1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የኒውክለር ጨረር ቴክኖሎጂን የተጠቀመው የጤፍ ምርምር

ረቡዕ፣ ኅዳር 10 2012

ለ60 ሚሊዮን ገደማ ኢትዮጵያውያን ዋነኛ ምግብ የሆነው ጤፍ ከሌሎች ሰብሎች ጋር ሲነጻጸር በሄክታር ዝቅተኛ የምርት መጠን የሚገኝበት ነው። የጤፍን ምርታማነት ከፍ የማድረግ ዓላማ ያለውና በደብረዘይት የግብርና ምርምር ማዕከል እየተካሄደ ያለ አንድ ምርምር የኒውክለር ጨረር ቴክኖሎጂን እስከመጠቀም ተጉዟል።

https://p.dw.com/p/3TPEb
Bildergalerie Äthiopien Teff
ምስል DW/J. Jeffrey

የኒውክለር ጨረር ቴክኖሎጂን የተጠቀመው የጤፍ ምርምር

የ70 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋው አቶ ገመዳ ያሚ አርሶ አደር ናቸው። ሁለት ሶስተኛ ዕድሜያቸውን በግብርና ያሳለፉት አቶ ገመዳ መቼ እርሻ እንደጀመሩ ሲጠየቁ “እንዴ! እርሻ ከጀመርኩ 50 ዓመት ይሆናል” ሲሉ በገረሜታ ይመልሳሉ።

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን አደአ ወረዳ ውስጥ በምትገኝ አነስተኛ ቀበሌ የሚኖሩት አቶ ገመዳ አሁንም ከማሳ አይጠፉም። ሰሞኑን ባለፈው ክረምት የዘሩት ጤፍ ደርሶ አጨዳ ላይ ናቸው። ሂዲ የተሰኘችው የእርሳቸው ቀበሌም ሆነች በአደአ የሚገኙ ገጠራማ ቦታዎች በጤፍ ምርታቸው ስማቸው የገነነ ነው።

የሶስት ሄክታር ስፋት ያለው መሬት ባለቤት የሆኑት አቶ ገመዳም በዋነኛነት የሚያመርቱት ጤፍን ነው። በአካባቢያቸው ባለው የገበሬ ህብረት ስራ ማህበራት ህብረት አማካኝነት በየጊዜው የተሻሻለ የጤፍ ዘር የሚያገኙ መሆናቸው ደግሞ ከሌሎች አርሶ አደሮች ግንባር ቀደም አድርጓቸዋል። “የዘር ማባዣ ማህበር ውስጥ ነው ያለሁት። ዘሩን እያባዛን ነው እንግዲህ። ለሌሎቹም ገበሬዎች እንዲያልፍ ቅድሚያ ለእኛ ይሰጣል” ይላሉ። 

Äthiopien neuer politischer Führer ist auf Unterstützung der Jugend angewiesen
ምስል Reuters/T. Negeri

አቶ ገመዳ አሁን እየተጠቀሟቸው ያሉ ሁለት የጤፍ ዝርያዎች ከድሮዎች ጋር ሲነጻጸሩ የተሻሻሉ እንደሆኑ ይናገራሉ። “ቦሰት የሚባለው ቁመቱም በልክ ነው የሚሆነው። ለንፋስ እና [ለዝናብ] አይጋለጠም። ቁንጮ ግን በጣም ይረዝማል። እና ሌላ ዘርም ደግሞ ከኋላ እየመጣ ነው ” ሲሉ በቀጣይ ሌሎች ዝርያዎች እንደሚኖሩም ጠቆም ያደርጋሉ። 

አርሶ አደሩ “ዘመናዊ እና የተሻሻሉ” እያሉ የሚጠሯቸው የጤፍ ዝርያዎች ከየት እንደሚመጡ ያውቃሉና ነው መጪውን መተንበያቸው። በጤፍ ዝርያዎች ላይ ዋነኛ ትኩረቱን ያደረገው የደብረዘይት የግብርና ምርምር ማዕከል የሚገኘው በአቅራቢያቸው ነው። ከዚህ ምርምር ማዕከል ላለፉት 40 ዓመታት 26 የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎች ወጥተዋል። የቤተ ሙከራ እና የማሳ የሙከራ ጊዜያቸውን በአጥጋቢ ሁኔታ ያጠናቀቁ የማዕከሉ የምርምር ውጤቶች ታዲያ ተባዝተው የሚከፋፈሉት እንደ አቶ ገመዳ ባሉ አርሶ አደሮች አማካኝነት ነው። 

የደብረዘይት የግብርና ምርምር ማዕከል በቅርቡም አዲስ የምርምር ውጤት ይዞ መጥቷል። በቤተ ሙከራ ደረጃ ሶስት ዓመታት የወሰደው ይህ የማዕከሉ ምርምር የኒውከለር ጨረር ቴክኖሎጂን የሚጠቀም መሆኑ ልዩ ያደርገዋል። የደብረዘይት የግብርና ምርምር ማዕከል በዳይሬክተርነት የሚመሩት ዶ/ር ሰለሞን ጫንያለው ይህን ምርምር ከሚያከናውኑ ሰባት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች አንዱ ናቸው። ስለ ምርምሩ ዓላማ ያብራራሉ። 

“የምርምሩ ዋና ዓላማ ይህንን የኒውክለር ቴክሎጂን በተለይ የጨረር ቴክሎጂን ተጠቅመን የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎችን ማስገኘት ነው። በተለይ ከምርት ጋር ተያይዞ ድርቅን የሚቋቋም፣ ቶሎ ፈጥኖ የሚደርስ እንዲሁም መጋሸብን የሚቋቋም ዝርያ ማውጣት ነው። መጋበሽ ማለት አይተኸው ከሆነ የጤፍ ሰብልን ትንሽ ምርት ሲይዝ ወደ መድረስ አካባቢ ላይ በንፋስም፤ በዝናብም ይወድቃል። ስለዚህ ያ መውደቁ የሰብሉን ምርቱን እና ጥራቱን ይቀንሰዋል። ሰብሉም ብቻ አይደለም ጭዱም ለከብቶች መኖነት ያገለግላል። እና ይህንንም የሚቋቋም ዝርያ ለማውጣት ታስቦ ነው። ከዚያ ውጪ አንዱ የፕሮጀክቱ ዓላማ ደግሞ የጤፍን የምግብ ይዞታ (nutrient content) የምንለውን ለማሻሻል ነው” ይላሉ ዶ/ር ሰለሞን።

በኢትዮጵያ ጤፍን እንደ ዋነኛ ምግብ የሚጠቀመው የህዝብ ብዛት 60 ሚሊዮን ገደማ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። በሀገሪቱ በአነስተኛ ማሳ ላይ ጤፍ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ብዛት ደግሞ ስድስት ሚሊዮን ገደማ ይደርሳሉ ተብሎ ይገመታል። እነዚህ አርሶ አደሮች ሶስት ሚሊዮን ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ ጤፍን ቢያመርቱም ከሌሎች ተመሳሳይ የግብርና ውጤቶች አንጻር በአንድ ሄክታር የሚሰበሰበው የጤፍ ምርት ግን ዝቅተኛ መሆኑን ተመራማሪዎች ያስረዳሉ። እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ በኢትዮጵያ ከአንድ ሄክታር የሚገኘው የጤፍ ምርት በአማካይ 15 ኩንታል ነው። 

Landwirtschaft Äthiopien Dreschen von Hirse
ምስል Getty Images/AFP/S. Gemechu

ከደብረዘይት የግብርና ምርምር ማዕከል የወጡ ምርጥ የጤፍ ዝርያዎችን የሚጠቀሙት አርሶ አደር ገመዳ ከአማካዩ ከፍ ያለ ምርት ቢያገኙም በቆሎ አምራቾች በሄክታር ከሚሰበስቡት ላይ ግን መጠጋት አልቻሉም። አቶ ገመዳ በሄክታር ከ16 እስከ 20 ኩንታል ጤፍ እንደሚያመርቱ ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ የበቆሎ ምርት በሄክታር 34 ኩንታል መድረሱን “ዘ ኦክስፎርድ ሀንድ ቡክ ኦፍ ኢትዮጵያን ኢኮኖሚ” በሚል ርዕስ የታተመው ጥናታዊ መጽሐፍ ጠቁሟል። ዶ/ር ሰለሞን አዲሱ ምርምራቸው የጤፍ ምርታማነትን በእጥፍ እንደሚጨምር ይገልጻሉ። “እኛ በምርምር ያወጣናቸው የተሻሻሉ ዝርያዎች በምርምር ማሳ እና በአንዳንድ በተሻሻሉ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ እስከ 32 እስከ ኩንታል ይገኛል ማለት ነው” ሲሉ የምርት ልዩነቱን ያስረዳሉ። 

በማሳ ሙከራ ላይ ያሉት እነዚህ የጤፍ ዝርያዎች በውስጣቸው ያለው የምግብ ንጥረ ነገር ይዘትም የተሻሻለ እንደሆነ ተነግሮላቸዋል። በኢትዮጵያ የተወሰኑ አካባቢዎች ያሉ ተመጋቢዎች የጤፍን የምግብ ይዞታ ለማሻሻል ከሩዝ እና ከአብሽ ጋር ቀላቅለው እንደሚያስፈጩ የሚጠቅሱት ዶ/ር ሰለሞን እርሳቸው እና ባልደረቦቻቸው በአዲሱ ምርምራቸው የጤፍን የፕሮቲን መጠን እና ሌሎች ንጥረ ነገሮችን ይዘት ለመጨመር መሞከራቸውን ይናገራሉ። 

“እንግዲህ ጤፍ በምግብ ይዘቱ እንደምታውቀው በአውሮፓም አሁን ጤናማ ምግብ እየተባለ ነው። በተለይ የceliac በሽታዎች intolerant ለሆኑ ሰዎች ተመራጭ ነው። በሌሎችም ንጥረ ነገሮች ጤፍ ከሌሎች ሰብሎች በጣም ብዙ የተከማቸ ንጥረ ንገር አለው። ፕሮቲንም ቢሆን ጤፍ ከሌላው ያነሰ ፕሮቲን የለውም። በተለይ ላይሲን ከአስፈላጊ አሚኖአሲዶች አንዱ የሆነውን ንጥረ ነገር ከሌሎች ሰብሎች፣ ከአንዳንዶቹ የተሻለ፣ ከአንዳንዶቹ ደግሞ ተመጣጣኝ የሆነ መጠን ነው ያለው” ብለዋል ዶ/ር ሰለሞን።

Äthiopien | Sorghum & Teff Farm
ምስል DW/E. Bekele

የጤፍን ምርታማነት ለመጨመር የተደረገው የቤተ ሙከራ ምርምር በኢትዮጵያ እምብዛም ያልተለመደ የኒውክለር ጨረር ቴክኖሎጂን ተጠቅሟል። ተመራማሪዎቹ አንድ የጤፍን ዘር ወስደው በተለያየ መጠን ለጨረር እንዲጋለጥ በማድረግ በዘሩ ላይ የሚፈልጉትን የዘረ-መል ለውጥ ለማምጣት ተደጋጋሚ ሙከራዎች እንዳደረጉ ዶ/ር ሰለሞን ይናገራሉ። የጨረሩ መጠን ለኤክስ ሬይ ህክምና ከሚውለው ከ10 እስከ 100 ሚሊዮን እጥፍ የበረታ በመሆኑ በባለሙያ እና በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚከናወን መሆኑንም ያስረዳሉ።

“ዘሩን ለጨረር እንጋልጠዋለን። ከነበረው ባህሪ ሌሎች የተለያዩ ባህሪዎች እንዲያመጣ ይደረጋል። ከእነዚያ ባህሪዎች እኛ በምንፈልገው መንገድ፣ የምንፈልገውን ጸባይ፣ ከምርታማነት አንጻር፣ አለመጋሸብን፣ ይሄ shattering የምንለው አለው ሲደርስ ብትን የሚለው ነገር እርሱንም የሚቋቋም ዝርያ ለማውጣት የምንጠቀምበት መሳሪያ ነው። ይሄ በተጠበቀ መልኩ የሚደረግ ነው። ሰው እዚያ ላይ አይጋለጥም። ራሱን የቻለ መሳሪያ አለ። የሚሰራውም በጣም ልምድ ያለው ሰው ነው” ይላሉ። 

ለመሆኑ ጤፍን የሚያህል ደቃቅ የሰብል ዘር ላይ እንደዚህ አይነት ውስብስብ የምርምር ስራዎች ማካሄድ አያስቸግርም? ለሚለው ጥያቄም ዶ/ር ሰለሞን ምላሽ አላቸው። አዲሱ የጤፍ ዝርያ እስካሁን ባለው የማሳ ሙከራ አጥጋቢ ውጤት ማሳየቱን የሚናገሩት ተማራማሪው “ለተለያዩ አካባቢዎች የሚስማሙ ዝርያዎች ለማውጣት ጥሩ ምልክት አይተናል” ይላሉ። ዶ/ር ሰለሞን እና ባልደረቦቻቸው ከሶስት እስከ አምስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ለአርሶ አደሮች የሚከፋፈሉ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለማድረስ የማሳ ሙከራው እንደቀጠለ ገልጸዋል።

ተስፋለም ወልደየስ  

ማንተጋፍቶት ስለሺ