው ግብ ጠባቂው ማኑዌል ኖየር ውድድሩ እንዳለቀ ተጠይቆ በሰጠው አስተያየት ጨዋታው እስኪጠናቀቅ ለቡድኑ በሙሉ አስጨናቂ ነበር።

«ፊሽካው ከተነፋ በኋላ የነበረው ደስታ ከፍተኛ ነበር። እፎይታ ነው የተሰማን። አምስት ተጨማሪ ደቂቃ ተጨምሮ፤ ኹላችንም ዳኛው በስተመጨረሻ ፊሽካውን እስኪነፉ ስንጠብቅ ነበር። የሚገባን፤ ስንመኘው የነበረ፤ ለእኛ በእውነቱ ሕልማችን ነበር» ብሏል።

ብዙ ተጠብቆ የነበረው ኔይማር በባየር ሙይንሽን ተከላካዮች አልፎንሶ ዳቪስ እና ጄሮም ቦአቴንግ ተከቦ
ብዙ ተጠብቆ የነበረው ኔይማር በባየር ሙይንሽን ተከላካዮች አልፎንሶ ዳቪስ እና ጄሮም ቦአቴንግ ተከቦ ምስል Getty Images/M. Lopes

የማሸነፊያዋን ግብ ለኪንግስሌይ ኮማ ያቀበለው የቀኝ መስመሩ ተከላካይ ዮሹዋ ኪሚሽ ልምድ ካላቸው ተጨዋቾች ጋር ተሰልፎ ውጤት በማስመዝገቡ ደስታውን እንዲህ ነበር የገለጠው።

«ከእነዲህ አይነት ቡድን ጋር በቦታው የመገኘትን ስሜት አንዳችም ነገር አይገልጠውም።   ከወንድሞች ጋር ዋንጫውን ስታሸንፍ፤ ያኔ ያ የከፍታህ ጫፉ ነው።»

በሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ጀርመናውያን ቡድኖች እንዲደርሱ ብዙዎች ተመኝተው ነበር። ያ ግን ሊኾን አልቻለም። አሰልጣኝ ቶማስ ቱኁል በፓሪ ሰንጄርሜን ታሪክ ቡድኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፍጻሜው በማድረስ የሀገራቸውን ልጅ ተስፋ አጨልመዋል። አትሌቲኮ ማድሪድን የሚያኽል ቡድን በሩብ ፍጻሜው 2 ለ1 ላሰናበተው የጀርመኑ ኤር ቤ ላይፕሲሽ በአጥቂ መስመሩ እነ ኔይማር፣ ዲማርያ እና እምባፔን ያሰለፈው ፓሪስ ሳን ጀርሜን መከራ ነበር የኾነበት። እነሱም በተራቸው ባየር ሙይንሽን መከራ ሊኾንባቸው።

ባየርን ሦስተኛ ዋንጫውን ሲያነሳ ደጋፊዎች ባይኖሩም የቡድኑ አባላት ግን ነበሩ። እናም በባየርን ደጋፊ መቀመጫ በኩል ከቡድኑ ሠራተኞች፤ የክብር እንግዶች እና የአመራር አባላት፦ «ኃያሉ ባየርን ሱፐር ባየርን» እያሉ አስቀድመው ሲዘምሩ ነበር። በኪንግስሌይ ኮማ ግብ የሊዝቦኑ ስታዲዮን ዳ ሉዝ ለባየርኖች ደስታ በብርሃን አሸብርቋል።

በአንድ የጨዋታ ዘመን ሦስት ዋንጫዎችን የሰበሰቡት የ55 ዓመቱ የባየር ሙይንሽኑ አሰልጣኝ ሐንስ ዲተር ፍሊክ
በአንድ የጨዋታ ዘመን ሦስት ዋንጫዎችን የሰበሰቡት የ55 ዓመቱ የባየር ሙይንሽኑ አሰልጣኝ ሐንስ ዲተር ፍሊክ ምስል Imago Images/Panoramic

የ55 ዓመቱ የባየር ሙይንሽኑ አሰልጣኝ ሐንሲ ፍሊክ ከምክትል አሰልጣኝነት የዋና አሰልጣኝነቱን ቦታ በሒደት ከኒኮ ኮቫች ከወሰዱበት ጊዜ አንስቶ በ35 ጨዋታዎች 32 ያኽሉን አሸንፈዋል። የእግር ኳስ አጨዋወት ስልታቸውን በቀላሉ ተጨዋቾቹ እንዲቀበሉ እና ለውጤት እንዲበቊ አስችለዋል።  መከላከል እና ባላጋራን የማስጨነቅ የአጨዋወት ስልት ብሎም ኳስን በዚህም በዚያ ብሎ መቆጣጠር ላይ ነው የሚያተኩሩት። ያለፉት የአጨዋወት ስልታቸውንም ኾነ የትናንቱን የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ለተከታተለ ተጋጣሚን በማስጨነቅ እና ግራ በማጋባት ግብ ማስቆጠር ላይ አተኩረው እንደሚጫወቱ በቀላሉ መመልከት ይቻላል።

በኅዳር ወር ውስጥ ጋዜጦች ርእስ አድርገው ያስነብቡ የነበረው «ከእንግዲህ ባየርንን የሚፈራ የለም» የሚሉ ነበሩ። ዛሬ ባየር ሙይንሽን የቀድሞ አስፈሪነቱን መልሷል። በእርግጥ በፍጻሜው ቀደም ሲል እንደታዩት ጨዋታዎች ፓሪስ ሳንጃርማን ብዙም ባያስጨንቀውም ማለት ነው።

ሐንስ ዲተር ፍሊክ፦ በወጣት ተጨዋቾች ያምናሉ። እነ ጆሹዋ ኪሚሽ፣ ሊዮን ጎሬትስካ እና ሠርጌ ግናብሬ ቊልፍ ተጨዋቾቻቸው ናቸው። ኹሉም ከ25 ዓመት አይበልጡም። አልፎንሶ ዳቪስ ገና 19 ዓመቱ ነው። አሰልጣኙ እንደ እነ ቶማስ ሙይለር እና ጄሮም ቦአቴንግን የመሰሉ በእድሜ የበሰሉ ተጨዋቾችንም እድል አይነፍጉም። እነዚህ ተጨዋቾች በኒኮ ኮቫች ጊዜ ብዙም ቦታ ሳይኖራቸው ገለል ተደርገው ነበር።

ቶማስ ሙይለር፤ ሠርጌ ግናብሬ እና ኪንግስሌይ ኮማ (ግቧን ያገባው) የማሸነፊያ ግቧ ከተቆጠረች በኋላ በደስታ ተውጠው
ቶማስ ሙይለር፤ ሠርጌ ግናብሬ እና ኪንግስሌይ ኮማ (ግቧን ያገባው) የማሸነፊያ ግቧ ከተቆጠረች በኋላ በደስታ ተውጠውምስል Getty Images/AFP/M. Lopes

ሐንስ ዲተር ፍሊክ ተሳክቶላቸዋል አኹን ደግሞ ኦሊቨር ካን ቀንቶታል። የቀድሞው የብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ኦሊቨር ካን ከባየር ሙይንሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ኃላፊነቱ ለመነሳት አንድ ዓመት የቀረው ካርል ሐይንትስ ሩሜኒገን  ለመተካት ታጭቶ ነበር። በሻምፒዮንስ ሊግ ድል ከተመዘገበ ቦታው እንደሚሰጠው ተነግሮት ነበር። «የሙከራ ጊዜው» ትናንት ተሳክቷል።  

ባየር ሙይንሽን ቡዳፔስት ውስጥ መስከረም 14 ቀን 2013 ዓም ከሴቪያ ጋር ሱፐር ካፕ (UEFA Super Cup 2020) ይጋጠምና ምናልባትም አራተኛ ዋንጫውን ይሰበስብ ይኾናል። የአውሮጳ ሱፐር ካፕ ዋንጫ፦ በሻምፒዮን ሊግ እና አውሮጳ ሊግ አሸናፊዎች መካከል የሚደረግ ነው።

ከጥቂት ቀናት በኋላ መስከረም 20 ቀን ደግሞ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋርም የጀርመን እግር ኳስ ሊግ ሱፐር ካፕ የዋንጫ ግጥሚያ ይኖረዋል። እንደ ደንቡ ለጀርመን ሱፐር ካፕ ተጋጣሚዎች የቡንደስሊጋ እና የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር (DFB) ዋንጫ አሸናፊዎች ነበሩ። ዘንድሮ ባየር ሙይንሽን ኹለቱንም ዋንጫዎች ስለወሰደ ምክትሉ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ለሱፐር ካፕ ተጋጣሚው ይኾናል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ