1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይጀሪያና የካሜሩን ፀረ-ቦኮሃራም ትብብር

ሐሙስ፣ ሐምሌ 23 2007

በናይጀሪያና በአካባቢው ሃገራት የደፈጣ ውጊያ የሚያካሂደው ፅንፈኛው ቡድን ቦኮሃራም መዳከሙ ቢነገርም አሁንም አደጋ መጣሉ አልቆመም። ቡድኑን ለመዋጋት የተመሠረተው ከአካባቢው ሃገራት የተውጣጣው ወታደራዊ ግብረ ኃይል ለችግሩ መፍትሄ ይሆናል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።

https://p.dw.com/p/1G7ft
Kamerun Präsidenten Paul Biya & Muhammadu Buhari Nigeria
ምስል Getty Images/AFP/R. Kaze

[No title]

ግብረ ኃይሉ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት የናይጀሪያው ፕሬዝዳንት ሙሃመዱ ቡሃሪ ወደ ጎረቤት ካሜሩን በመጓዝ ከካሜሩኑ አቻቸው ፓውል ቢያ ጋር የቦኮሃራምን ጥቃት መመከት በሚቻልበት መንገድ ላይ መክረዋል።

የናይጀሪያው ፕሬዝዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረጉት የካሜሩን ጉብኝት ብዙዎች ሲጠብቁት የነበረ ነው። የዚህም ምክንያቱም ሁለቱ ሃገራት የጋራ ችግር ውስጥ መውደቃቸው ነው። በአሁኑ ጊዜ የናይጀሪያው ደፈጣ ተዋጊ ቡድን የፅንፈኛው ቦኮሃራም ወታደራዊ እንቅስቃሴ መዳከሙ ቢታመንም አልሞት ባይ ተጋዳይነቱ ግን አይሏል። ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ቡድኑ በጣላቸው የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃቶች ወደ 800 የሚጠጉ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል ።ፕሬዝዳንት ቡሃሪ በአሁኑ የካሜሩን ጉብኝታቸው ከካሜሩኑ ፕሬዝዳንት ፓውል ቢያ ጋር በተለይ አሸባሪውን ቦኮሃራምን ለመዋጋት በአካባቢው ሃገራት በተቋቋመው ወታደራዊ ግብረ ኃይል ላይ አትኩረው መክረዋል ።ቡሃሪ ያውንዴ ውስጥ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት የሁለቱ ሃገራት የጋራ ጠላት በሆነው በቦኮሃራም ላይ መንግሥታቸው የያዘውአቋም ከቀድሞው የተለየ አይደለም ።
«ናይጀሪያ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን ህይወት ያጠፋውን ያቆሰለውን ብዙዎችንም መኖሪያ አልባና ያደረገውንና ህይወታቸውንም ያሰናከለውን ቦኮሃራምን ለመውጋት አሁንም በቁርጠኝነቷ እንደፀናች ነው ።»

ቦኮሃራም በናይጀሪያና በአካባቢው ሃገራት የሚጥላቸው የሽብር ጥቃቶች በሃገራቱ ኤኮኖሚ ላይ ተፅእኖ ማሳደሩ ነው የሚነገረው ። በካሜሩን የናይጀሪያ መንግሥት አማካሪ ና የካሜሩን ነዋሪ የሆኑት ነጋዴ ኢሪክ ኦዱስ እንደሚሉት ፀጥታው አስተማማኝ አለመሆኑ የሃገራቱን የኤኮኖሚ ኃይል እያዳከመ ነው ። ይህም እንደ ኦዱስ በሃገሬው ህዝብም ሆነ በውጭ ዜጎች ላይ ተፅእኖ ማሳደሩ አልቀረም ። በዚህና በሌሎችም የሽብር ጥቃቱ ባስከተላቸው ተፅእኖዎች ሰበብ ከቅርብ ወራት ወዲህ የአካባቢው ሃገራት ወታደራዊ ትብብራቸውን አጠናክረዋል ። በጎርጎሮሳዊው በ2015 መጀመሪያ ላይ የቻድ ወታደሮች ቦኮሃራምን ከሰሜን ምሥራቅ ናይጀሪያ በማስወጣት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ። በአሁኑ ጊዜ የደፈጣ ተዋጊው የቦኮሃራም የመጨረሻው ዋነኛ ምሽግ ካሜሩን ድንበር ላይ የሚገኘው የዛምቢዛ ጫካ ሆኗል ።ከዚያን ወዲህ ፀረ ሽብሩ ውጊያ አልቀጠለም ። ናይጀሪያ ዋና ከተማ አቡጃ የሚገኘው የዲሞክራሲና ልማት ማዕከል የተባለው ተቋም ባልደረባ ጂብሪን ኢብራሂም ቡድኑ ከሚከተለው የውጊያ ስልት በመነሳት የቦኮሃራምን የሽብር ጥቃት በአጭር ጊዜ ማቆም አይቻልም ይላሉ ።
« ቦኮ ሃራም ያልታጠቀ ማህበረሰብ ላይ ነው የበቀል እርምጃ የሚወስደው ።ቡድኑ የሽምቅ ውጊያ ስልት ነው የሚከተለው ። ይህ ደግሞ አሁን በሽሽት ላይ መሆኑንና ከዚህ ቀደም ናይጀሪያ ውስጥ የያዛቸውን አካባቢዎች መልሶ የመቆጣጠር አቅም እንደሌለው ያመለክታል ። በርግጥ ለዚህ የሚከፈለው መስዋዕትነት ከፍተኛ ነው ። የሰው ህይወት ይጠፋል ፤ ንብረት ይወድማል ። በርግጥ ይህን መሰሉን እርምጃ ማቆም እስከሚቻል ድረስ ጊዜ ይወስዳል ። ምክንያቱም ታጣቂ በሌለበት መንደር አንድ የታጠቀ ሰው ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላልና። »

Kamerun Anschlag in Maroua
ምስል Getty Images/AFP/Stringer


ናይጀሪያ ካሜሩን ቻድና ኒዠር ቦኮሃራምን በጋራ ለመዋጋት 8700 ሠራዊት ያለው አዲስ ግብረ ኃይል ለማሠማራት አቅደዋል ።በኢብራሂም እምነት የጋራው ስጋት በናይጀሪያ ይመራል የተባለው ግብረ ኃይል የታሰበለትን ዓላማ እንዲያሳካ ይረዳል።
«በቅርብ ዓመታት ውስጥ ቦኮሃራም ያተኮረው በናይጀሪያ ላይ ነበር ። ሶስቱ የናይጀሪያ ጎረቤቶች ኒዠር ቻድና ካሜሩን እስካሁን ድንበሮቻቸውን ከቦኮሃራም ጥቃት ሲከላከሉ ነበር የቆዩት።አሁን ደግሞ ቦኮሃራምን ለመዋጋት በሚካሄደው እውነተኛው ውጊያ ውስጥ ሊገቡበት ነው ።አሁን ሁሉም ቦኮሃራም የናይጀሪያ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሃገራት ስጋት መሆኑን ተገንዝበው የውጊያ ስልታቸውን ቀይረዋል »
ናይጀሪያ ና ካሜሩን በ19980 ዎቹ በነዳጅ ዘይት በበለፀገችው በባካሲን ልሳነ ምድር ምክንያት ደም አፋሳሽ ጦርነት ያካሄዱ ሃገራት ናቸው ። ሆኖም ሃገራቱ ያለፈውን ግጭት ለታሪክ በመተው አሁን የጋራ ጠላቸውን ቦኮሃራምን ለመዋጋት ተባብረው ለመሥራት ተስማምተዋል ።

Nigeria Anschlag in Gombe
ምስል picture-alliance/dpa

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ