1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይጀሪያ ሙስሊሞች በምዕራባዉያን እይታ

ረቡዕ፣ ጥር 3 1998

ምዕራባዉያን የስለላ ተቋማት ስጋት ቢኖራቸዉም እንደ ዖሳማ ቢን ላደን ያሉት ፅንፈኛ ሙስሊሞች ተስፋና ሃሳብን ግን የናይጀሪያ ሙስሊም ህብረተሰብ እንደማይደግፈዉ የዜና ወኪሎች ያደረጉት የምርመራ ዘገባ ዉጤት አመለከተ። በሰሜን ናይጀሪያ የሚገኙት የሙስሊም እምነት መሪዎች እንደሚሉት በድህነቷ በምትታወቀዉ አፍሪካ የሚገኙ እምነት አጥባቂ ሙስሊሞች በእምነታቸዉ ስም ለመጣዉ እንዲህ ላለዉ የፅንፈኝነት አብዮትም ሆነ አመፅ ዝግጁ አይደሉም።

https://p.dw.com/p/E0jA
የናይጀሪያ ፕሬዝደንት ዖሊሴንጎን ዖባሳንጆ
የናይጀሪያ ፕሬዝደንት ዖሊሴንጎን ዖባሳንጆምስል dpa

AFP የዜና ወኪል ባካሄደዉ የምርመራ ተግባር በናይጀሪያ በጣም ጥቂት የሚባሉ ናቸዉ ካለፈዉ ዓመት የትጥቅ ግጭት በኋላ የሙስሊም ፅንፈኝነትን የሚሰብኩ።
በወቅቱ 60ሚሊዮን በሚሆነዉ የናይጀሪያ ሙስሊም ህብረተሰብ መካከል ከፍተኛ ብጥብጥና አለመረጋጋትን የሚያስከትል ግጭት ለመቀስቀስ ታልሞ ነበር።
ሆኖም በህዝብ ብዛት በተጨናነቀችዉና ህገወጥነት ይታይባታል በምትባለዉ አፍሪካዊቷ ናይጀሪያ ስጋት ከመንገሱ ባሻገር የናይጀሪያ ሙስሊሞች ኢአማንያን በሆኑት መሪዎቻችሁ ላይ ተነሱ ለሚለዉ ላለፈዉ ዓመት የቢንላደን ጥሪ ጆሮ የሰጠዉ አልነበረም።
ባጭሩ የተቀጨዉን ያለፈዉን ዓመት የሃይማኖት ዉዝግብ የናይጀሪያ ታሊባን በሚል የግል ስያሜ ማቀነባበሩ የሚነገርለት አሚኑ ታሽን ኢሊሚ ከተደበቀበት ከሰሜን ግዛት ለAFP እንደነገረዉ ናይጀሪያን ወደእስላማዊ መንግስትነት ለመለወጥ በድጋሚ ጦር ለመስበቅ ተዘጋጅቶ ነበር።
ሌሎች የሙስሊሙ እምነት መሪዎች ግን ዛቻዉን በአካባቢዉ ያለዉን የጠነከረ የመቻቻል ባህል ከግምት ያላስገባ ባዶ ፉከራ በማለት አጣጥለዉታል።
ማንኛዉም በምሁራዊ ዉይይት ላይ ያልተመሰረተ ሆኖም በጦር ኃይል እንጂ በመነጋገር የማያምን እምነት ሁሉ የዉሸት እምነት ነዉ ምክንያቱም ቅዱስ ቁርአን ሙስሊሞች ሌሎችን ወደእምነቱ ለማምጣት በመረጃ አግባቡ እንጂ በጦር መሳሪያ አስገድዱ አይልም ይላሉ አብዱልጃባር ናሲሩ ካባራ።
ካባራ በሰሜናዊ ናይጀሪያ የካኑ ከተማ በአገሪቱ ከሚገኙት የእምነቱ ተከታዮች በርካታዉን ቁጥር የሚይዙት የሱፊ ሙስሊም መሪዎች አንዱ ናቸዉ።
በአካባቢያቸዉ የፖለቲካ ይዘት እንዳለዉ በሚነገርለት በሳዉዲ አረቢያዉ ዋሃቢይ ባህል እርዳታ የመስጊድ ግንባታዉ የተስፋፋ ቢሆንም አማንያኑ መቻቻልን የሚፃረረዉ ፅንፈኝነት አራማጆች እንዳልሆኑ ይነገራል።
ካባራ እንደሚሉት በአገራቸዉ ለመንቀሳቀስ የሞከረዉ ራሱን ታሊባን ብሎ የሚጠራዉ ቡድን የናይጀሪያ ሙስሊሞችን ልብ የሚያሸፍትበት መረጃ እንዳጠረዉ ማየት ይቻላል።
በእሳቸዉ ገለፃም በናይጀሪያ ባለፈዉ ዓመት የተከሰተዉን የእምነት መሰል አመፁን የፈጠረዉ ድህነትና የፍትህ መዛባት ነዉ።
ሁኔታዉ በሃይማኖት ሰበብ ሊያስከትል የሚችል ችግርና ስጋት ድህነት ባጠቃዉ ህብረተሰብ ዉስጥ የፈጠረ መሰለ።
አያይዘዉም በግጭቱ የተሳተፉት አብዛኛዎቹ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸዉ፤ በመማር ላይ የሚገኙ ቢኖሩም በብዙ ዉጣ ዉረድ ትምህርታቸዉን የሚከታተሉ፤ በአገሪቱ ባለዉ ጠባብ የስራ እድል ስራ የማግኘት ተስፋቸዉ የመነመነ መሆናቸዉን ይገልፃሉ።
ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ ከሱኒ እስልምና ጋር የሚመሳሰለዉ የሰሜን ናይጀሪያ ሱፊ ሙስሊሞች ቢሆኑም ግማሾቹ ሺዝም ተከታዮች ናቸዉ።
በተለይም በኢራን በፈረንጆቹ 1979ዓ.ም የእስላም መንግስት ለመመስረት በሚል ከተካሄደዉ አብዮት ወዲህ ናይጀሪያም የተወሰኑ ለዉጦችና ሀሳቡ ተቀባይነት አግኝቷል።
በፈረንጆቹ 1999ዓ.ም ላይ ነበር ከብዙ መወዛገብ በኋላ በናይጀሪያ የሰሪያ ህግን እንደገና በህግነት የመቀበል እርምጃ የተወሰደዉ።
ያም ቢሆን ግይ ይላሉ የናይጀሪያዉ የሙስሊም ንቅናቄ ተጠሪ ሙሃመድ ቱሪ ራሱን ታሊባን እያለ በሚጠራዉ ቡድን የተነሳዉ ዓይነት አመፅ ተቀባይነት የለዉም።
ቱሪም እንዲሁ ሙስሊም በእስልምና ህግ መኖር እንዳለበት የሚያምኑ መሆናቸዉን በመግለፅ ታሊባን ተብዬዎቹ ግን ሰፋ አድርገዉ ማገናዘብ እንደሚገባቸዉ ጠቁመዋል።
ምክንያቱንም ሲያብራሩ በቅድሚያ ሙስሊሞችን ስለ እስላማዊ መንግስት አስፈላጊነት ሳያስተምርና ሳያነቃ መሳሪያ በማንሳት በግዳጅ ልጫን የሚለዉ ሙከራዉ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ሊያዉቅ ይገባል ብለዋል።
ያም ሆነ ይህ ከፍተኛ የሙስሊም ቁጥርና ስርዓተ አልበኝነት ይታይባታል የምትባለዉ ናይጀሪያ የእምነቱ መሪዎች እንደገለፁት የዓማፅያኑን ጥያቄም ሆነ ዓላማ ምዕራባዉያኑ እንደፈሩት ሳይሆን የሚደግፉ አይመስሉም።