1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይጀሪያ ምርጫና አሳሳቢው የሃገሪቱ ፀጥታ

ዓርብ፣ ጥር 8 2007

ከአራት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በናይጀሪያ የምክር ቤት አባላትና ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ይካሄዳል ። በአሁኑ ጊዜ በሽብር ማዕበል በምትናወጠው በናይጀሪያ ምርጫ እንዴት ሊካሄድ ይችላል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል ።በምርጫው ዋዜማ በናይጀሪያ አሳሳቢው የፀጥታ ችግር ብቻ አለመሆኑን የዶቼቬለዋ ሽቴፋኒ ዱክሽታይን ዘገባ ያስረዳል ።

https://p.dw.com/p/1ELrm
Wahlkampf in Nigeria 2015
ምስል Reuters/A. Sotunde

በናይጀሪያዋ የቦርኖ ፌደራል ክፍለ ግዛት የባጋ ከተማ ከሳትላይት በሚታየው ምስሏ ከተማይቱን መለየት ያዳግታል ። ቦኮሃራም ባደረሰው ተደጋጋሚ ጥቃት በከተማዋ ብዙ ጥፋቶች ደርሰዋል ። አንድ የዓይን ምስክር በቡድኑ ጥቃት የተገደሉ 100 ሰዎችን ማየቱን ከሌሎች ጋር ነፍሱን ለማዳን ሲሸሽ ከአጠገባቸው ቦኮሃራም ተጨማሪ ሰዎች ሲገድልና ሲያቆስልም መመልከቱን ተናግሯል። ከአፍሪቃ በህዝብ ብዛት ቀዳሚውን ቦታ በምትይዘው በናይጀሪያ 69 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ድምፅ መስጠት ይችላሉ ። ቶክ ቪሌጅ ኢንተርናሽናል የተባለው የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ዓምደ መረብ ባልደረባ ስቴፋን ኦጉንቶይንብ ፣ ፍርሃት የነገሰበት ይህ ህዝብ እንዴት ስለ ምርጫ ሊያስብ ይችላል ሲል ይጠይቃል ።

«አሁን በሰሜን ምስራቅ ናይጀሪያ ምን እየሆነ ነው ለሚለው እንደሚመስለኝ ስለ ቦኮሃራምና ስለሌሎችም ጉዳዮች ስንናገር መንግሥታችን በትክክል ፀጥታ ማስከበር የቻለ አይመስለኝም ። አንዳንድ ፌደራዊ ግዛቶች በቦኮሃራም እየተጠቁ ነው ። በቦኮሃራም ቁጥጥር ስር ባሉት በነዚህ ግዛቶች በልበ ሙሉነት ለምርጫ መውጣት እጅግ አደገኛ ነው ።»

Wahlkampf in Nigeria 2015 Akinwunmi Ambode
ምስል picture-alliance/AP Photo/S. Alamba

የናይጀሪያ ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን በተቻለ መጨን አደጋዎችን ለመቀነስ ጥረት እንደሚያደርግ ነው የሚናገረው ። የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ኒክ ፓዛንግ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት የፀጥታ ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች የፀጥታ ጥበቃ እንዲጠናከር ይደረጋል ።

« ሰዎችና የምርጫ ቁሳቁሶች ከአደጋ እንዲጠበቁ መራጮችም ከሁከት ነፃ በሆነ አካባቢ እንዲመርጡ ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር እየሰራን ነው ። ይህን እንዲፈፀም ከፀጥታ ድርጅቶች ጋር በትጋት እየሰራን ነው ። ከፈተኛ አደጋ አላቸው ብለን በምናስባቸው አካባቢዎች የፀጥታ ኃይላት በብዛት እንዲሰማሩ እናደርጋለን ።እናም አካባቢዎቹን እንደ ሚያስከትሉት ስጋት መጠን ዝቅተና መካከለኛ ከፍተና ብለን ደረጃ እንሰጣቸዋለን ።የፀጥታ አስከባሪዎች ስምሬትም የኛን ግመገማ መሰረት ያደረገ ይሆናል ። »

በሰሜን ናይጀሪያዎቹ በቦርኖ ፣ በዮቤና በአዳማዋ ፌደራዊ ግዛቶች በቦካሃራም ጥቃት ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጓል ። የናይጀሪያ የምርጫ ኮሚሽን ግን በመላ ሃገሪቱ ምርጫ መካሄድ የሚችል መሆኑን ያረጋግጣል ።እንደገና ፓዛንግ

« ከነዚህ ሶስት ፌደራዊ ክፍለ ግዛቶች በርካታ ሲቭሎች በሃገር ውስጥ ተፈናቅለዋል ። አብዛኛዎቹ በመጠለያዎች ውስጥ ናቸው ።ቦርኖ ውስጥ ለምሳሌ በ11 መጠለያዎች ውስጥ ነው ያሉት ። የተፈናቀሉት ሰዎች የሚገኙባቸው እነዚህ መጠለያዎች በአካባቢው መንግሥት ይወከላሉ ። ከሚሽኑ ያሰበው መምረጥ የሚችሉ ሰዎች በመጠለያዎቹ ውስጥ ለሚፈልጉት እጩ ድምጻቸውን መስጠት እንዲችሉ ለማድረግ ነው ።»

Thema - Binnenflüchtline in Nigeria
ምስል DW/Uwaisu Idris

በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ በርካታ ሰዎች ሰሜን ምሥራቅ ናይጀሪያን ለቀው ወደ ሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎች ና ወደ ዋና ከተማይቱ አቡጃ ተሰደዋል ። የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን እንደሚለው በናይጀሪያ የሃገር ውስጥ ተፈናቃዩ ቁጥር 650 ሺህ ደርሷል ። ከዚያ በተጨማሪም ከነዚህ ግዛቶች ብዙ ናይጀሪያውያን ወደ ጎረቤት አገራትም ተሰደዋል ።ይሁንና አነዚህ ናይጀሪያውያን መምረጥ አይችሉም ።ምክንያቱን ፓዛንግ ያስረዳሉ ።

«ሰዎቹ በናይጀሪያ ጎረቤት በሆኑት በካሜሩን በቻድ ና በኒጀር ሪፐብሊክ በስደት የሚኖሩ ናቸው ። በናይጀሪያ ህግ ከሚሽኑ ከናይጀሪያ ድንበር ውጭ ምርጫ ማካሄድ አይችልም ።»

ከዚህ ሌላ የመራጮች ካርድ ጋር የተያያዙ ችግሮች መኖራቸውም ይሰማል ።የመራጮች ካርድ ዝግጅት አለመጠናቀቁ ይነገራል ። ካርድ ሊቀበል የሄደ ተማሪ አንድ ተማሪ ለሌላ ጊዜ ቀጠሮ ተስጥቶት መመለሱ ን ሌሎች ተማሪዎችም እስካሁን ካርድ አለማግኘታቸውን ተናግሯል ።ምርጫው ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ በቀረበት በአሁኑ ጊዜ በርካታ ናይጀሪያውያን የቦኮሃራም ጥቃት ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚለe ፍርሃታቸው ጨምሯል ።በናይጀሪያም ፖለቲከኞች ያለውን አሳሳቢ የፀጥታ ጉዳይ መነሻ በማድረግ በምርጫ መሸነፍ ቢያጋጥም ህዝቡ ለመምረጥ ስላልቻለ ነው የሚል ምክንያት በማቅረብ የምርጫውን ውጤት አጠራጣሪ ሊደርጉት ይችላሉ የሚልም ስጋት አለ ።

ኂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ