1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነዳጅ ፍጆት መጨመርና የዋጋው መናር ችግር

ረቡዕ፣ መጋቢት 3 2000

የነዳጅ ዘይት ፍጆት መጨመርና የዋጋውም መናር ዛሬ በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ብርቱ ፈተና ከደቀኑት ችግሮች አንዱ ነው። በበርሚል መቶ ዶላር የደረሰው የነዳጅ ዋጋ በርከት ባሉ አገሮች ከባድ የኑሮ ውድነትን ሲያስከትል ዕድገትንና የሥራ መስኮች ከፈታን አንቆ መያዙም አልቀረም።

https://p.dw.com/p/E0cL
ምስል AP

በአሕጽሮት ኦፔክ በመባል የሚታወቀው የነዳጅ ዘይት አምራች ሃገራት ድርጅት በዚሁ ጉዳይ ለመነጋገር ባለፈው ሣምንት መቀመጫው በሆነችው በአውስትሪያ ርዕሰ-ከተማ በቪየና ተሰብስቦ ነበር። በሚኒስትሮች ደረጃ የተካሄደው ስብሰባ የምርቱ ኮታ ከፍ በሚልበት ሁኔታ መክሮ መፍትሄ ያመላክታል ተብሎ ነበር የተጠበቀው። ተገልጋዮቹ ሃገራትም በኮታው መጨመር ችግራቸው እንደሚለዝብ ተሥፋ ማድረጋችው አልቀረም። ግን አልሆነም።

የኦፔክ ተጠሪዎች እየተፋጠነ ለሄደው የነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር የቅርቡን ዓለምአቀፍ የፊናንስ ቀውስና የዩ.ኤስ. አሜሪካን ምንዛሪ የዶላርን መዳከም ተጠያቂ አድርገዋል። በዚሁ የተነሣም ያለፈው ሣምንት የድርጅቱ የሚኒስትሮች ስብሰባ በተሥፋ የተጠበቀውን ለውጥ አላስከተለም። የኦፔክ ሃገራት የምርት ኮታችውን ባለበት ማቆየቱን ነው የመረጡት። ይህ ደግሞ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉትን ፈጂ አገሮች ቅር ማሰኘቱ አልቀረም። ሁኔታው አማራጭ መፍትሄ የመፈለጉን ጥረት፤ በአምራቾቹ ሃገራት ላይ የሚደረገውን ተጽዕኖም ይበልጥ የጠነከረ ያደርገዋል።
በተለይ ከአሜሪካ በኩል የሚደረገው ግፊት አይሎ መቀጠሉ የማይቀር ጉዳይ ነው። መለስ ብሎ ለማስታወስ ያህል ፕሬዚደንት ጆርጅ-ደብልዩ-ቡሽ ባለፈው ጥር ወር መካከለኛ ምሥራቅን ሲጎበኙ ወደ አካባቢው ብቅ ያሉበት ዓላማ የእሥራኤል-ፍልሥጤሙን የሰላም ጥረት ወደፊት ማራመድ ወይም ለዋሺንግተን የኢራን ፖሊሲ ድጋፍ መሰብሰብ ብቻ አልነበረም። ነዳጅ ዘይት፣ የዋጋው ከመጠን በላይ እየናረ መሄድና በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ያስከተለው ተጽዕኖም የውስጥ አጀንዳቸው ነበር። እናም የኦፔክ ቀደምት ዓባል በሆነችው የሳውዲት አረቢያ ጉብኝታቸው የማያሻማ ማስጠንቀቂያ ነበር የሰነዘሩት። “ዋና የነዳጅ አቅራቢያችን የሆነው ኦፔክ ስለ አዲስ የምርት መጠን በሚወያይበት ጊዜ የኛ ኤኮኖሚ በተጎዳ ቁጥር የርሱም ሽያጭ እያቆለቆለ እንደሚሄድ ይገነዘባል ብዬ ተሥፋ አደርጋለሁ”

ሳውዲዎች እርግጥ በቡሽ ማስጠንቀቂያ ብዙም አልበረገጉም። ይሁንና አባባላቸው በሌሎች ዘንድ የቀድሞ ትውስትን መቀስቀሱ አልቀረም። የነዳጅ ዘይት ዋጋ በሰባኛዎቹ ዓመታት በበርሚል ከሶሥት ዶላር ያነሰ ነበር። ዛሬ ግን በብዙ ዕጅ በመጨመር መቶ ዶላር ገደማ ደርሷል። በዚህ አያበቃም፤ የዋጋው ንረት ወደፊትም ቀጣይ እንደሚሆን ነው የሚታመነው። ብዙዎች ይህን የዋጋ ማሻቀብ እ.ጎ.አ ጥቅምት 1973 ዓ.ም. የመካከለኛ ምሥራቅ ጦርነት ወቅት የኦፔክ የነዳጅ እገዳ የድርጅቱ የተጽዕኖ መሣሪያ እንደሆነ ነው የሚያምኑት።

ምዕራባውያን መንግሥታት በነዳጅ ዘይት አምራቾቹ ሃገራት ድርጅት በኦፔክ ውስጥ ይህን መሰሉን ስጋት ለማስፋፋትና ሃላፊነት የተመላበት የኤነርጂ ፖሊሲን ለማራመድ የተነሱ ለማስመሰል ጥረት ይደረጋል ሲሉ ይወቅሳሉ። ሆኖም የአልጄሪያው የነዳጅ ዘይት ሚኒስትር ቼኪብ ኬሊል ሁኔታውን እኒህ ያቃልሉታል።“አቅርቦቱ ፈላጊ ካለ ምንጊዜም የሚረጋገጥ ጉዳይ ነው። ስለዚህም የዓለም ኤኮኖሚ በነዳጅ እጥረት ሳቢያ ችግር ላይ ይወድቃል ብሎ ማሰቡ አስፈላጊ አይደለም። ይልቁንም በወቅቱ የምናየው በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው የፊናንስ ሁኔታ ነው ለስጋት መንስዔ ሊሆን የሚገባው”

የነዳጅ ዘይት አምራቾቹ ሃገራት ድርጅት ኦፔክ የተቋቋመው እ.ጎ.አ. በመስከረም ወር 1960 ዓ.ም. ባግዳድ ላይ ነበር። መስራቾቹ አምሥት ሃገራትም ኢራቅ፣ ኢራን፣ ኩዌይት፣ ሳውዲት አረቢያና ቬኔዙዌላ ነበሩ። ኦፔክ ዛሬ 13 ዓባል ሃገራት ሲኖሩት እነዚሁም በዓለም ላይ ሩቡን የነዳጅ ዘይት ሃብትና የምርቱን አርባ በመቶ ድርሻ የሚቆጣጠሩት ናቸው። በምሥረታው ወቅት የኦፔክ ዋና ዓላማ የነዳጅ ምንጮች በመንግሥት ይዞታ ስር እንዲሆኑ ማድረግና የምርት መጠኑንም መወሰን መቻል ነበር። ግን ይህ ዓላማ በታሰበ መልኩ ገቢር ሊሆን አልቻለም። እርግጥ ከዚህ በላይም ነበር የሚታሰበው። የጊዜው የኢራን ገዢ ሻህ ፓህሌቪ ቴህራን ውስጥ በ 1971 በተካሄደ የኦፔክ ስብሰባ ላይ እንዲህ ነበር ያሉት። “የሚመረጠው በራሳችን ማምረት፣ በራሳችን ማጣራትና የተለያዩ ምርቶችን ለማውጣት ብንችል ነበር”

ግን አልሆነም፤ ዛሬም ታላላቅ ምዕራባውያን ነዳጅ ዘይት አውጭ ኩባንያዎችና ድርጅቶች ናቸው ገበያውን የሚቆጣጠሩት። ለማንኛውም በኢራን የሻሁ ከሥልጣን መውረድና የእሥላማዊው ዓብዮት መከተል ከዚያም ብዙ ሳይቆይ የፈነዳው የኢራንና የኢራቅ የስምንት ዓመታት ጦርነት የነዳጅ ዘይቱ ዋጋ ለጊዜውም ቢሆን እንዲንር ያደርጋሉ። እርግጥ አዳዲስ የነዳጅ ምንጮች በመከፈታቸውና ከኦፔክ ውጭ የሆኑ አምራች ሃገራትም ገበያ ላይ ብቅ በማለታችው ዋጋው መልሶ መውረዱ አልቀረም። በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታትም አማራጭ ገበያ እንዲሹ ሁኔታው ይበጃቸዋል።

ግን ይህ የማገገም ሁኔታ ብዙ ዕድሜ አልነበረውም። ጦርነቶችና ቀውሶች እንደገና የፍጆተኛው ፍላጎት ከፍ እንዲል ያደርጋሉ። በተለይም ሩቡን የነዳጅ አቅርቦት የምትፈጀው የቻይና የተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፤ አለውም። በዚህ የተነሣ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ብቻ በእጥፍ ገደማ ነው ያደገው። ምንም እንኳ በአንጻሩ የነዳጁ ክምችት ከፍ ቢልም!
ከዚህ የተነሣ የኦፔክ ሚና እየተለወጠ ነው የመጣው። ድርጅቱ የአምራቾቹ ሃገራት የትግል መሣሪያ በመሆን ፈንታ ለፈጂዎቹ እንደ አጋር ሆኖ ለመታየት ነው የሚሻው።

ከያቅጣጫው የሚሰነዘርበትን ወቀሣም ለማርገብ ይጥራል። የድርጅቱ ጠቅላይ ጸሐፊ አብዱላህ-አል-ባድሪ፤ “በመጀመሪያ የምንመለከተው እርግጥ የዓባል አገሮቻችንን ጥቅም ነው። ግን ሚዛን የጠበቀ ገበያን ለማየትም እንፈልጋለን። ለገበያ እጥረት እንደቆምን ሆነን መታየት የለብንም። እና የገበያው ፍላጎት ሲሆን ምርታችንን ከፍ ወይም ዝቅ ከማድረግ ወደ ኋላ አንልም”

ሃቁ ባለፈውም ሣምንት የኮታው መጠን ባለበት ተገትቶ መቀጠሉ ነበር። የነዳጅ ዘይት ዋጋ በከፍተኛ መጠን መናር ከትራንስፖርትና ከእርሻ ምርቶች ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ በተለይ በታዳጊው ዓለም ላይ ነው ብርቱ ፈተና የደቀነው። መሠረታዊ የሆኑ የዕለታዊ ፍጆት ዕቃዎች ለምሳሌ የምግብ ምርቶች ለተራው ሕዝብ ከአቅም በላይ እየሆኑ ሄደዋል። ሩቅ ሳንሄድ ዛሬ በኢትዮጵያ እንኳ ጤፍና በርበሬን የመሳሰሉት ዕለታዊ መገልገያ ምርቶች የደረሱበት ሰማይ-ጠቀስ ዋጋ ራስ ምታት የሚያስይዝ ነው። በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ዜጋና የቀን ተዳዳሪው ድሃ ኑሮውን እንዴት እንደሚገፋ መረዳቱ ያዳግታል።