1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነገሥታቱ ሐውልቶች እና ሌሎችም

ዓርብ፣ የካቲት 8 2011

​​​​​​​የአፍሪቃ ኅብረት ቅጥር ግቢ የቆመው የዓጼ ኃይለ-ሥላሴ መታሰቢያ ሐውልት እሳቸውን ይመስላል አይመስልም የሚል ውዝግብ አስነስቷል። የአማርኛ ቋንቋ የአፍሪቃ ኅብረት ይፋዊ ቋንቋ ኾነ የሚል የተሳሳተ መረጃን በርካቶች ተቀባብለውታል። በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ቀጥለዋል። የሳምንቱ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ይመለከታቸዋል።

https://p.dw.com/p/3DPWX
Äthiopien - Die Afrikanische Union enthüllt eine Statue von Haile Selassie.
ምስል Bekele Mekonnen

«ሐውልቱ እሳቸውን ይመስላል አይመስልም?»

በአፍሪቃ ኅብረት ቅጥር ግቢ የተተከለው የአጼ ኃይለ-ሥላሴ ሐውልት በትክክል እሳቸውን አይመስልም፤ ግርማ ሞገሳቸውም ዐይታይበትም የሚል ቅሬታ በሳምንቱ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ተንጸባርቋል። በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የነገሥታቱ ሐውልቶች ላይ ጉዳት መድረሱ በስፋት አነጋግሯል። የአማርኛ ቋንቋ የአፍሪቃ ኅብረት ይፋዊ ቋንቋ ኾነ በሚል የተሰራጨው የተሳሳተ መረጃም ሌላኛው ዐቢይ መነጋገሪያ ነበር። እዚህም እዚያም የሚያገረሹ ግጨቶች ብዙዎችን አሳስበዋል።

የነገሥታቱ ሐውልቶች

ባለፈው ሳምንት የብዙዎችን ቀልብ እጅግ የሳበው ጉዳይ 32ኛው የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ አልነበረም። ጉባኤው በአፍሪቃዪቱ መዲና አዲስ አበባ ሲካሄድ ከግማሽ ምእተ ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። ይልቁንስ በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎችን ያስደመመው በአፍሪቃ ኅብረት ቅጥር ግቢ ለመታሰቢያ የቆመው የአጼ ኃይለሥላሴ ሐውልት ጉዳይ ነበር፤ የበርካቶች መነጋገሪያ ኾኖ ሰንብቷል።

ሐውልቱ የግርማዊ አጼ ኃይለሥላሴን ግርማ እና ሞገስ የማያንጸባርቅ እና እሳቸውን የማይመስል ነው የሚሉ አስተያየቶች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት ተሰራጭቷል። ሀውልቱ በኢትዮጵያዊ ቀራጺ በመሠራቱ ምስጋና ያቀረቡም ነበሩ። ጭራሽ ሐውልት ሊቆምላቸው አይገባም ነበር ሲሉ የሞገቱም አልጠፉም። የኹሉንም አስተያየት ሰብሰብ አድርገን ለማቅረብ እንሞክራለን።

በማኅበራዊ መገኛኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን በተለይ ንጉሡን አይመስሉም የሚሉትን እንዳነበቧቸው የገለጡት የሐውልቱ ቀራጺ ተባባሪ ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን በፌስ ቡክ ገጻቸው ዘለግ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ተቺዎቹን፦ «መልኩ አልመሰለም ባዮቹ በጠቅላላ ንጉሱንም ሆነ የተሰራውን ሀውልት ለደቂቃ ባይናቸው አይተው የማያውቁ መሆኑን አረጋገጥን» ሲሉ ጽፈዋል። 

Äthiopien - Die Afrikanische Union enthüllt eine Statue von Haile Selassie.
ምስል Bekele Mekonnen

ለሐውልቱ ቀራጺ የፌስቡክ ጽሑፍ መልስ የሰጠው ወሰን ዘሪሁን፦ «ትችቱን በቅንነት ማየት አይጎዳም» በማለት ጽሑፉን ያንደረድራል። «የፊታቸው መጠን ከሰውነታቸው ጋር ሲመዛዘን (proportionality) በሐውልቱ ላይ ከሚታየው ከፍ ያለ፣ ጺም ያለበትና ለግርማቸው ትልቅ አስተዋፅዖ ያለው መሆኑ የተዘነጋ ይመስላል። በሐውልቱ ዕድሜያቸው አነስ፣ አንገታቸው ረዘም ብሏል። በዚህም ምክንያት የአንገታቸው መርዘም ከፊታቸው ማነስ፣ ከሚታየው ዕድሜ ማነስና ኮት ብቻ ከመልበሳቸው ጋር ተደምሮ የምናውቀውን ግርማ አላየንበትም መባሉ ትክክል ነው። በፎቶግራፉ ላይ የሚታየው ዘና ማለታቸውም በሐውልቱ ላይ አይታይም። ምናልባትም የሚታየው ተቃራኒው ነው» ሲል ዝርዝር ነገሮችን ጽፏል።  «በተረፈ ግን ዋናው ነገር ሐውልታቸው እንዲቆም መወሰኑ ስለሆነ የሚስተካከለውን ተነጋግሮ ማስተካከል ነው» ሲልም አክሏል።

«ከእሳቸው አንድ ብር እና ዳቦ ብዙ ጊዜ ተቀብያለሁ ትንሽ ልጅ ኾኜ፤ ህጻን ልጅ ኾኜ» ያሉት ቀራጺው ሐውልቱን ለመሥራት ጥልቅ ጥናት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።  መሐሪ ዲነግዴ፦ «እኔ ሀውልቱን ሄጄ በቅርበት አይቼዋለሁ» በማለት በፌስቡክ ጽሑፉ ትችቱን ሰንዝሯል። «ልብሳቸው የተጣበቀ፤ ፂም የሌላቸው ባጠቃላይ በመሸማቀቅ ነው ያየሁት» ብሏል። በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተሠራው የአጼ ምንሊክ ሀውልት አስደማሚነቱን ለንጽጽር በማቅረብ፦ «ሀውልቱ እንደገና ይሰራ መልእክቴ ነው» ሲል ጽሑፉን ቋጭቷል።

ተስፋዬ ወልደየስ በትዊተር ገጹ በእንግሊዝኛ ባሰፈረው ጽሑፉ የሐውልቱ ቀራጺን አድንቋል። «ተባባሪ ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን በንጉሠ ነገሥት ኃይለሥላሴ ሐውልት ላይ ድንቅ ሥራ ነው የሠሩት። አንዳንዶች በመጥፎ የካሜራ ማእዘን የተወሰደ ምስል ተመልክተው በበቂ ኹኔታ ያልተሠራ ነው የመሰላቸው» በማለት አድናቆቱን አስፍሯል።

«ለአቶ በቀለ መኮንን» ሲል አስተያየቱን በፌስቡክ ያሰፈረው ቴዲ አበራ፦ «አንድ ኪነጥበብ ሲሰራ ሊያስተላልፈው የሚገባው ሀሳብ፣ ሊገልጸውና ሊገለጽበት የሚፈልገው ግብ አለው» በማለት ይቀጥላል። «አንድን ሀውልት ሱፍ አልብሰህ ስትሰራው ምን ለማለት ነው፡፡ አንገቱን ደፋ አድርገህ ስትሰራው ምን ለማለት ነው» ሲል ቀራጺውን ጠይቋል።

የሐውልቱ ቀራጺ በማኅበራዊ መገናኛ አውታራቸው ላይ ካሰፈሩት ረዘም ያለ ጽሑፍ ቀጣዩ እንዲህ ይነበባል። «አፍሪካን ለማስተባበር ወጥተው በወረዱበት ዘመን ሁሉ ጃንሆይ ይለብሱ የነበረው ሁሌም ጥቁር ወይም ግራጫ፡ ሱፍ በክራቫት ብቻ ነው። በአፍሪካ ህብረት እንግዳ፡ሲያስተናግዱም ሆነ ሲስተናገዱ አቁዋቁዋማቸውና፡ እጆቻቸው ሁሌም በዚህ መልክ ተመዝቦ የሚታወቅ መሆኑን ቤተሰባቸውን ጨምሮ በሁሉም ዘንድ ምክክር ከተደረገበት በኋዋላ የተወሰነ ነው።» 

Äthiopien - Die Afrikanische Union enthüllt eine Statue von Haile Selassie.
ምስል Bekele Mekonnen

አበራ ሞካ በፌስቡክ ጽሑፍ፦ «እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሐውልቱን የስሩትን ኢትዮጵያዊያን በመሆናችው ብቻ አደንቃችዋለሁ አመስግናችዋለሁ» ብሏል። «ሌላው በተስራው ስራ ላይ የስሪዎችን ብቃት ከምን እንደተስራ ሥራውን ለመስራት የተጠቀሙበትን ሂደቱን ስንስማ ከማክበር በቀር ሥራውን የመተችት ሞራሉም ብቃቱም የለንም» ሲል አክሏል። ቢንያም ካሣሁን በተቃራኒው፦ «አንድ ብር ላይ ያለውን ልጅ ነው ሚመስለው» ሲል ጽፏል። 

«ግን ግርማ ሞገሳቸው የታል?» የተመስገን ኮንቹ አጭር የፌስቡክ ጥያቄ ነው። ሜሮን አማረም አጠር ባለ ጽሑፏ፦ «እጃቸው ነው የሚመሣሠለው» ስትል ሐሳቧን ገልጣለች። 

«ሁሉንም ህዝብ በማያስቆጣ ተደርገዉ መሰራቱ ጥሩ ብልጠት ነዉ» ያለው ፋንታ አየለ ነው። «ሀዉልታቸዉ ይሰራል ሲሉ ለነበሩት ይሄዉ ሰራንላችሁ፤ ሀዉልታቸዉ መሰራት የለባቸዉም ለምን ሰራችሁት ለሚሉ ደግሞ አይንህን ግለጥ እና እይ መች ሰራን የሚል መልስ ያለዉ ገራሚ ሀዉልት» ብሏል። 

ሐውልቱ እሳቸውን ይመስላል አይመስልም የሚለውን ትተው በሀውልቱ የአፍሪቃ ኅብረት ቅጥር ግቢ መቆም ላይ ብቻ አስተያየት ከሰጡ መካከል ለአብነት ያኽል ቀጣዮቹ ይገኙበታል። «የአፍሪካ አባት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ እውቅናና ዝና የማይደበዝዝ አንፀባራቂ በቀላሉ የማይደረስበት ከፍታ ላይ ነው ያለው። የዓመታት ፕሮፓጋንዳ ይበልጥ አገነናቸው። የዓመታት አለመዘከር ይበልጥ እንዲወራላቸው ሆነ።» የክብሩ ይስፋ የትዊተር አስተያየት ነው።

ዓለም ገብረእየሱ በፌስቡክ ጽሑፉ፦ «የዛሬ ስድስት አመት የኩአሜ ኑኩሩማ ሃዉልት መታስቢያ ሲቆም ምነው የአፍሪካ ህብረት የእኛን ንጉስ ሃይለስላሴን እረሳ ብዬ ነበር ዛሬ ደግሞ በልጆቻቸው ድንቅ ጥበብ ሲከበሩ ማየት ምንኛ ደስ ይላል እናመሰግናለን» የሚል አስተያየት አስፍሯል።

ዶክተር ቫኔሳ ኦኪቶ ዌዲ በሚል የትዊተር ስም የቀረበ የእንግሊዝኛ ጽሑፍ ደግሞ እንዲህ ይነበባል። «የአፍሪቃ ኅብረት አባት ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ-ሥላሴ በስተመጨረሻ በአፍሪቃ ኅብረት ክብራቸው ከፍ ብሏል። ዕውቅናውም ለአፍሪቃ የነጻነት ትግል እና የፓንአፍሪቃዊነትን በመጠንሰስ ላበረከቱት አስተዋጽዖ የተሰጠ ዕውቅና ነው።»

የአጼ ኃይለ-ሥላሴ ሐውልት በአፍሪቃ ኅብረት መቆሙ በተነገረበት የአባታቸው የራስ መኮንን ሐውልት ሐረር ጀጎል ሐኪም ቤት ውስጥ ኾን ተብሎ በተሽከርካሪ ተገጭቶ እንደወደቀ ተሰምቷል። ጥገና እየተደረገለትም ነው ተብሏል።  የአእመeሮ ኅመምተኛ ናት የተባለች ሴት ደግሞ ጎንደር ከተማ ውስጥ የአጼ ቴዎድሮስ ሐውልት ላይ በምሽት ጉዳት አደረሰች መባሉ እና ዳግም ጥገና እንደተደረገለት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተገልጧል።

Äthiopien Notstände in Amhara
ምስል DW/J. Jeffrey

አማርኛ በአፍሪቃ ኅብረት

በሳምንቱ ሌላኛው ዐቢይ የመነጋገሪያ ርእስ በእዛው በአፍሪቃ ኅብረት ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው። ኅብረቱ የአማርኛ ቋንቋን ይፋዊ ቋንቋው አድርጎ አጸደቀው የሚል የተሳሳተ መረጃ በፍጥነት በርካታ ሰዎች ጋር ተዳርሷል። ዜናውን በርካታ ተከታዮች ያሏቸው የተለያዩ የድረ ገጽ መገናኛ አውታሮች እና ታዋቂ ሰዎችም አስተጋብተውታል።

ጋዜጠኛ ኤልያስ መሰረት የአፍሪቃ ኅብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ቃል አቀባዪት ከኾኑት ኤባ ካሎንዶ ጋር ደውዬ አገኘኹት ባለው መረጃ መሰረት፦ «የቋንቋ ምርጫ የመሪዎቹ አጀንዳ ላይ ጭራሽ አልነበረም» ብለዋል ሲል መረጃው ሐሰት መኾኑን በፌስቡክ ገጹ ዐሳውቋል። በስህተት መረጃውን ያስተላለፉ ሰዎች መረጃውን ከገጻቸው አጥፍተው ለተሳሳተ መረጃቸው ይቅርታ ጠይቀዋል። አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች በተለይ በመገናኛ አውታር ዙሪያ የሚሠሩ ሰዎች ፈጣን መረጃን ለማድረስ በሚል የተሳሳቱ መረጃዎችን ከማሰራጨት በፊት ተደጋጋሚ ማጣራት እንዲያደርጉ መክረዋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እዚህም እዚያም የሚስተዋሉ ግጭቶች እንዲሁም በየጊዜው ሄድ መለስ የሚለው አዲስ አበባ የማናት ንትርክ በዚሁ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ከተስተዋሉ መነጋገሪያ ነጥቦች ይገኙበታል። የበርካቶችን አስተያየት አጠቃሎ በያዘው ቀጣዩ የትዊተር መልእክት እንቋጭ። ሰማ በላይ ነው መልእክቱን ያሰፈረው። እንዲህ ይነበባል።

«አጀንዳው መሆን ያለበት መቀሌም ሆነ አሳይታ፣ ጋምቤላም ሆነ አዳማ፣ አዲስአበባም ሆነ ጅማ፣ ባህርዳርም ሆነ አሶሳ፣ ሃረርም  ሆነ ጂጅጋ እንዲሁም አዋሳ 2ኛ ዜጋ አይኑር ነው። ሁሉም የኢትዮጵያ መሬት ለእያንዳንዱ የሃገሪቱ ዜጋ የተመቸ ይሁን ነው።»

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ