1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነዳጅ ዘይት መወደድና የኤኮኖሚ ተጽዕኖው

ረቡዕ፣ ግንቦት 6 2000

የበርሚል ነዳጅ ዘይት ዋጋ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በአሥር ዕጅ በመጨመር ዛሬ ከመቶ ዶላር በልጦ ነው የሚገኘው። ሂደቱ በቅርቡ ሊገታ የሚችል ለመሆኑም ለጊዜው ጎልቶ የሚታይ ምልክት የለም።

https://p.dw.com/p/E0cD

የብዙዎች ግምት የዋጋው ንረት ቢቀር በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታትም ቀጣይነት ይኖረዋል የሚል ነው። ታዲያ ሂደቱ በዓለም ኤኮኖሚ ይዞታ ላይ አደገኛነቱ ምን ያህል ነው? የጥሬው ዘይት ክምችት እስከመቼ ይበቃል፤ የአምራች ሃገራት የዋጋ ተጽዕኖስ ወሣኝነቱ እስከምን ድረስ ነው? እነዚህ ጥያቄዎች ዛሬ በዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ላይ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ አነጋጋሪ የሆኑ ዓበይት ጉዳዮች ናቸው።

ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ላልታየለት ለዛሬው የነዳጅ ዘይት ዋጋ ንረት በርከት ያሉ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ። ሆኖም ዋናው ምክንያት የፍላጎቱ መጨመር ነው። የዓለምአቀፉ ፍጆት መጠን ያለማቋረጥ ወደ ላይ ማሻቀቡን ቀጥሏል። ታዲያ ነዳጅ ዘይት የዓለም ኤኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑ ሲታሰብ የዴካ ባንክ ባለሙያ ዶራ ቦርቤሊይ እንደሚሉት ሁኔታው በዕውነትም ለስጋት መንስዔ የሚሆን ነው። “በተለይ ራመድ ባሉት አዳጊ አገሮች ፍላጎቱ በተፋጠነ ሁኔታ ማደጉን ቀጥሏል። ከዚህ ሌላ ጃፓንንና አውሮፓን በመሳሰሉት የኢንዱስትሪ አካባቢዎችም ፍጆቱ እንደጠነከረ ነው የሚገኘው። በአንጻሩ ፍላጎቱ ደከም ያለባት አካባቢ አሜሪካ ብቻ ናት”

እንግዲህ አቅርቦቱ፤ ከፍጆቱ መጠን ጋር አብሮ ሊራመድ በሚችልበት ሁኔታ ላይ አይገኝም። በምድራችን ላይ ያለው የነዳጅ ክምችት የማያልቅ ዘላለማዊ ነገር አይደለም። ምርቱን ማውጣቱም ከብዙ ችግሮች ጋር የተሳሰረ ነው። በወቅቱ ለምሳሌ ናይጄሪያ ውስጥ የምርት መተጓጎል አለ፤ በሰሜን ባሕርም ተመሳሳይ ሁኔታ ነበር። እና በዚሁ ደግሞ ፍላጎቱ ከአቅርቦቱ በላይ እየሰፋ መሄዱ አልቀረም። ሌሎች ብዙ ምክንያቶችም ሊጠቀሱ ይችላሉ። አውሎ-ነፋስን የመሰለው የተፈጥሮ ቁጣ በሜክሢኮ ባሕረ-ሰላጤ መፈራረቁ ለዋጋው መናር አስተዋጽኦ አድርጓል። በዓለምአቀፉ የፊናንስ ገበያ ላይ ትርፍ አጋባሾች የሚፈጥሩት ውዥምብርም እንዲሁ የራሱ ድርሻ አለው። የጦርነቶች ተጽዕኖ ደግሞ እጅግ ከበድ ያለ ነው።
አብዛኛው የዓለማችን ዘይት የሚወጣው መካከለኛ ምሥራቅን ከመሰለው የውዝግብ አካባቢ ነው። ጦርነቶች ወይም ሽብርተኞች በነዳጅ ዘይት ቧምቧዎች ላይ ሊያደርሱት የሚችለው ጥቃት ገና ሳይደርስ በሃሣቡ እንኳ የምርት ተግባርን በማሰናከል የዋጋ ንረትን የሚያስከትል ነው። ለምሳሌ አሜሪካ በኢራቅ እንዳደረገችው ኢራንን ለመውረር ብትወስን ስጋቱ በገበዮች ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ በቀላሉ የሚገመት አይሆንም። ለዚህም ነው አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር የዋጋው ንረት በቅርብ መገታቱን ለማመን የሚያዳግተው።

ሌላው ነገር በምድራችን ላይ ያለው የነዳጅ ሃብት የሚያልቅ እንጂ ዘላለማዊ አለመሆኑ ነው። ያለ ጥቁሩ ወርቅ የኢንዱስትሪ ዕድገትና ብልጽግና በዓለም ላይ ሊኖር ባልቻለም ነበር። ነዳጅ ዘይት የብልጽግና ሞተር ነው። እና የክምችቱ እየተሟጠጠ መሄድ የተገኘው ብልጽግና ሁሉ እየጠፋ የመሄዱን ስጋት ይበልጥ ጥልቅ ያደርገዋል። ያለፈው አንድ ምዕተ-ዓመት የሰውልጅ የነዳጅ ዘይት ጥም በቀላሉ የማይረካ መሆኑ የተከሰተበት ነበር። መረጃዎችን ለመጠቆም ያህል ከ 1864 ዓ.ም. ወዲህ ከአርባ በመቶ የሚበልጠው ክምችት ከከርሰ-ምድር ተሟጦ ወጥቷል። አንዳንድ ጠበብት የሚናገሩት የፍጆቱ መጠን በአሁኑ መልክ ከቀጠለ የነዳጅ ዘይት ምንጮች በአርባ አመታት ውስጥ ተመጠው እንደሚያልቁ ነው።
እርግጥ ግምቱን የተጋነነ አድርገው የሚመለከቱም አሉ። የሆነው ሆኖ መጠኑን በተመለከተ ትክክለኛ ግምት መስጠቱ ቀላል ነገር አይሆንም። ቦርቤሊይ እንደሚያስረዱት ይህም ያለ ምክንያት አይደለም። “በአንድ በኩል የነዳጁ ክምችት መጠን የሚቀርበው በመንግሥታቱ በተናጠል ነው። በተለይ በመካከለኛ ምሥራቅ ዓለምአቀፍ ታዛቢዎች በክምችቱ ላይ ተጨባጭ ግምት እንዲወስዱ የሚፈቀድላቸው ባለመሆኑ ጉዳዩን ከባድ ያደርገዋል። ሌላው ነጥብ ክምችቱ ከዋጋው ጋር የሚያድግ መሆኑ ነው። ክምችቱ እንደ ክምችት የሚቆጠረው ከወቅቱ የቴክኖሎጂ ደረጃና ዋጋ ጋር በተጣጣመ መጠን ሊራመድ ሲችል ነው”

በሌላ በኩል በዓለም ላይ ገና ያልተነኩ የነዳጅ ምንጮች መኖራቸውም አንዱ ሃቅ ነው። ለምሳሌ በአፍሪቃ በአንዳንድ አካባቢዎች አዳዲስ ምንጮች ተከፍተዋል፤ ብዙ ክምችቶችን አውጥቶ ለመጠቀም የተያዘው ፍክክርና ሩጫም እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው። እርግጥ በወቅቱ በቂ ነዳጅ ጠፍቶ አይደለም፤ የፍላጎቱን ያህል እንዲወጣ አለመደረጉ እንጂ! ከዚሁም ሲሶው የሚገኘው በመካከለኛው ምሥራቅ ነው። በሌሎች የዓለም አካባቢዎችም በከርሰ-ምድርና በባሕር ውስጥ ሃብቱን ለማግኘት የሚደረገው ጥረት እንዲሁ ተስፋፍቷል።

በቅርቡ የነዳጅ ዘይት ክምችት ተገኘ ከተባለባቸው ቦታዎች አንዱ የብራዚል ደቡባዊ ጠረፍ አካባቢ ነው። ምንጩ ስምንት ሚሊያርድ በርሚል ዘይት እንዳለበት ሲነገር ይህም ከወቅቱ የዓለም ክምችት 2,5 ከመቶው መሆኑ ነው። ወደፊትም ተመሳሳይ ምንጮች ሊገኙ ይችላሉ። ይሁንና ችግሩ ነዳጁን የማውጣቱ ወጪ በጣም ከፍተኛ ሊሆን መቻሉ ላይ ነው። የብራዚሉ ዘይት አምሥት ኪሎሜትር ከባሕር በታች በጨው ድልድል ሥር የሚገኝ ሲሆን ከወቅቱ የቴክኖሎጂ ደረጃ አንጻር በምን ወጪና መቼ ለማመንጨት እንደሚቻል እንዲህ ብሎ ለመናገር ያዳግታል።

ወደ ዋጋው ንረት እንመለስና በጉዳዩ ወሣኝ ተጽዕኖ ያለው የነዳጅ ዘይት አምራች አገሮች ድርጅት ኦፔክ ነው። የድርጅቱ ዓባል ሃገራት ከዓለምአቀፉ ምርት አርባ በመቶውን የሚያወጡ ሲሆን ሶሥት አራተኛው የዓለም የዘይት ክምችት የሚገኘውም በነዚሁ ዕጅ ነው። 13 ዓባል መንግሥታትን ያቀፈው ድርጅት መቀመጫው በሆነችው በቪየና በየመንፈቁ ተሰብስቦ የዋጋ ተመን ያስቀምታል። ኦፔክ ምንም እንኳ መላውን አምራች መንግሥታት ባይጠቀልልም በዋጋ ውሣኔ ጉዳይ ሃያሉ ድርጅት ነው። ድርጅቱ በወቅቱ ምዕራባውያን መንግሥታት እንደሚጠይቁት ምርቱን ለማሳደግ ፈቃደኛ አይደለም።
የገበያው አቅርቦት የተሟላ ነው፤ የዋጋ መረጋጋት አዝማሚያም እየታየ ነው ይላል፤ የድርጅቱ ፕሬዚደንት የአልጄሪያው የነዳጅ ዘይት ሚኒስትር ቻኪብ ኬሊ በቅርቡ እንደገለጹት። “የድርጅቱ ውሣኔ አግባብ ያለው ነው። በገበያ ላይ እንዳለፉት አምሥት ዓመታት ሁሉ በቂ ዘይት አለ። እኛ እንዲያውም የምንጠብቀው ፍላጎቱ ጋብ እያለ እንደሚሄድ ነው”

የኦፔክ አምራች ሃገራት በወቅቱ እያሻቀበ በሚገኘው ዋጋ የበለጠ ገቢ በማግኘት ይቀጥላሉ ማለት ነው። በዓለም የፊናንስ ገበዮች የተፈጠረው ውዥምብር የሚያስከትለው የዋጋ ንረትም ለነርሱው ነው የሚበጀው። የዋጋ ፖሊሲያቸው ተጽዕኗቸውን ሃያል ያደርገዋል። ሃቁ ይህ ሲሆን የኦፔክ ፖሊሲ በዓለም ኤኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ግፊት ቀላል አይሆንም። የሰባኛዎቹ ዓመታት የነዳጅ ዘይት ቀውስ ያስከተለው ችግር ዛሬ በዋጋው ንረት ሳቢያ እንደገና የሚታወስ ነገር ሆኗል። ኦፔክ ያኔ የዘይት ቧምቧዎቹን ግጥም አድርጎ ሲዘጋ ዕርምጃው ወዲያው ለዋጋ ማሻቀብ ምክንያት ነበር የሆነው።
ዓለም፤ በተለይም የበለጸጉት ምዕራባውያን መንግሥት ከባድ የኤኮኖሚ ቀውስ ላይ ይወድቃሉ። የኑሮ ውድነት፣ የሥራ አጡ ቁጥር መጨመር የቀጣዩ ዓመታት ገጽታ ነበር። ዛሬስ እነዚህ አገሮች በነዳጅ ዘይት ላይ ጥገኝነታቸው እስከምን ድረስ ነው? ዛሬም ቢሆን በአብዛኞቹ በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉ አገሮች ጥሬ ዘይት እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ያለሱ የምርት ተግባራቸውን ለማከናውን አይችሉም። ለምሳሌ ፕላስቲክ ምርቶች፤ ቀለማ-ቀለምና የመንገድ ንጣፍ-ካትራሜ ሣይቀር ከሱ ነው የሚሰሩት። ፋብሪካዎች ጨርሶ ካላመረቱ ወይም በጥቂቱ ከተወሰኑ ብዙ የሥራ መስኮች ሊዘጉ ይችላሉ። ያለ ነዳጅ ዘይት ጠቅላላው የምርት ትራንስፖርትም መሰናከሉ ነው።

ከሰባኛዎቹ ዓመታት ቀውስ በኋላ እርግጥ የአማራጭ ኤነርጂ ምንጮች አስፈላጊነት የበለጠ ግንዛቤ አግኝቶ ቴክኖሎጂውም እንዲራመድ ተደርጓል። ችግሩ የሚገባውን ያህል ተስፋፍቶ የፍጆቱን ጉድለት ለመሸፈን ከሚበቃበት መጠን አለመድረሱ ላይ ነው። የኤኮኖሚው ባለሙያ ክላውስ ብራይል እንደሚሉት የኤነርጂ አጠቃቀም ብቃት ከዘመናዊው ቴክኖሎጂ ዕርምጃ ጋር ቢሻሻልም በነዳጅ ዘይት ላይ ያለው ጥገኝነት በቀላሉ የሚለወጥ አይሆንም። “ኤኮኖሚው አሁንም በዘይት ላይ ጥገና ሆኖ ይቀጥላል። በአማራጭ የኤነርጂ ምንጮች የነዳጅ ዘይት ጥገኝነቱን መቀነሱ አዝጋሚ ሂደት የሚኖረው ጉዳይ ነው”

ይህም በገበያው ኤኮኖሚ ሂደት ላይ ጎጂ እንደሚሆን አያጠያይቅም። የነዳጅ ዘይት ዋጋ በጨመረ ቁጥር ኩባንያዎች ለምርቱና ለትራንስፖርት የበለጠ ገንዘብ ማፍሰስ ይኖርባችዋል። ይህን ተጨማሪ ወጪ ለምሳሌ አንዳንድ አየር መንገዶች እንደሚያደርጉት በመንገደኛው ላይ የኬሮዚን ግብር በመጫን ጥቂትም ቢሆን ሸክሙን ለማቃለል ይቻላል። ግን ፍቱንነቱ ውሱን ነው። ኩባንያዎችን ሊገጥማቸው የሚችለው ሌላው ዋናው ግፊት የሚመነጨው ከደምበኞቻቸው አኳያ ነው። ተጠቃሚው በነዳጅ ዘይት መወደድ የተነሣ ለክረምት ወራት የቤት ማሞቂያና ለቤንዚን የበለጠ ገንዘብ እንዲያወጣ ከተገደደ ፍጆቱን ከመቀነስ ሌላ ምርጫ አይኖረውም። የፍጆት ምርቶች ፍላጎት ያቆለቁላል ማለት ነው። በአጠቃላይ ከነዳጅ ዘይት ጥገኝነት ለመላቀቅ አማራጭ ምንጮችን ማዳበሩ ከመቼውም በላይ ግድ እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም።