1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይሮቢዉ ግጭትና የአል-ሸባብ ዛቻ

ሐሙስ፣ ጥር 13 2002

ዉዝግቡ አነጋግሮ ሳያበቃ የሶማሊያዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አል-ሸባብ በኬንያ ላይ ጦርነት አዉጇል።ቡድኑ በየአምደ መረቡ ባሰራጨዉ ሙዝሙር ፉከራና ቀረርቶ ናይሮቤን እንደሚመታ እየዛተ ነዉ።የኬንያ መንግሥትም ዛቻዉን በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተከታተለዉ ነዉ።

https://p.dw.com/p/Ld3b
ናይሮቢምስል picture-alliance / TPH Bildagentur / Spectrum

21 01 10

ኬንያ ርዕሠ-ከተማ ናይሮቢ ዉስጥ አንድ ጃማይካዊ የሙስሊም ሐይማኖት መሪ በመታሠራቸዉ ምክንያት በፀጥታ አስከባሪዎችና የሶማሊያ ዝርያ ባላቸዉ የከተማይቱ ነዋሪዎች መካካል የተነሳዉ ግጭት ተረጋግቷል።ይሁንና የሶማሊያዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አል-ሸባብ የኬንያ ፀጥታ አስከባሪዎችን ርምጃ ለመበቀል መዛቱ ሌላ መዘዝ እንዳያስከትል እያሰጋ ነዉ።ዛቻዉ እንደተሰማ የኬንያ መንግሥት የፀጥታ ቁጥጥሩን አጠናክሯል።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝር ዘገባ አለዉ።

የኬንያ ባለሥልጣናት ጃማይካዊዉን የሐይማኖት መሪ ሼክ አብዱላሕ ኤል ፈይሰልን ከሐገር ለማባረር ባለፈዉ ሳምንት ማሰራቸዉ ከሐገሪቱ ሙስሊሞች በተለይ ደግሞ ከሶማሊያ ስደተኞችና የሶማሊያ ዝርያ ካላቸዉ ነዋሪዎች ያልታሰበ ቁጣ ነበር-የቀሰቀሰዉ።እስራቱን በመቃወም በሰልፍ አደባባይ በወጣዉ ሕዝብና በፀጥታ አስከባሪዎች መካካል በተፈጠረ ግጭት በትንሹ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል። ብዙዎች ቆስለዋል።በመንግሥት መግለጫ መሠረት ወደ ሁለት መቶ ሺሕ ዶላር የሚገመት ሐብት ንብረት ወድሟል።

በናይሮቢ የኪስዋሒሊ ቋንቋ ዘጋቢ አልፍሬድ ኪቲ እንደታዘበዉ ግጭቱ በዚሕ ጥፋት አላበቃም።
«ከዚያ በሕዋላ ፖሊስ የሶማሊያ ዝርያ ያላቸዉ ሰዎች በብዛት የሚኖሩበትን አካባቢ በጥብቅ ያስስ ገባ።እና ሕገ-ወጥ ስደተኞችን ለመቆጣጠር ባለዉ ዘመቻዉ በትንሹ ስምንት መቶ ሰዎችን አሰረ።»

የናይሮቢዉ ፖሊስ አዛዥ አንቶኒ ኪቡቺ የሰላም እጦት አስገድዷቸዉ የተሰደዱ የሶማሊያ ተዋላጆችን «ሐገራቸዉን ያጠፉ» በማለት እስከ መዝለፍ ነበር-የደረሱበት።ኪቡቺ የሚያዙት ፖሊስ በሰላማዊ ሰልፉ ሰበብ የተፈጠረዉን ግጭት በሌላ ቀይሮ ሕጋዊ ፍቃድ የሌላቸዉ ባለቸዉ የሶማሊያ ስደተኞች ላይ ነዉ የዘመተዉ።

የተሰጠዉ ምክንያት ጋዜጠኛ አል ፍሬድ እንተከታተለዉ የሶማሊያዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን የአል-ሸባብ ሚሊሺያዎች ከስደተኞች ጋር ተመሳስለዉ ወደ ኬንያ ገብተዋል የሚል ነዉ።
«የሚባለዉ የአል-ሸባብ ሚሊሺያዎች ከጎረቤት ሐገር ሶማሊያ የመጡ ስደተኞችን ተቀላቅለዉ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኬንያ ገብተዋል ነዉ።በሰላማዊ ሰልፉም ሳይሳተፉ አይቀርም ተብሎ ይጠረጠራል።»
በዘመቻዉ ከታሰሩት ስምንት መቶ ያሕል ሰዎች ጥቂቱ ተለቀዋል።አብዛኞቹ ግን ዛሬም እንደታሰሩ ነዉ።ዘመቻዉ በሰላማዊ ሰልፉ የተሳተፉ፥ ያደራጁ ወይም ግጭት ቀሰቀሱ ተብለዉ የተጠረጠሩትን ብቻ የሚመለከት አልነበረም።የኬንያ መንግሥት የሚደግፈዉ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ባለሥልጣናት፥ የራሷ የኬንያ እንደራሴ ባለቤትም ጭምር ታስረዉ ነበር።

«አስራ-ሁለት የሶማሊያ መንግሥት የምክር ቤት አባላት ታስረዉ ነበር።ትናንት እንኳን ኬንያዊት ግን የሶማሊያ ዝርያ ያላቸዉ አንዲት የቀድሞ የኬንያ ምክር ቤት እንደራሴ ባለቤት አስራ-ሥምንት አመት ካልሞላዉ ልጃቸዉ ጋር ታስረዉ ነበር።ኋላ ግን ተለቅቀዋል።»
ሙስሊም ሑዩማን ራትስ ፎረም የተባለዉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የፖሊስን እርምጃ ባንድ ነገድና ባንድ ሐይማኖት ተከታዮች ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ በማለት አጥብቆ አዉግዞታል።የኬንያ የሰብአዊ መብት ብሔራዊ ኮሚሽን በበኩሉ በተወሰነ ሕዝብ ዘንድ ፍራቻን ለማስረፅ ያለመ በማለት ተቃዉሞታል።
ሁለቱ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እንደሚሉት ሕገ-ወጥ ስደተኞችን መቆጣጠር ፀጥታን ማስፈን ተገቢ ነዉ።ሰልፍን መከልከል፥ ሕገ-ወጥ ስደተኞችን በመቆጣጠር ሥም የተወሰኑ ጎሳ ወይም ሐይማኖት ተከታዮችን ማሸማቀቅ ግን የሐገሪቱን ሕግ የሚጥስ ነዉ።ዉዝግቡ አነጋግሮ ሳያበቃ የሶማሊያዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አል-ሸባብ በኬንያ ላይ ጦርነት አዉጇል።ቡድኑ በየአምደ መረቡ ባሰራጨዉ ሙዝሙር ፉከራና ቀረርቶ ናይሮቤን እንደሚመታ እየዛተ ነዉ።የኬንያ መንግሥትም ዛቻዉን በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተከታተለዉ ነዉ።

«የመንግሥት ምንጮች እንዳስታወቁት በድንበር አካባቢ የፀጥታዉ ቁጥጥር ተጠናክሯል።መንግሥት ዛቻዉን ከምር ነዉ የወሰደዉ።በዚሕም ምክንያት በተለይ በድንበር አካባቢ የሚያደርገዉ ቁጥጥር በጣም ተጠናክሯል።»

Schwere Gefechte in Somalia Islamistische Miliz in Mogadishu
የአልሸባብ ታጣቂዎችምስል AP

Agenturen,Interv.mit Kiti

Negash Mohammed

Hirut Melesse