1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይጄሪያ ወጣት ሴት አሸባሪዎች

ረቡዕ፣ ጥር 6 2007

ቦኩ ሐራም ልጃገረዶችን ለእጥፍቶ ጠፊነት ማዝመቱን መንታ ድል እንደሚያስገኝለት ሥልት ነዉ የሚቆጥረዉ።አንደኛ «ሴቶችም ይዋጋሉ» እያለ ወጣቶች ዓላማዉን እንዲቀበሉ መቀስቀሻ ያደረገዋል።ሁለተኛ ቡድኑን ይበልጥ ተፈሪ ያደርገዋል።

https://p.dw.com/p/1EKdF
ምስል AFP/Getty Images/P. Utomi Ekpei

የናይጄሪያዉ አሸባሪ ቡድን ወጣት ሴቶችን ቦምብ እያስታጠቀ ሕዝብ የተሰበሰበበትን አካባቢ ማሸበርን እንደ አዲስ የጥቃት ሥልት ተያይዞታል።ባለፈዉ ዕሁድ ሁለት ወጣት ሴት አሸባሪዎች ፖቲስኩም በሚባለዉ ከተማ ገበያተኛ መሐል ባፈነዱት ቦምብ አራት ሰዎችን አጥፍተዉ ጠፍተዋል።ሌሎች 21 አቁስለዋል።ከአንድ ቀን በፊት (ቅዳሜ) ማይዱጉሪ በተባለችዉ የሰሜናዊ ናይጄሪያ ከተማ አንዲት የአስር ዓመት ታዳጊ ወጣት ባፈነዳችዉ ቦምብ 19 ሰዎች ተገድለዋል።ሽቴፋን ዱክሽታይን እንደዘገበችዉ ተደጋጋሚዉ የወጣት ሴት አሸባሪዎች ጥቃት ቦኮ ሐራም አዲስ የጥቃት ሥልት መከተሉን ጠቋሚ ነዉ።

የአስር ዓመቷ ወጣት ሃያ ራስዋን ያጠፋችዉ አንድ ትልቅ የገበያ አዳራሽ ደጃፍ ነበር።ወደ አዳራሹ ለመግባት ስትሞክር ዘበኞች አስቆሟት።ሊፈትሿት ሲጠጉ-የታጠቀችዉ ቦምብ ፈነዳ።አስራ-ዘጠኝ ገደለች፤ ሞተችም።ብዙዎች፤ ታዳጊዋ ሕፃን የታጠቀችዉ ቦምብ የፈነዳዉ በርቀት መቆጣጠሪያ መሳሪያ ሳይሆን አልቀረም ብለዉ ያምናሉ።

Nigeria Anschlag 28.11.2014
ምስል Reuters

የማይዱጉሪ ሚሊሺያ አዛዥ አሺሩ ሙስጠፋ እንደሚሉት ደግሞ ልጅቱ ከሰወንቷ ላይ ተጠቅልሎ የነበረዉ ነገር ፈንጂ መሆኑን ማወቅዋ ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።ቦንቡን ልጅ አፈነዳዉ አዋቂ፤ ሴት አጋየዉ ወንድ ፈንዳታ-ሽብሩ መደጋጋሙ፤ የዶቸ ቬለዉ ወኪል ዓል አሚን መሐመድ እንደሚለዉ የሕዝቡን ሥጋትና ፍረሐት እያናረዉ ነዉ።

«ጥቃቱ ሕዝቡን እያስፈራ ነዉ።ሰዎች በሠላም ወጥተዉ መመለሳቸዉን እየተጠራጠሩ ነዉ።»ሰዎች በተለይ ወጣቶች እጥፍቶ ለመጥፋት የሚቆርጡበትን ትክክለኛ ምክንያት ማወቅ ሲበዛ ከባድ ነዉ።የናጄሪያ ወጣት ሴቶችም ሁኔታ እንደሁ።የፅንፈኝነትን ምክንያት የሚያጠኑትና የናይጄሪያ የፀጥታ መረብ ባልረባ ኤሊዛቤት ፔርሰን ባለፈዉ ወር የተያዘች የአንዲት 13 ዓመት ታዳጊ ወጣትን ቃል አብነት ይጠቅሳሉ።

«አምልጣ መምጣቷን ወጣትዋ ገልፃለች።ወላጆችዋ የቦኮ ሐራም ደጋፊዎች እንደነበሩ እና የቦምብ ጥቃት እንድትጥል እደመለመሏ ነዉ-የተናገረችዉ። ወላጆዋ ጥቃቱን እንድታደርስ ሊያስገድዷት ሞክረዉ ነበር።ግን አላደረገችዉም።ታሪኳ እዉነት ከሆነ የቦኩ ሐራም ደጋፊዎች ልጆቻቸዉን ሳይቀር አደጋ እንዲጥሉ ይገፋፏቸዋል ማለት ነዉ።»

ቦኮ ሐራም ጎዳና አዳሪ ወጣቶችን ቦምብ እያስታጠቀ እንደሚያዘምትም አጥኚዋ ይናገራሉ።ከጥቂት ወራት በፊት ካኑ በተባለችዉ ከተማ በርካታ ሰዎችን አጥፍተዉ የጠፉት ወጣቶች ጎዳና አዳሪዎች ነበሩ።አንዳዴ ደግሞ፤ ወይዘሮ ፔርሰን እንደሚሉት ወላጆች ገንዘብ እየተከፈላቸዉ ልጆቻቸዉን ለአሸባሪነት ያዘምታሉ።

ጋዜጠኛ አል አሚን መሐመድ «ለወትሮዉ ሴቶች አደጋ ይጥሉብናል ብለን ጨርሶ አናስብም ነበር ይላል «አሁን ግን፤ይቀጥላል።

«ሰዎች፤ አንዲት ሴት ባጠገባቸዉ ባለፈች ቁጥር ቦምብ ታጥቃ ይሆናል ማለት ጀምረዋል።ሰዎች ከሴቶችና ከልጃገረዶች ጋር ያላቸዉን ግንኙነት በጅጉ ቀይሮታል።አጠቃላይ አመለካከታቸዉ ተለዉጧል።»

Nigeria Anschlag 28.11.2014
ምስል Reuters

ናይጄሪያ ዉስጥ የመጀመሪያዋ አሸባሪ በታጠቀችዉ ቦምብ አጥፍታ የጠፋቸዉ ቦኩ ሐራም ከሁለት መቶ በላይ ሴት ተማሪዎችን ባገተ በወሩ ነበር።ባለፈዉ ዓመት ሰኔ።ቦኩ ሐራም ልጃገረዶችን ለእጥፍቶ ጠፊነት ማዝመቱን መንታ ድል እንደሚያስገኝለት ሥልት ነዉ የሚቆጥረዉ።አንደኛ «ሴቶችም ይዋጋሉ» እያለ ወጣቶች ዓላማዉን እንዲቀበሉ መቀስቀሻ ያደረገዋል።ሁለተኛ ቡድኑን ይበልጥ ተፈሪ ያደርገዋል።

«ሴት አጥፍቶ ጠፊዎች በጥቃቱ መሳተፋቸዉ ለቦኮ ሐራም በጣም ጠቃሚ ነዉ።ምክንያቱም ከፍተኛ እዉቅና ያገኝበታል።ለቡድኑ ሌሎችም ጥቅሞች ያስገኝለታል።ቡድኑ በሰፊዉ ሲታወቅ የሚያሳድረዉም ፍረቻ ይንራል።በጣም ጨካኝ፤ ምሕረት የለሽ መሆኑን ያሳይበታል።»

የናይጀሪያ ባለሥልጣናት ቦኮ ሐራምን ለማጥፋት በተደጋጋሚ ቢዝቱም እስካሁን የቡድኑ መጠናከር እንጂ መዳከሙ አልታየም።ፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታን የሐገራቸዉ ጦር አሸባሪዉን ቡድን መግታት እንዳልቻለ በቅርቡ አምነዋል።ሌላ ስልት ሥለመቀየሳቸዉ ግን የሚታወቅ ነገር የለም።

ሽቴፋኒ ዱክሽታይን

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ