1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚአፍሪቃ

የነዳጅ ስርቆትንና ሕገወጥ ንግድን ለመቆጣጠር የተወሰደ እርምጃ

ሰኞ፣ ሰኔ 13 2014

በኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ አሻጥር በመፈጸም የሀገሪቱን ንግድ ለማዛባት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ እና የነዳጅ ሥርጭትና አቅርቦትን በማስተጓጎል እንቅፋት የፈጠሩ ከ103 ሺህ በላይ ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰዱን የኢትዮጵያ ንድግና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/4Cwnx
Äthiopien Addis Abeba Benzinrationierung
ምስል Solomon Muchie/DW

የነዳጅ ስርቆት

በኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ አሻጥር በመፈጸም የሀገሪቱን ንግድ ለማዛባት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ እና የነዳጅ ሥርጭትና አቅርቦትን በማስተጓጎል እንቅፋት የፈጠሩ ከ103 ሺህ በላይ ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰዱን የኢትዮጵያ ንድግና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሃሰን መሃመድ ከዶይቼ ቨል ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ባለፈው ወር ብቻ መንግሥት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማኅበረስብ ክፍሎች እንዳይጎዱ ከ 16.6 ቢልዮን ብር በላይ ለነዳጅ ድጎማ ማድረጉን ገልጸዋል። ከዚህ በማያያዝም በቅርቡ የሚኒስትሮች ምክርቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት በነዳጅ የዋጋ ጭማሪ ማስተካከያው የውጭ ተራድዖ ድርጅቶች ኤምባሲዎች ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ከፍተኛ ሃብት ያላቸው የነዳጅ ድጎማው ተጠቃሚ አይሆኑም ብለዋል። በዚህም ለነዳጅ ድጎማ ይውል የነበረውን አንድ አምስተኛው የሀገሪቱ ዓመታዊ በጀት ለመሰረተ ልማት ግንባታዎችና ማስፋፊያ እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማኅበረሰቡ ክፍሎች ለተለያየ ርዳታ እንደሚውል እንደሚሆንም ሚኒስትሩ አመልክተዋል። እስከ ዛሬ ኢትዮጵያ ከዓለም ገበያ በምትገዛውን ነዳጅ ላይ ድጎማ በማድረግ በግማሽ ቀንሳ መሸጧን እንደ መልካም አጋጣሚ የቆጠሩ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች እና ሕገወጦች ይህን ከሌሎች ጎረቤት ሃገራት ጋር ሲነጻጸር በዝቅተኛ ዋጋ የሚሸጥ የነዳጅ ምርቷን እየሰረቁ ድንበር አሻግረው በጥቁር ገበያ እንዲሸጡ አድርጓቸው ቆይቷል ያሉት አቶ ሃሰን የዋጋ ማስተካከያው ከጎረቤት ሃገራት ጋር የችርቻሮ መሸጫውን ዋጋ ተመጣጣኝ ስለሚያደርገው ስርቆትን እንደሚያስቀር እና የነዳጅ ቦቴዎችን እንቅስቃሴ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመቆጣጠር የሚያስችል አሠራር መዘርጋቱንም ይፋ አድርገዋል። 

እንዳልካቸው ፈቃደ 

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ