1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይጄሪያ ምርጫ፤ አስተምሕሮቱ

እሑድ፣ ሚያዝያ 4 2007

ባለፈዉ መጋቢት 28 በተደረገዉ ምርጫ የመላዉ ለዉጥ አራማጆች ኮንግረስ (APC) ዕጩ የቀድሞዉ ጄኔራል መሐመዱ ቡኸሪ አሽንፈዋል።ከቡኻሪ ማሸነፍ እኩል በሥልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታን ሽንፈታቸዉን አምነዉ መቀበላቸዉ በናጄሪያ በብዙ የአፍሪቃ ሐገራትም ብዙ ያልተለመደ ዓይነት ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽሽግር ነዉ የሆነዉ።

https://p.dw.com/p/1F69m
ምስል U. Ekpei/AFP/Getty Images / AP Photo

ናይጄሪያ በ1960 እጎአ ከብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ እንደ ዲሞክራሲያዉ ይትበሐል በምርጫ መሪዎችዋን ለመሾም የተለያዩ ሙከራዎች ተደርገዉባት ነበር።ይሁንና እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር እስከ 1999 ድረስ የተመረጠ የሲቢል አስተዳደር ተደላድሎ ሥልጣን ይዞባት አያዉቅም።

ብዙ ጊዜ በጦር ጄኔራሎች መፈንቅለ መንግሥት፤ አልፎ፤ አልፎ በርስ በርስ ጦርነትና ግጭት ሥትታበጥ አርባ ዓመት ያሕል ያስቆጠረችዉ ምዕራብ አፍሪቃዊት ሐገር አነሰም በዛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማስተናገድ የጀመረችዉ እጎአ በ1999 ነዉ።ከ1999 እስካሁን ድረስ የሚገዛት ግን ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (PDP) የተሰኘዉ ነዉ።

ባለፈዉ መጋቢት 28 በተደረገዉ ምርጫ ግን አራት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያጣመረዉ የመላዉ ለዉጥ አራማጆች ኮንግረስ (APC) ዕጩ የቀድሞዉ ጄኔራል መሐመዱ ቡኸሪ አሽንፈዋል።ከቡኻሪ ማሸነፍ እኩል በሥልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታን ሽንፈታቸዉን አምነዉ መቀበላቸዉ በናጄሪያ በብዙ የአፍሪቃ ሐገራትም ብዙ ያልተለመደ ዓይነት ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽሽግር ነዉ የሆነዉ።

Nigeria Goodluck Jonathan Abdulsalami Abubakar Muhammadu Buhari
ምስል DW/Ubale Musa

እርግጥ ነዉ ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ በሕዋላ ለወትሮዉ በመፈንቅለ መንግሥት፤ በነፍጥ ትግል ወይም በዉርስ መሪዎች ሲፈራረቁባቸዉ የነበሩት ብዙ የአፍሪቃ ሐገራት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እናስተናግዳለን ማለታቸዉ አልቀረም።ይሁንና በትክክለኛ ምርጫ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የተደረገባቸዉ ፤ ደቡብ አፍሪቃ፤ቦትስዋና፤ሞዛምቢክ፤ ጋና፤ ታንዛኒያ እያልን የምንቆጥራቸዉ የአንድ ዕጅ ጣቶችን እንኳ የማይሞሉ ሐገራት ናቸዉ።

ያሁኑ የናጄሪያ ምርጫ ሒደትና ዉጤት ለአፍሪቃዉያን ምን ያስተምራል ነዉ?የሚለዉ ጥያቄ የዉይይታችን አብይ ጭብጥ ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ልደት አበበ