1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይጀሪያ/ካመሩን የድንበር ውዝግብ እና የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ውሳኔ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 5 1996
https://p.dw.com/p/E0lI
ናይጀሪያና ካመሩን ባለፈው አሠርተ ዓመት ውስጥ በጋራ ድንበራቸው በሚገኙ የባካሲ ልሳነ ምድርና በሌሎች በርካታ መንደሮች የባለቤትነት ጥያቄ የተነሣ ሲወዛገቡ ቆይተዋል። ይኸው በጊኔ ባህረ ሠላጤ አቅራቢያ የሚገኘው አንድ ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው በዓሣ ይዘቱ የበለፀገ ከመሆኑ ሌላ፡ ግዙፍ የነዳጅ ዘይት ንጣፍ እንዳለውም ነው የሚገመተው። ናይጀሪያና ካመሩን እአአ በ 1960 ዓም ነፃነታቸውን ከተጎናፀፉ ወዲህ፡ የሁለቱ ጎረቤት ሀገሮች ጦር ኃይላት በዚሁ አካባቢ በተደጋጊሚ ተጋጭተዋል። ውዝግቡ እየተባባሰ በሄደበት እና ሁለቱ ሀገሮችም እጦርነቱ አፋፍ ላይ በደረሱበት ጊዜ፡ የካመሩን መንግሥት በናይጀሪያ ላይ ክስ በመመሥረት ጉዳዩን ዘ ሄግ፡ ኔዘርላንድስ ለሚገኘው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት አቀረበው። ፍርድ ቤቱ ክሱ ከቀረበለት ከስምንት ዓመታት በኋላ ጥቅምት 2002 ዓም ላይ ብያኔውን በማሳለፍ፡ የባካሲ ልሳነ ምድር እና በቻድ ሐይቅ ዙርያ የሚገኙት አከራካሪዎቹ ሠላ ሦስት መንደሮች የካመሩን ግዛት ከፊል መሆናቸውን አስታወቀ። ከዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ለብያኔ አሠጣጡ ሂደት በይበልጥ የተመረኮዘው በቅኝ አገዛዙ ዘመን በቅኝ ገዢዎቹ ብሪታንያ፡ ፈረንሣይና ጀርመን መካከል በተፈረሙት ስምምነቶች ላይ ነበር። ይሁንና፡ ናይጀሪያ ይህንኑ ይግባኝ የማይባልበት ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን የመጨረሻና አሣሪ ውሳኔ መጀመሪያ ላይ ውድቅ በማድረጓ፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ብያኔው ተግባራዊ የሚሆንበትን መፍትሔ ለማስገኘት ሲል ኅዳር 2002 ዓም በዠኔቭ ባካሄድ ምክክር ላይ አንድ ከናይጀሪያውያንና ከካመሩን ዜጎች የተውጣጣ የጋር ኮሚስዮን አቋቋመ። ናይጀሪያ በአወዛጋቢዎቹ ግዛቶች የሚኖሩት ወደ ሦስት መቶ ሺህ ዜጎችዋ የወደፊት ኅልውና ዋስትና ስላሳሰባት ብቻ የዓለም አቀፉን ብያኔ እንዳለቀበለችው ለጋራ ኮሚስዮኑ አስረድታ ነበር። የጋራው ኮሚስዮን ከኅዳር 2002 እስከ አሁን ድረስ በርካታ ድርድሮች ካካሄደ በኋላ ናይጀሪያ የዓለም አቀፉን ፍርድ ቤት ውድቅ ያደረገችበትን አቋሟን ለመቀየር በቅታለች። በዚሁ የናይጀሪያ መንግሥት አሁን ባሳየው የአቋም ለውጥ መሠረት፡ የባካሲን ልሳነ ምድር በሚቀጥለው ግንቦት ወር ለካመሩን መልሶ ለማስረከብ አቅዶዋል። ይኸው ዕቅዱ ሁለቱን ጎረቤት ምዕራብ አፍሪቃውያቱን ሀገሮች ለብዙ ዓመታት ላነታረከው የግዘት ባለቤትነት ውዝግብ ዘላቂውን መፍትሔ ያስገኛል ተብሎ ተስፋ ተደርጓል። ዘ ሄግ፡ ኔዘርላንድስ የሚገኘውን ፍርድ ቤት ብያኔ ተግባራዊ እንዲያደርግ የተቋቋመው የናይጀሪያና የካመሩን የጋራ ኮሚስዮን አወዛጋቢዎቹ የድንበር ግዛቶችና መንደሮች ለካመሩን በሚመለሱበት የዚዜ ዕቅድ ላይ ስምምነት የደረሰው ባለፈው ነሐሴ ቢሆንም፡ ናይጀሪያ ከጎረቤት ካመሩን ጋር ትርጉም አልባ የሆነ ጦርነት ላለመጀመር ስትል፡ የዓለም አቀፉን ብያኔ ለመቀበል ዝግጁነትዋን ከጥቂት ሣምንታት በፊት በይፋ እስከገለፀችበት ጊዜ ድረስ ይፋ ኣወጣም ነበር። ናይጀሪያ ለካመሩን ይመለሱ በሚባሉት ግዛቶች የሚኖሩት ዜጎችዋ፡ ከግዛት ርክክቡ በኋላ ለኅልውናቸው ጥበቃ ተገቢውን ዋስትና የሚያገኙበትን ስምምነት ለማስገኘት ነበር እስካሁን ስትጥር የቆየችው። በዕቅዱ መሠረት፡ ናይጀሪያ በባካሲ ልሳነ ምድር ያሉትን የመንግሥት ሠራተኞችዋንና የፀጥታ ኃይላትዋን ከፊታችን ሚያዝኣ እስከሚቀጥለው ግንቦት ወር ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ እወጥትጨርሳለች። ለዚሁ የርክክብ ሥራ ዝግጅቱ በሚቀጥለው የካቲት ወር በሚካሄደው የጋራው ኮሚስዮን ስብሰባ ላይ ይጠናቀቃል። ሠላሣ ሦስቱ መንደሮችም የተያዘው አውሮጳዊ ዓመት 2003 በሚያበቃበት ታኅሳስ ሠላሣ አንድ ለካመሩን ይመለሳሉ። ይሁንና፡ በሰሜን ምሥራቅ ናይጀሪያ ያለው የቦርኖ ክፍለ ሀገር ሕዝብ መንደሮቹ የሚመለሱበት ጊዜ በዚያ በሚኖሩትና በግብርና ላይ ጥገኛ በሆኑት ሀምሳ ስድስት ሺህ ቤተሰቦች ኤኮኖሚያዊ ኅልውን ላይ ብርቱ ጉዳት ያስከትላል በሚል ርክክቡ ቀስ በቀስ እንዲከናወን ጠይቀዋል። ምክንያቱም ጊዜው የመኸር መሰብሰቢያ ነውና። የባካሲን ልሳነ ምድር ርክክብም በተመለከተ፡ የግዛቱ ነዋሪዎች የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ያሳለፈውን ብያኔ በመቃወም፡ ናይጀሪያ ግዛቱ ለካመሩን የሚመለስበትን ድርጊት ተግባራዊ ካደረገች ለመገንጠሉ እንደሚታገሉ አስታውቀዋል። የናይጀሪያ ፕሬዚደንት ኦሉሴጉን ኦባሳንዦ እና የካመሩን አቻቸው ፖል ቢያ ውዝግቡ በሰላማዊ መንገድ ማብቃት ይቻል ዘንድ የሀገሮቻቸው ሕዝቦች የዓለም አቀፉን ፍርድ ቤት ብያኔ እንዲቀበሉ ለማግባባ የሚቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል። ኦባሳንዦ ከጥቂት ጊዜ በፊት በሀገራቸው ቴሌቪዥን ባሰሙት ንግግር፡ ለካመሩን ይመለሳሉ በሚባሉት ግዛት የሚኖሩት ናይጀሪያውያን ወደ ትውልድ ሀገራቸው ለመመለስ ከፈለጉ፡ የናይጀሪያ መንግሥት ተገቢው የአቀባበል ዝግጅት እንደሚደረግላቸው፡ በዚህ ፈንታ ግን በካመሩን ለመቆየት ካሰቡ ደግሞ በዚያ እንደሚኖሩት ሌሎች ሦስት ሚልዮን የናይጀሪያ ዜጎች የካመሩንን ሕግ አክብረው መኖር እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።