1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነፋስ ኃይል ምንጭ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 17 2004

ከምንኖርባት ፕላኔትም አልፈው በሌሎች፣ እንዲሁም በጨረቃዎችና ስባሪ ከዋክብት ወደፊት ማዕድን ለማውጣት የቋመጡ መንግሥታት መኖራቸው እሙን ነው። በተለይ ከጨረቃ፣ ሄልየም 3 የተሰኘውን ጋዝ ወደ ምድር በማምጣት ለኃይል ምንጭ ለማዋል አስቀድመው

https://p.dw.com/p/14kzz
ምስል R. Hörig/DW

ጽኑ ፍላጎታቸውን ካንጸባረቁት መካከል የመጀመሪያይቱ ሩሲያ ናት።

ዩናይትድ እስቴትስም ብትሆን ያን ያህል ከሩሲያ ያነሰ ፍላጎት አይደለም ያላት። ቻይናና ህንድም መቋመጣቸው አልቀረም። እንደሚባለው ከሆነ 40 ቶን የሄልየም -3 ክምችት፤ ዩናይትድ እስቴትስ አንድ ዓመት ሙሉ ለኤልክትሪክ ማመንጫ ኃይል የሚያስፈልጋትን መሸፈን የሚችል ነው። ጨረቃ፣ ከተፈጠረችበት ከ 4,5 ቢልዮን ዓመታት ገደማ አንስቶ፣ የፀሐይ ነፋስ የሚያመጣውን በማጠራቀም ፣ በውስጧ ከአንድ ሚልዮን እስከ 5 ሚሊዮን ቶን የሚመዝን፣ ሄልየም -3 አጠራቅማለች። በአፈሯ ውስጥ የሚገኘውን ሄልየም 3 ጋዝ የጨረቃን አቧራ ወይም አፈር 1,300 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በሚደርስ ግለት ማሞቅ ተገቢ ይሆናል። የሃይድሮጂን ቅይጥ ጋዞች ከማቀጠል ይልቅ፤ ሄልየም -3 ን ማቃጠሉ የላቀ የኃይል ምንጭ ያሻዋል። ይሁንና ጠቀሜታው ከፍ ያለ በመሆኑ ፣ በተለይ በቀጣዩ ክፍለ ዘመን በኃይል ምንጭነት መሪ ቦታ መያዝ እንደሚችል ነው የሚገመተው።

ይም ሆነ ይህ ፣ የሩቁን ለሩቁ ዘመን ትቶ ፣ የቅርቡን ማሰቡና ፤ በዚያም መጠቀሙ ሳይሆን አይቀርም ፤ የዓለምን ህዝብ የሚገላግለው። ምድራችን ደግሞ በዛ ያሉ አማራጭ ማገዶዎችን፤ የኃይል ምንጮችን ይዛለች። ከብዙዎቹ አንደኛው ነፋስ ነው። ለመሆኑ፤

የነፋስ ኃይልን በሰፊው መጠቀሙ በአፍሪቃም በአፋጣኝ ይስፋፋ ይሆን?

በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች ፣ በኢንዱስትሪ ይበልጥ ለመደርጀት፣ ሰፊ የኃይል ምንጭ እንደሚያሻቸው የታወቀ ሲሆን፤ በኢንዱስትሪ የገሠገሡት አገሮችም በአሁኑ ዘመን በሰፊው ከሚጠቀሙባቸው የተለያዩ የኃይል ምንጭ ማስገኛ ዘዴዎች ጎን ለጎን ቀደም ሲል በጨረፍታ እንደጠቀስነው፣ ማንኛውንም አማራጭ ከመጠቀም የተቆጠቡበት ጊዜ የለም።

NO FLASH Windenergie Windräder Windkraft
ምስል AP

የነፋስ የኃይል ምንጭ ፤ በዓለም ዙሪያ ከሞላ ጎደል በ 83 አገሮች ጥቅም በመስጠት ላይ ነው። መጠኑ ለጊዜው 3 ከመቶ ሲሆን፤ ወደፊት እጅግ እየተስፋፋ መሄዱ አይቀሬ ነው። የኤልክትሪክ ኃይል ለማግኘት፣ ነፋስ ሰፊ ጠቀሜት ነው ያለው። ባለፈው 2011 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ብቻ፤ በዓለም ዙሪያ፣ ከ 50 ቢሊዮን ዬውሮ በላይ የሚሆን ገንዘብ ነው ፣ በነፋስ ኃይል ኤልክትሪክ ለማመንጨት ሥራ ላይ የዋለው። ይኸ ይበልጥ ተጠናክሮ የቀጠለው፣ በአውሮፓና በእስያ ነው። ለብዙ የአፍሪቃ አገሮችም የነፋስ የኃይል ምንጭ የሚያማልል ነው። ችግሩ፤ ተፈላጊ ቅድመ ግዴታዎችን የማሟላቱ ጣጣ ነው።

ከአውሮፓ ፣ እስፓኝ ና ደንማርክ፤ 20 ከመቶ የኤልክትሪክ አገልግሎት የሚያገኙት ፣ በነፋስ ኃይል ከሚሽከረከሩ አውታሮች ወይም ማማዎች ነው። ጀርመን እስካሁን በነፋስ ኃይል አማካኝነት የምታመነጨው የኤልክትሪክ የኃይል መጠን 10 ከመቶ ብቻ ነው። እ ጎ አ እስከ 2020 መጠኑን በ 20 እና 25 ከመቶ ከፍ የማድረግ እቅድ ነው ያላት።

እ ጎ አ እስከ 2011 ማለቂያ ድረስ፤ 237 ጊጋዋት ኃይል የሚያመነጩ በነፋስ ኤይል የሚሠሩ አውታሮች ተተክለው ነበር።

በጀርመን 29 ጊጋዋት(GW)

በእስፓኝ 22 ጊጋ ዋት(GW)

በቀሪዎቹ የአውሮፓ ኅብረት አገሮች 43 ጊጋዋት(GW)

በአጠቃላይ አውሮፓ 94 ጊጋዋት(GW)

በዩናይትድ እስቴትስ 47 ጊጋዋት(GW)

በህንድ 16 ጊጋዋት(GW)

በሌሎች አገሮች18 ጊጋዋት(GW)

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ውስጥ በስፋት በነፋስ ኃይል የኤልክትሪክ ኃይል በሚያመነጩ አውታሮች የምትጠቀም ግንባር ቀደም ሀገር ቻይና ናት።

Flash-Galerie Niederlande Windmühle
ምስል picture-alliance/dpa

ቻይና፤ ካላት ግዙፍ የቆዳ ስፋትና የተለያዩ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ያላቸው ቦታዎች ፤ የዓለም ጣራ የመሰለው ከፍተኛ ቦታ ብቻ ሳይሆን ረጅም የባህር ጠረፍም ያላት እንደመሆኑ መጠን፤ ለዚህ የሚበጁ፤ ኃይለኛ ነፋስ የማይለያቸው ጣቢያዎች ለተጠቀሰው ዓላማ እንዲውሉ በመደረግ ላይ ነው። እስካለፈው ታኅሳስ ወር ማለቂያ ገደማ (እ ጎ አ እስከ 2011 ዓ ም ፍጻሜ ) ቻይና 62 ጊጋዋት ኤልክትሪክ ማመንጨት ችላ ነበር። እ ጎ አ እስከ 2015 ፤ 100 ጊጋዋት(GW) ለማመንጨትና ከነፋስ ኃይል 190 ቢሊዮን ኪሎዋት ኤሌክትሪክ በሰዓት ለማግኘት ነው እቅዷ! እስከ 2030 ደግሞ በአጠቃላይ አገሪቱ የሚያስፈልጋትን ኤልክትሪክ ማቅረብ እንደማይሳናት ነው የተነገረው።

በነፋስ ኃይል ኤልክትሪክ የሚያመነጩ አውታሮች ተከላ እጅግ እየተስፋፋ የመጣው፣ ዋጋውም ዝቅ ያለ በመሆኑ ነው። በነፋስ ኃይል ከሚንቀሳቀሱ ታላላቅ አውታሮች ወይም ማማዎች የሚመነጨው ኤልክትሪክና በሰዓት ለኪሎዋት የሚከፈለው ከ 5-9 ዬውሮ ሳንቲም(ሴንት) ነው። የዓለም የነፋስ ኃይል ምንጭ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ Stefan Gsänger እንደሚሉት ከሆነ፣ ዋጋው ባጣሙን አማላይ ነው።

(1)«የሚከፈለውን ዋጋ ስንመለከት፤ በአሁኑ ጊዜ ፤ የነፋስ ኅይል ምንጭ፣ እጅግ ረከስ ካሉት የኃይል ምንጮች አንዱ ነው ማለት እንችላለን። ለማንኛውም፤ ከአቶም ኃይል ማመንጫ አውታሮች ከሚገኘው ምናልባትም ከቤንዚን ናፍጣም ሆነ የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋው ይበልጥ የረከሰ ሳይሆን አይቀርም። የፋስ ኃይል ምንጭ፣ በዘመናዊ መልክ ከሚሠሩ የድንጋይ ከሰል የኃይል ምንጭም ሆነ፤ የጋዝ ኃይል ምንጭ የተሻለ ነው። በዋጋ ደረጃ ማለት ነው።»

የዓለም የነፋስ ኃይል ምንጭ ድርጅት እንደሚገምተው፣ እ ጎ አ እስከ 2020 ድረስ፤ በዓለም ዙሪያ በነፋስ ኃይል የሚሠሩ አውታሮች ተግባር በ 4 እጥፍ ይጨምራል። የ 1,000 ጊጋዋት(GW) አቅም መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ 1,000 ታላላቅ የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታሮች የሚሰጡት ጉልበት ነው።

አፍሪቃ ውስጥ፤ የነፋስ ኃይል እስከዚህም የተሰጠው ግምት አልነበረም። እርግጥ ነው በጥቂቱም ቢሆን፤ በነፋስ ኃይል የሚሠሩ አውታሮች፤ በግብፅ ፤ ሞሮኮ፣ ቱኒሲያ፣ ኢትዮጵያ፤ ናይጀሪያና ደቡብ አፍሪቃ እንዲሁም በካቡ ቬርደ ደሴቶች ለናሙና በሚመስል መልኩ ተተክለዋል።

እሽቴፋን ግዜንገር የዓለም መንግሥታት፤ ግራም ነፈሰ ቀኝ፤ ከነፋስ ኃይል ለሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ ፣ ዋስትና ያለው ተመሳሳይ ዋጋ ቢመድቡ፤ ገንዘባቸውን ሥራ ላይ ለሚያውሉ ባለወረቶችም ይበጃል ሲሉ ይመክራሉ። ወደፊት፤ ለትንንሽ ከተሞችና ለመንደሮች አነስ ያሉ በነፋስ ኃይል ኤልክትሪክ የሚያመነጩ አውታሮች ኑዋሪዎችን ይታደጋሉ ብለው ያምናሉ።

(2)«በእርግጥ፣ ለአፍሪቃ አገሮች፤ የሚበጀው ሥነ-ቴክኒክ፤በነፋስ ኃይል የሚሠሩ አነስተኛ አውታሮች የሚተከሉበት እርምጃ ነው። ገበያም ይኖራል። አፍሪቃ ለዚህ ገበያ ተስማሚ ስለሚሆን፣ ከሞላ ጎደል ፣ እስከዚህም ውድ ያልሆነ መሣሪያ ሠርተን ለማቅረብ በሚገባ ማሰላሰል ይኖርብናል። »

በፀሐይ ኃይል ለሚሠሩ አውታሮች፤ የዋጋ ክፍያ ፣ እስያና አፍሪቃ፣ በአነስተኛ ወለድ ብድር እንደሚሰጥ ሁሉ ፤ በነፋስ ኃይል ለሚገኘው የኤልክትሪክ ጉልበትም ተመሳሳይ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል። የገጠር ልማት ባለሙያ ሄርማን አልበርስ፤ 20 ዓመታት የዜጎች ፓርኮች የሚሏቸውን በነፋስ ኃይል የሚሠሩ አውታሮች ሲተክሉ የቆዩ እንደመሆናቸው መጠን፤ የጋራ ማኅበረሰባዊ ፕሮዠዎች እንደሚበጁ ይናገራሉ።

(3)«እንደእውነቱ ከሆነ፤ በግልጽ መገንዘብ እንደቻልነው፤ ፕሮጀክቶች የላቀ ተቀባይነት የሚያገኙት፣ ራሳቸው ዜጎች ገንዘብን ሥራ ላይ በማዋሉ ረገድ ሲሳተፉና የኃይል ምንጭ አቅራቢዎችም ሲሆኑ ነው። የኃይል ምንጭ አውታሮች ተግባራዊ በሚሆኑባቸው አካባቢዎች፣ ህዝቡ እጅግ ላቅ ያለ እርካታ ነው የሚሰማው።»

ዜጎች የሚሳተፉበት ተጋባር የዓለም የነፋስ ኃይል ምንጭ ጉዳይ ድርጅት እንደሚገነዘበው፤ ለአየር ንብረት መጠበቅ የሚበጅ የኃይል ምንጭ የሚቀርብበት እርምጃ በዓለም ዙሪያ እንዲዛመት አስተዋጽኦ ያደረጋል። እናም፣

የማኅበረሰብ ኃይል(Citizens’ Power)በሚል መፈክር፤ ቀጣዩ የዓለም የነፋስ ኃይል ምንጭ ነክ ጉባዔ፤ በመጪው ሰኔ ወር ማለቂያ ላይ በቦን ጀርመን እንዲካሄድ ቀነ-ቀጠሮ ተይዟል።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ