1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነዳጅ ዘይት ዋጋ መናርና ተጠቃሚ፤ ተጎጂው

ሐሙስ፣ ጳጉሜን 3 1997
https://p.dw.com/p/E0eO

ባለፈው ሣምንት በበርሚል ከሰባ ዶላር በላይ ሆኖ በነበረው የነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር በወቅቱ ተጠቃሚ የሆኑትና በትርፍ መዋኘት የያዙት በእጣት የሚቆጠሩ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎችና በተወሰነ ደረጃም ጥሬ ምርት አቅራቢዎቹ አገሮች ብቻ ናቸው። ይህ ሁኔታ ችግር ያስከተለው ታዲያ በነዳጅ ዘይት ላይ በሰፊው ጥገኛ በሆኑት በምዕራቡ ዓለም ኢንዱስትሪዎች ላይ ብቻ አይደለም። በዚህ የተፈጥሮ ሃብት ባልታደሉት ታዳጊ አገሮች ጭምር የልማትና የኤኮኖሚ ዕድገት ተሥፋን የሚያደበዝዝ ነው የሆነው።

የዓለም ኤኮኖሚ ቢቀር ካለፉት አሥር ዓመታት ወዲህ ተጎታች ወይም አዝጋሚ ዕድገት ሲታይበት ነው የቆየው። በተለይ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸገው ዓለም በአማካይ ከሁለት በመቶ ባልበለጠ ዕድገት ተወስኖ መቆየቱ ለቆረቆዘው ሁኔታ ዋነኛው ምክንያት ነው። ይህ ሂደት ደግሞ አሁን የታዳጊው ዓለም ሁኔታ ለሚጠይቀው አጣዳፊ ዕርምጃ መሰናክል ሊሆን መቻሉ ብዙ አያጠያይቅም።

የምዕራቡ ዓለም ችግር የዓለም ኤኮኖሚን ወደ ኋላ የሚጎትት ብርቱ አደጋ ላይ እንዳይጥል እያሰጋ መምጣቱን የተባበሩት መንግሥታት የንግድና ልማት ጉባዔ ሰሞኑን ባወጣው ዓመታዊ ዘገባ አመልክቷል። ዘገባው እንደሚለው የዓለም ኤኮኖሚ ምንም እንኳ በተወሰነ መጠን መስፋፋቱን ቢቀጥልም የዕድገቱ ሂደት በዚህ ዓመት ከተጠበቀው ለዘብ ብሎ መገኘቱ ማስጠንቀቂያ ሊሆን የሚገባው ነው።

በዚሁ በአሕጽሮት ዩንክታድ እየተባለ በሚጠራው ተቋም ዘገባ መሠረት ዋነኛው የዓለም ኤኮኖሚ አንቀሳቃሽ መንኮራኩር የአሜሪካ ኤኮኖሚ ሌሎች አገሮች ወይም አካባቢዎች ይህን ሚና ለመያዝ ከመብቃታቸው በፊት እስትንፋሱን እንዳያጣ በጣሙን ነው የሚያሰጋው። እስካሁን ለዚህ ግንባር-ቀደምነት ሚና ጥያቄ ውስጥ የሚገቡት የአውሮፓው የምንዛሪ ሕብረት አገሮች ለረጅም ጊዜ ተጭኗቸው ከቆየው የምጣኔ-ሐብት ዕድገት ድቀት ሊላቀቁ አልቻሉም። ጃፓንም ጥቂት ታገግም እንጂ የኤኮኖሚ ቀውሷን ገና ጨርሳ ልታስወግድ በቅታ አትገኝም።

የበለጸገው ዓለም ሃቅ በወቅቱ ይህን የመሰለ ሲሆን በአንጻሩ አዳዲስ የኤኮኖሚ ዕድገት ሞተሮች እየሆኑ በመገስገስ ላይ የሚገኙት አገሮች ቻይናንና ሕንድን የመሳሰሉ ጥቂት መንግሥታት ብቻ ናቸው። በምዕራቡ ዓለም በተለይ በአውሮፓውና በጃፓን ለዕድገቱ መጓተት ምክንያቱ በአብዛኛው የአሜሪካ የበጀት ኪሣራ ነው። የአሜሪካ የንግድ ኪሣራ ባለፈው ዓመት ከ 660 ሚሊያርድ ዶላር በላይ የናረ ነበር። ይህም ከአገሪቱ አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት አንጻር ስድሥት በመቶ ያህል መሆኑ ነው።

ዋሺንግተን ኪሣራውን ለማለዘብ ከዚህ ቀደም እንደታየው የዶላርን ዋጋ በሰፊው ዝቅ ካደረገች በአውሮፓና በእሢያ አገሮች ላይም የሚያስከትለው ችግር ቀላል አይሆንም።
እርግጥ የአሜሪካ መንግሥት የበጀት ኪሣራው ያስከተላቸውንና ወደፊት የሚከተሉትንም ችግሮች በሚገባ ያውቃል። ዋሺንግተን ለራሷ የውጭ ንግድ ራሷ በምታትመው ምንዛሪ የምትገለገል በመሆኗም ኤኮኖሚዋ ኪሣራውን በተሻለ ሁኔታ ሊቋቋም መቻሉ ሌላ ውሃቅ ነው።

ብዙዎች አገሮች ወደ ውስጥ ለሚያስገቡት ገንዘብ የውጭ ምንዛሪን ማግኘት ወይም መበደር ስለሚኖርባቸው ይህን መሰሉ የአሜሪካ ዕድል የላቸውም። የአሜሪካ የበጀት ኪሣራ እስከምን መጠን ሊሄድ እንደሚችል ከወዲሁ ለመገመት አይቻልም። ይሁን እንጂ ለዘለቌታው እየጨመረ መሄድ ግን የሌለበት ጉዳይ ነው።

ለበጀቱ ኪሣራ ማደግ አንቀሳቃሽ ሞተር ሆነው የሚገኙት የአገሪቱ የውጭ ንግድ አዝጋሚ ሂደትና እየተፋጠነ ከሄደው የተጠቃሚው ሕዝብ ፍጆታ ጋር እያደገ የመጣው ወደ አገር የሚገባ ምርት መጨመር ናቸው። በአሜሪካ የአገር ውስጡ ፍጆታ ለዓመታት ሲበዛ ከፍተኛ ሆኖ ነው የቆየው።
የየቤተሰቡ ነፍስ-ወከፍ የቁጠባ ይዞታ ያቆለቆለና በዕዳ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ሁኔታው በዚህ መልክ እንደማይቀጥል ጠበብት ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል። የሆነው ሆኖ ዋሺንግተን ውስጥ ሰሚ ጆሮ አላገኙም። ይህ ሂደት ከቀጠለ በአንድ ወቅት የአገሪቱን የባንክ ሥርዓት ብርቱ ችግር ላይ እንዳይጥል በጣሙን ያሰጋል። ከሆነ የሚያስከትለው ውጤት ደግሞ የወለድን መጨመር ወይም ማደግ ነው የሚሆነው።
ታዲያ ይህ ከነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ ዕዳ ተከምሮባቸው የሚገኙት ዜጎች አንዴ ይህንኑ መክፈል ከማይችሉበት ደረጃ እንዲደርሱ ማድረጉ የሚቀር አይመስልም። አደገኛ አዝማሚያ ነው፤ የተጣጣመና የተፋጠነ መፍትሄን ይጠይቃል። ከታዳጊው ዓለም አንጻር አበረታች ሆኖ የሚታይ ነገር ቢኖር የቻይናና የሕንድ የተፋጠነ ዕድገት ሌሎችን የማዳረስ አዝማሚያ መያዙና የረጅም ጊዜ ጽናት ማሣየቱ ነው።

ሌላው ለብዙዎች አገሮች ቀውስ መንስዔ የሚሆን ሊጠበቅ የሚችል ሂደት ደግሞ ቻይና ምንዛሪዋን ለልውውጥ ነጻ ለማድረግና ተመኑን ከፍ ለማድረግ መነሣቷ ይሆናል። ቢሆን እርግጥ ቻይናም ራሷ በዚህ ሂደት ተጎጂ ነው የምትሆነው። ይህ እርግጥ ከዚህም አልፎ ለዓለምአቀፉ ንግድም የሚበጅ አይሆንም።

ሕዝባዊት ቻይና የምንዛሪዋን ተመን ከፍ ብታደርግ ዕርምጃው እያበበ የመጣው የአገሪቱ የውጭ ንግድና የኤኮኖሚ ዕድገት እንዲያበቃ ወይል እንዲገታ የሚያደርግ ነው የሚሆነው። ይህ ደግሞ በብዙዎች ታዳጊ አገሮች ላይ የሚያስከትለው ችግርም ይኖራል። ምክንያቱም የቻይና የጥሬ ምርት ፍላጎት መጨመር በዓለምአቀፍ ደረጃ ዋጋን በማሳደጉ የምርቱ አቅራቢዎች በሁኔታው መለወጥ ተጎጂ ሊሆኑ ነው።

ለምሳሌ ያህል ብራዚልና ደቡብ አፍሪቃ በጥሬ ብረት፣ ቺሌ፣ ፔሩና ዛምቢያ ደግሞ በመዳብ ዋጋ ማደግ በወቅቱ ተጠቃሚ ሆነው የሚገኙት አገሮች ናቸው። በቻይና የኤኮኖሚ ዕድገት መፋጠን ባለፉት ዓመታት በአፍሪቃና በላቲን አሜሪካ የውጭ ንግዱ ዋጋ ወደ ውስጥ ከሚገባው ምርት ተመን ይልቅ የተሻለ ዕርምጃ ታይቶበታል። ከዚህ አንጻር የቻይና ዕርምጃ ማክተም ማለት ታዳጊ አገሮች ድህነትን ለማለዘብ የሚያደርጉትን ትግል ማክበድ ማለት ነው የሚሆነው። ስለዚህም ዛሬ በቻይናም ሆነ በሕንድ የሚታየው የተፋጠነ ዕድገት ሕያው ሆኖ መቀጠል የሚገባው ነው።

በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት በበኩላቸው የአሜሪካን የንግድና የበጀት ኪሣራ ለማለዘብ ምን ዓይነት ዕርምጃዎች መውሰድ እንደሚገባቸው ጤናማ መስፈርትን በጠበቀ ሁኔታ ከልብ ማጤን ይጠበቅባቸዋል። በዓለም ንግድ ላይ የተፈጠረውን የሚዛን ዝቤት ለማስተካከል የሚቻለው ዕርምጃዎቹ የጋራ ጥቅምን ያስተዋሉና እርጋታ የሰፈነባቸውም ሲሆኑ ብቻ ነው።

በሌላ በኩል በዓለም ገበዮች ላይ የሰፈነው የጥሬ ነዳጅ ዘይትና የቤንዚን ዋጋ ከዚህ ቀደም ባልታወቀ መጠን እየናረ መምጣት ሲታሰብ የዓለም ኤኮኖሚ ጤናማ ዕድገት ይዞ መራመድ መቻሉን ቢቀር በወቅቱ አጠያያቂ ያደርገዋል። በዋጋው መናር ወርቃማ የትርፍ ማግበስበዝ ዘመን የተከፈተላቸው በዕጣት የሚቆጥሩት ዓለምአቀፍ ነዳጅ ዘይት አጣሪና ሻጭ ኩባንያዎች ናቸው።
እነዚሁ ኩባንያዎች በያዝነው 2005 ዓ.ም. የመጀመሪያ አጋማሽ ብቻ ትርፋቸውን ሰላሣ በመቶ ከፍ አድርገዋል ነው የሚባለው። ሂደቱ ቀጣይ ለመሆኑም አንድና ሁለት የለውም። 120 ሚሊያርድ ዶላር! ይህ የፖርቱጋልን አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት የሚያክለው ገንዘብ ሥምንት ታላላቅ የነዳጅ ዘይት ኩባንያዎች በዚህ ዓመት ያስገቡት ትርፍ ነው።
ኤክሶን ሞቢል ለብቻው በተመሳሳይ ጊዜ ሰላሣ ሚሊያርድ ዶላር አትርፏል። ይህም ቢሆን በዓለምአቀፍ ደረጃ ሁለት-ሶሥተኛ የሚሆኑ አገሮች ያሣዩትን የኤኮኖሚ ጥንካሬ የሚያስከነዳ ነው። ሚስጥሩ ምንድነው? በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸገው የምዕራቡ ዓለም ከሰባኛዎቹ ዓመታት ቀውስ ወዲህ ይህን መሰሉን ችግር ያየበት ጊዜ አይታወስም። ያኔ የአምራች አገሮች የነዳጅ ዘይት እገዳ ነበር የችግሩ መንስዔ።

ከዚያም የፋርስ ባሕረ-ሰላጤው ጦርነት በምርቱ ዋጋ ሂደት ላይ የአጭር ጊዜ ተጽዕኖ አስከትሎ አልፋል። ዛሬ ተጠቃሚው ኪሱን እንዲያማጥጥ መገደዱ በተለይ በዓለም ላይ የነዳጅ ዘይት ፍላጎት እየጨመረ በመሄዱ ነው። በቀን ሃያ ሚሊዮን በርሚል ነዳጅ ዘይት ለፍጆት ይቀርባል። በዓለምአቀፍ ደረጃ ከሚያስፈልገው ዘይት ሩቡን የምትፈጀው ዛሬም አሜሪካ ናት። ግን የጥሬ ሐብት ጥሟ የጠነከረው ቻይናም ሚዛኑን እየቀየረች በመሄድ ላይ ነው የምትገኘው።
ዛሬ ቤይጂንግ ውስጥ ብቻ በየቀኑ 1,500 አዳዲስ አውቶሞቢሎች አደባባይ ይወጣሉ። ሕዝባዊት ቻይናና በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙ መሰል ለሚ አገሮች በወቅቱ ኢንዱስትሪያዊ ዓብዮትን በማራመድ ላይ ነው የሚገኙት። ከዚህ የተነሣ ዓለም ምናልባት በያዝነው ዓመት መጨረሻ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሚመረተው የበለጠ ነዳጅ ዘይት የመፍጀት ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችል ይሆናል።

ይህም የሚያመላክተው የነዳጅ ዘይት ዋጋ የመናር ሂደት በቅርብ መገታቱ አጠራጣሪ መሆኑን ነው። ይሁንና ታላላቁ ኩባንያዎች ሁኔታውን በመጠቀም የሚያካሂዱት ከዝርፊያ እምብዛም ያልተለየ የተጋነነ የትርፍ ማግበስበስ ዘመቻ ሊገታ መቻል ይኖርበታል።

ዛሬ በዚህ በምዕራቡ ዓለም አምራቹ ኢንዱስትሪ ብቻ ሣይሆን አውቶሞቢል አሽከርካሪውና ተጠቃሚው ሕዝብ በነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር ሳቢያ ከባድ የኑሮ ውድነት ተጭኖት ነው የሚገኘው። በነዳጅ ዘይት መወደድ የተነሣ የቤት ማሞቂያው ዘይት፣ የቁሳቁሱና በአጠቃላይ ገበያ ላይ የሚቀርበው ምርት ዋጋ ከመጠን በላይ ንሯል። እየተቃረበ ባለው ክረምት ነዋሪው ለቤት ማሞቂያ ከዚህ ቀደም ከነበረው ወጪ ሰላሣ በመቶ ከፍ ያለ ገንዘብ መክፈል ሳይኖርበት የሚቀር አይመስልም።
ይህ ደግሞ ሲበዛ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ነው። የነዳጁ መወደድ ብዙዎች ፋብሪካዎች እንዲከስሩና እንዲዘጉ፤ ወይም ሠራተኛ እንዲያሰናብቱ ሊያደርግ ስለሚችልም በሥራ አጥ ብዛት በተወጠሩት ጀርመንን በመሳሰሉት አገሮች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው የሚሆነው። ሕብረተሰቡ ነጻ የገበያ ኤኮኖሚ ሥርዓት የሰፈነበት ቢሆንም ጥቂት ኩባንያዎች ያላግባብ ትርፍ ሲያካብቱ ዝም ብሎ መመልከቱ ተገቢ አይሆንም። መንግሥታት ከመለመንና ከማግባብ አልፈው ፍቱን ተጽዕኖ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፤ መቻልም አለባቸው።