1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይጄሪያ እና ሴኔጋል ምርጫዎች ምን ያመለክታሉ?

ቅዳሜ፣ የካቲት 23 2011

በምዕራብ አፍሪካ የምትገኘው ሴኔጋል የተረጋጋ ዲሞክራሲ እንዳለባት ሀገር ትወሰዳለች። በርካታ መንፈቅለ መንግስቶችን ያስተናገደችው ጎረቤቷ ናይጄሪያ ግን ስሟ በዚህ ረገድ የጠለሸ ነው። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የየሀገራቱን ፕሬዝዳንት ለመምረጥ ድምጽ የተሰጠባቸው ሁለቱ ሀገራት በምርጫ አኳያም የሚጋሩት ጥቂት ነው።

https://p.dw.com/p/3EMpd
Senegal Präsidentschaftswahlen | Stimmenauszählung
ምስል AFP/C. Abd Ali

የናይጄሪያ እና ሴኔጋል ምርጫዎች ምን ያመለክታሉ?

በአፍሪካ አህጉር ከዲሞክራሲያዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ስማቸው እንደ ምሳሌ ከሚነሱ ጥቂት ሀገራት መካከል ሴኔጋል በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት አንዷ ናት። ባለፈው ሳምንት እሁድ በሀገሪቱ በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንኳ 16 ሚሊዮን ከሚጠጋው ህዝቧ 6.5 ሚሊዮን ያህሉ ተሳትፏል። ለፕሬዝዳንትነት የተወዳደሩት ዕጩዎችም እንደሌላው ሀገር ቁጥራቸው በርካታ አልነበረም- አምስት ብቻ ናቸው። 

ባንጻሩ ከአንድ ቀን በፊት ተመሳሳይ ምርጫ ባካሄደችው ናይጄሪያ 73 ግለሰቦች ለፕሬዝዳንትነት በዕጩነት ቀርበው ነበር። በአፍሪካ በህዝብ ብዛት ቀዳሚ በሆነችው ናይጄሪያ ከ191 ሚሊዮን ህዝቧ የዛሬ ሳምንት በተካሄደው ምርጫ 73 ሚሊዮኑ ያህሉ ድምጽ ለመስጠት ወጥቷል። ምርጫው በርካታ ህዝብ ቢያሳትፍም ከሰላማዊ ሁኔታ በጣሙኑ የራቀ ነበር። በናይጄሪያ ከድምጽ አሰጣጡ ጋር በተያያዘ ብጥብጥ 39 ሰዎች ተገድለዋል። የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እና ምርጫ ጽህፈት ቤቶች ተቃጥለዋል።  እንዲህ በብጥብጥ እና በውዝግብ በጠለሸው የናይጄሪያ ምርጫ በስልጣን ላይ ያሉት ማሁማዱ ቡሃሪ ማሸነፋቸው ባለፈው ረቡዕ ታውጇል።

Nigeria, Abuja: Präsident Muhammadu Buhari begrüßt seine Unterstützer
ምስል Reuters/B. Omoboriowo

የመላው ተራማጅ ኮንግረስ (APC) የተሰኘው የፕሬዝደንቱ ፓርቲም ከሰላሳ ስድስቱ የናይጄሪያ ግዛቶች በአስራ ዘጠኙ በለስ እንደቀናው ተገልጿል። ተቃዋሚው የህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (PDP) በመዲናይቲ አቡጃ እና በ17 ግዛቶች አሸናፊ መሆኑን የሀገሪቱ ነጻው ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል። የቡሃሪ ዋነኛ ተቀናቃኝ አቲኩ አቡበከር የምርጫውን ውጤት ውድቅ አድርገዋል። አቡበከር “የውሸት” ሲሉ የጠሩትን የምርጫ ውጤት በፍርድ ቤት እንደሚሞግቱ ገልጸዋል።    

እንደ ናይጄሪያ ሁሉ በሴኔጋልም የምርጫው አሸናፊ ሆነው የወጡት አሁን በስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ናቸው። የመጨረሻቸው ለሆነው የስልጣን ዘመን የተወዳደሩት ሳል ከአስራ አራቱ የሀገሪቱ ክልሎች በአስራ ሶስቱ ከተሰጠው ድምጽ ቢያንስ 57 በመቶ በማግኘት አሸንፈዋል ተብሏል። ይህ በተገለጸ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች በምርጫው ጎልቶ የወጣ አሸናፊ ስለሌለ “ድጋሚ ምርጫ መካሄዱ አይቀሬ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።  

Senegal Präsidentschaftswahlen | Macky Sall
ምስል Imago/Xinhua/D. Gueye

በሁለቱ ሀገራት የተካሄዱ ምርጫዎችን የገመገሙ የፖለቲካ ታዛቢዎች የተለያየ አስተያየት አላቸው። ኦላይንካ አጃላ በብሪታንያው ዮርክ ዩኒቨርስቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እና ስለ ግጭቶች ጥናት የሚካሄዱ ባለሙያ ናቸው። ናይጄሪያ በርካታ ተግዳሮቶች ቢኖሩባትም ወደ ዲሞክራሲ የሚወስዳትን “አዲስ መንገድ እየጠረገች ነው” ይላሉ። 

“በናይጄሪያ ዲሞክራሲ በፍጥነት እያደገ ለመሆኑ አንዱ ማመላከቻ ባለፉት ሁለት ዓመታት የመጡት የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛት ነው። ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው ምርጫ ለፕሬዝዳንትነት የተወዳደሩ 73 ዕጩዎች ነበሩ። ይህ በርካታ ሰዎች ዲሞክራሲን መቀበላቸውን ያሳያል። አነስተኛ ፓርቲዎች እያደጉ ነው። ነባሮቹ ሰዎች ቀስ በቀስ ቦታውን እየለቀቁ አዳዲስ ሰዎች ወደፊት እየመጡ ነው” ብለዋል አጃላ ።  

የፖለቲካ ተንታኙ በመጨረሻ ላይ ላነሱት ነጥብ እንደምሳሌ የሚጠቅሱት የናይጄሪያ ምክር ቤትን (ሴኔት) በፕሬዝዳትነት ይመሩ የነበሩት ቦኮላ ሳራኪ በምርጫው የምክር ቤት ወንበራቸውን ማጣታቸውን ነው። “ከዚህ ቀደም እንደእርሳቸው አይነት የፖለቲካ ስልጣን ያላቸው ሰዎች በምርጫ ማሸነፍ በጣም አስቸጋሪ እንደነበር መለስ ብለው ያስታውሳሉ።  ናይጄሪያ በትክክለኛው መንገድ ላይ ለመሆኗ “ይህ አንድ ማመላከቻ ነው” ባይ ናቸው።  

ከናይጄሪያ በተሻለ ዲሞክራሲን ተግባራዊ አድርጋለች ተብላ በምትሞካሸው ሴኔጋል ግን “እንደቀድሞው ትቀጥል ይሆን?” የሚሉ ጥያቄዎች መነሳት ጀምረዋል። ናይጄሪያ ነጻነቷን ከብሪታንያ እንዳገኘች በርካታ መፈንቅለ መንግስቶች አስተናግዳለች። ሀገሪቱ በአለመረጋጋት ውስጥ የቆየችባቸው ጊዜያትም ብዙ ናቸው። በአንጻሩ ሴኔጋል በ1960ዎቹ ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች ወዲህ በፖለቲካ ስርዓቷ አንድም መንገራገጭ ሳያጋጥማት ቀጥላለች። ዲሞክራሲያዊ የተባሉ ምርጫዎችንም አካሂዳለች። 

ሀገሪቱ ባስመዘገበችው የኢኮኖሚ ዕድገት ምክንያት በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል በአሁኑ ምርጫ እንደሚያሸንፉ አስቀድሞም ተተንብዮ ነበር። ሆኖም ተቺዎች ፕሬዝዳንት ሳል የፖለቲካ ተቃናቃኞቻቸውን ከጨዋታ ውጭ አድርገዋል በሚል ይወነጅሏቸዋል። የፕሬዝዳንቱ ዋነኛ ተቃናቃኞች የሆኑት ካሊፋ ሳል እና የቀድሞው ፕሬዝዳንት አብዱላሄ ዋዴ “በሙስና ወንጀል ተጠርጥረዋል” በሚል ከምርጫው ታግደዋል። ካሊፋ ሳልም ሆነ አብዱላሄ ዋዴ የቀረበባቸውን የሙስና ክስ “በፖለቲካ የተቃኘ ነው” ሲሉ ያጣጥላሉ። ኦፕን ሶሳይቴ ኢንሼይቲቭ ዌስት አፍሪካ በተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የሴኔጋል ኃላፊ የሆኑት ሃዋ ባ “ይህ ሁኔታ በሴኔጋል ዝና ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል” ይላሉ።  “እነዚህ ዕጩዎች በምርጫ እንዳይወዳደሩ የተከለከሉት የፍርድ ቤት ክስ ስላለባቸው ቢሆንም ሴኔጋል ባላት የዴሞክራሲያዊ ሀገርነት ገጽታ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። የምርጫው ፍትሃዊነት እና ሂደት ላይም እንደዚያው። ምክንያቱም እነርሱ በስልጣን ላይ ያሉት ዕጩ ዋነኛ ተቃናቃኝ ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው”ሲሉ ያስረዳሉ።  

Senegal Präsidentschaftswahlen | Wahllokal
ምስል Getty Images/AFP/M. Cattani

በሁለቱ ሀገራት ምርጫዎች በአፍሪካ ለዲሞክራሲ ያለው ግንዛቤ እያደገ መምጣቱ ተንጸባርቋል። “በሴኔጋል ህዝቡ በምርጫ በጣሙኑ ያምናል። ህዝቡ የመንግስት ተቋማት ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ እንደሚያካሂዱ እምነቱን ጥሏል። በምርጫ ውድድር ያምናል። ማንኛውም ዜጋ የሚፈልገውን ለመምረጥ ዘመናዊ የምርጫ ስርዓት መንገድ እንደሆነ ተቀብሏል። ለሴኔጋል ዜጎች የድምጽ ሰጪ ካርድ እንደ የተከበረ ነገር ነው የሚታየው። በምርጫ ድምጽ መስጠት እንደ መሰረታዊ መብት ነው የሚወሰደው” ይላሉ ሃዋ ባ። 

የመብት ተሟጋቿ ሃዋ ባ ሰዎች በመራጮች መዝገብ ላይ ያልተገኘ ስማቸውን ለማፈላለግ እስከ ሶስት ድምጽ መስጪያ ጣቢያዎችን ሲያካልሉ ታዝበዋል። “በህዝቡ ዘንድ ፕሬዝዳንትም ይሁን ከንቲባ አሊያም የምክር ቤት አባል ለመምረጥ አንድም ቢሆን ድምጼ ዋጋ አለው የሚል እምነት አለ” ይላሉ ሃዋ። ለዚህም ይመስላል ምርጫው በሰላማዊ ሁኔታ የተካሄደው። እንደ ሃዋ ባ ገለጻ 98 በመቶው የምርጫ ጣቢያዎች በሰዓታቸው ተከፍተዋል። “ዘጠና በመቶ ገደማ በሚሆኑ ምርጫ ጣቢያዎች ሁሉም የምርጫ ቁሳቁሶች በቦታቸው ነበሩ። ከዚያ በኋላ ነው ምርጫው የተካሄደው” ሲሉ የታዘቡትን ይናገራሉ። 

Nigeria Präsidentschaftswahlen Schlange vor Wahllokal
ምስል Getty Images/AFP/L. Tato

በኢኮኖሚስት መጽሄት የዲሞክራሲ ጠቋሚ ዝርዝር ሴኔጋል ከ167 ሀገራት 73ኛ ደረጃን አግኝታለች። በዝርዝሩ ውስጥ ናይጄሪያ የተቀመጠችው በ108 ደረጃ ላይ ነው። ናይጄሪያ ምርጫ ማካሄድ የጀመረችው ከወታደራዊ አገዛዝ ተላቅቃ መሆኑን የሚያስታውሱት የፖለቲካ ተንታኙ ኦላይንካ አጃላ ይህም ለሀገሪቱ ዝቅተኛ ደረጃ ማስመዘገብ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ያስረዳሉ። 

“ከዚያን ጊዜ ወዲህ ይሄኛው ስድተኛው ምርጫ ነው። በናይጄሪያ ዲሞክራሲ ገና እያደገ ነው።  ዲሞክራሲ እንዲያብብ እንደ የህግ የበላይነት የመሳሰሉ በርካታ ነገሮች እንዲኖሩ ይጠበቃል። ነገር ግን ናይጄሪያ በየአራት ዓመቱ ምርጫ ማካሄድ የጀመረችው ከ1999 ወዲህ ነው” ይላሉ አጃላ። 

በናይጄሪያ የአሁኑ ምርጫ ቡሃሪ እና አቡበከር ከፍተኛ ፉክክር ማካሄዳቸውን የሚጠቅሱት አጃላ ይህም የህዝቡን ፍላጎት በግልጽ የሚያመላክት ነው ይላሉ። ተቃዋሚው ዕጩ አሸናፊውን “እንኳን ደስ አለህ ይላል” ብለው ቀድሞውን እንዳልጠበቁ የሚናገሩት የፖለቲካ ተንታኙ የምርጫውን ውጤት በመቃወም ግን ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት እርግጠኛ እንደነበሩ ያስረዳሉ። “በምርጫው ውጤት ምክንያት በናይጄሪያ ብጥብጥ ይኖራል ብዬ አልጠብቅም” ሲሉም እምነታቸውን ገልጸዋል።  

ተስፋለም ወልደየስ