1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኔቶ ስብሰባ የአሜሪካ ማረጋገጪያ

ረቡዕ፣ የካቲት 8 2009

ዩናይትድ ስቴትስ ለምትመራዉ ለሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) የምትሰጠዉን ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደምትቀጥል አዲሱ የሐገሪቱ መከላከያ ሚንስትር አረጋገጡ።

https://p.dw.com/p/2Xd3R
Belgien US Außenminister  James Mattis auf NATO Treffen in Brüssel
ምስል Getty Images/AFP/E. Dunand


መከላከያ ሚንስትር ጄምስ ማቲስ ዛሬ ብራስልስ-ቤልጂግ ዉስጥ ለተቀሩት የኔቶ አባል ሐገራት መከላከያ ሚንስትሮች እንደነገሩት የጦር ተሻራኪዎቹ ድርጅት ለአሜሪካም ሆነ ለተቀሩት አባላቱ በሙሉ የማዕዘን ድንጋይ ነዉ።«በጋራ ለመቆም በመወሰናችን፤ ሽርክናዉ ለዩናይትድ ስቴትስም ሆነ ባጠቀላይ ለአትላንቲክ ማዶ ለማዶ ማሕበረሰብ ጠንካራ መሠረት ነዉ።ፕሬዝደንት ትራምፕ እንዳሉት ለኔቶ ጠንካራ ድጋፍ ያደርጋሉ።ኔቶ ደግሞ በለዉጥ ሒደት ላይ ነዉ። የሚያጋጥሙትን የፀጥታ ፈተናዎች ለመቋቋም እራሱን ማስተካከል አለበት።ይሕ አዲስ ነገር አይደለም።የለዉጡ ሒደት ትንሽ አዝግሞ ይሆናል።ግን ይሕን ማስወገድ አይገደንም።ፍፁም አስፈላጊም ነዉ።አንድ የአዉሮጳ መከላከያ ሚንስትር ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት ከዓለም እጅግ ምርጥ የሆነዉን የመከላከያ ጥቅም የሚያገኙ በሙሉ፤ ነፃነትን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስፈልገዉን ወጪ እንዲጋሩ ቢጠየቁ ተገቢ ጥያቄ ነዉ።አንድ መርሳት የሌለብን ነገር እኛ በኔቶ አማካይነት ከጥቃት የምንከላከለዉ ነፃነትን መሆኑን ነዉ።»አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት ኔቶን «ያረጃ» እና ለአሜሪካ «ሸክም ነዉ» ማለታቸዉ አዉሮፓዉያንን  ክፉኛ አስደንግጦ ነበር።መከላከያ ሚንስትር ጄምስ ማቲስ ዛሬ ከአዉሮጳ አቻዎቻቸዉ ጋር ያደረጉት ስብሰባ በትራምፕ መልዕክት የተደናገጡትን መንግስታት ለማረጋጋት ያለመ ነዉ።የቀድሞዉ ጄኔራል ከአዉሮጳ መከላከያ ሚንስትሮች ጋር በግልፅ ለመነጋገር እና የሌሎቹን ሐሳብ ለመስማት ዝግጁ መሆናቸዉንም አስታዉቀዋል።