1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኔቶ ጉባኤና አዲስ ስልቱ

ሰኞ፣ ኅዳር 13 2003

...በአዲሱ የኔቶ-ሥልት መሠረት ሚሳዬል መከላከያ ጦር መሳሪያ ለመገንባት ግን አለም አቀፍ የሰላም ንቅናቄ ባልደረባ ራይነር ብራዉን እንዳሉት የኔቶ አባላት በፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬጋን ዘመን ለጦር መሳሪያ ከወጣዉ ከፍተኛ ገንዘብ ይበልጥ ቢሊዮነ-ቢሊዮናትን ለመከስከስ ተስማሙ።

https://p.dw.com/p/QFTC
የሊዝበኑ ጉባኤምስል AP

22 11 10


የካቲት 1952 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሊዝበን-ፖርቱጋል የተሰየመዉ ጉባኤ በዋና ፀሐፊነት የመረጣቸዉ ጄኔራል ሔስቲንግስ ሊዮኔል ኢስሜይ እንደ መጀመሪያዉ ዋና ፀሐፊ የገለጡት የድርጅቱ አላማ ዛሬም ብዙ አልተቀየሩም።ፕሬዝዳንት ሐሪ ኤስ ትሩማን የዩናይትድ ስቴትስን አባልነት ሲያፀድቁ-የፀደቀለት ስም-ተልዕኮ፣ ብራስልስ ላይ የተመዘገበለት አባል-እየጨመረ የተጠነሰሰለት ትልም-እየረቀቀ አብሮት አረጀ።የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት-ኔቶ በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ።ሊዝቦኑ-የኔቶ ጉባኤ-መነሻ ዳራዉ ማጣቀሻ፣ የአሮጌ-አዲስ ስልቱ አንድ-ሁለትነት መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብሯችሁን ቆዩ።

ሶቬት-ሕብረትና ዩናይትድ ስቴትስ የመሩና ያስተባበሩት ሐገራት ጦር የናትሲ ጀርመን ጠላቱን አዉድሞ፣ የሁለተኛዉን ትልቅ ጦርነት ድል-አብስሮ፥ የደቀቀችዉን ጀርመን እሁለት ገምሶ ቢቆጣጠራትም ተሸናፊዋ ዳግም አንሠራርታ ጠላቶችዋን ትብቀላለች ከሚል ሥጋት ፈጥኖ አልተልተላቀቀም ነበር።

በመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት ተሸንፋ የነበረችዉ ጀርመን-ባጭር ጊዜ ተደራጅታ ገሚስ ዓለምን ያጋየዉን ሁለኛ ጦርነት ለመጫር የበቃቸዉ-የመጀመሪያዉ ጦርነት አሸናፊዎች በተለይ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ በድል ማግሥት የመዘናጋተቸዉ ስሕተት ዉጤት ተደርጎ ይታይ ነበር።ሁለቱ ሐገሮች ከተባባሪዎቻቸዉ ጋር ጀርመንን ከመቆጣጠሩ ጋር-ጀርመን ዳግም ተደራጅታ ሰወስተኛ ጦርነት ብታዉጅ በጋራ የሚወጉበትን ዉል ዱንክሪክ-ፈረንሳይ ላይ ተፈራረሙ።መጋቢት 1947።

ያዉ ዉል ግን የለንደንና የፓሪስን ሥጋት የሚያስወግድ አልሆነም።እናም ቤልጅግን፣ ኔዘርላንድስን እና ሉክሰንበርግን (ቤኔሉክስ ይባላሉ አንድ ላይ) ጨምረዉ ብራስልስ ላይ «የምዕራብ አዉሮጳ ሕብረት የመከላከያ ድርጅት» ያሉትን የጋራ መከላከያ ስምምነትን ተፈራረሙ።መጋቢት 1948ዲሚትሪ ሮጎዚኒ-አሁን በኔቶ የሩሲያ አምባሳደር ናቸዉ።ከዘንድሮዉ የኔቶ ጉባኤ በፊት ጉባኤዉ የግዙፉን አንጋፋ የጦር ድርጅት ሥልትን ሊቀየር ነዉ-እያሉ የአለም ግዙፍ መገናኛ ዘዴዎች ማራገባቸዉ ለሩሲያዉ ዲፕሎማት የቸከ ነበር።

«ይኸ ያዉ በአሜሪካ የሚዘወር ቁልፍ፣ እና የአሜሪካ የምትወስነዉ ነዉ»
አሉ-አርብ።

በዋሽንግተንና በሞስኮ የተመራዉ ተባባሪ ጦር በ1945 የገደለዉን የበርሊን አንበሳ አስከሬንን ለመደብደብ፥ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ በ1947-ባመቱ ደግሞ ቤኖሉክሶችን አክለዉ ባንድ-ሲያብሩ ድፍን ምሥራቅ አዉሮጳን የጨመደደዉን-የሞስኮን ሕያዉ-ሐያል አንበሳ-ብዙም ከቁብ የቆጠሩት አይመስሉም ነበር።አሜሪካንንም ለመቀየጥም-ጓጉ እንጂ አልጨመሩም ነበር።ባመቱ ግን በርግጥ ዘየዱ።
አዲሲቱን የአለም ልዕለ ሐያል ሐገር ከማሕበሩ ቀየጡ።ሚያዚያ 1949።የሰሜን አትላንቲክ የጋራ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ተመሠረተ።ኔቶ-በምሕፃሩ።

NATO Hauptquartier Brüssel
የኔቶ ጠቅላይ ዕዝ-ብራስልስምስል Alen Legovic

አላማዉም በአባል ሐገራት ላይ በተለይም ከሶቬት ሕብረት የሚሰነዘር ጥቃትን መከላከል-ቀዳሚ ጀርመንን መከታተል-ተከታዩ አደረገ።እንደ መጀመሪያዉ የድርጅቱ ዋና እንደ እንደ ብሪታንያዊዉ ጄኔራል ሔስቲንግስ ልዮኖል ኢስሜይን ግን- የድርጅቱን የዚያ ዘመን አላማ ባጭር አረፍተ ነገር የገለፀዉ ግን አልነበረም።
«ሩሲያዎችን ማባረር፣ አሜሪካንን መያዝ፣ ጀርመንን እንደደፈቁ መቀጠል» አሉ ያኔ።

ጄኔራል ኢስሜይን የመረጠዉ ጉባኤ በተጠናቀቀ ባመቱ ክሬምሊንን ሙሉ በሙሉ የተቆጧጠሩት ኒኪታ ክርስቾቭ በኮሚንስታዊቷ ልዕለ-ሐያል ሐገርቸዉና በተባባሪዎቻዋ ላይ ያነጣጠረዉን የምዕራብ ሐገራት የጦር ድርጅት የሚፃረር ሌላ ድርጅት ለመመስረት-አንድ ሁለት ማለት ሲጀምሩ-ኢስሜይ «ጀርመንን መድፈቅ» ያሉት የኔቶ መርሕ-ቢያስ ለምዕራብ ጀርመን ተሠረዘ።የሶቬየት ሕብረትና የስድስት የምሥራቅ አዉሮጳ ሐገራት መሪዎች የኮሚንስቶቹን የጦር ተሻራኪ ድርጅት ለመመስረት ዎርሶ-ፖላንድ ላይ ሲሰበሰቡ፥ ፓሪስ ላይ ተሰይሞ የነበረዉ የኔቶ ጉባኤ የምዕራብ ጀርመንን ሙሉ አባልነት አፀደቀ።ግንቦት ዘጠኝ 1955።

ለኔቶ-ታሪካዊ እመርታ፥ ለምዕራብ ጀርመን፥ በጣሙን ለመራሔ-መንግሥት ኮንራድ አደናወር ደግሞ በርግጥ ታላቅ ድል ነበር።የተዋደችዉ ጀርመን ዛሬ-ከስልሳ አመት በፊት ሊደፍቃት ከተመሠረተዉ ድርጅት ዋሳኝ አባላት አንዷ፥-መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከሊዝበኑ ጉባኤ በፊት እንዳሉት ደግሞ ከአዲሱ ስልት ቀያሾች ዋነኛዋ ናት።

«በርግጥም የተልዕኮዉ የአዲስ ሥልት ፅንሰ ሐሳብ አለን።ባንድ በኩል ከአደገኛ ጦር መሳሪያዎች ጥቃት የሚከላከልን (ሥልት)፥ በሌላ በኩል ደግሞ የጦር መሳሪያ በተለይ ደግሞ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ቅነሳ ጉዳይን ልንዘነጋዉ የማይገባ ጉዳይ ነዉ።»

ጄኔራል-ኢስሜይን ከሐምሳ-ስምንት አመታት በፊት ኔቶ-ይይዛታል ያሏት ዩናይትድ ስቴትስ ያን ግዙፍ ድርጅት እንደያዘች-የሩሲያዉ አምባሳደር በቀደም እንዳሉት ደግሞ ባሻት እንደዘወረች ዛሬም ቀጥላለች።ከጥቂት አመታት በፊት ዩናይትድ ስቴትስ አስጊ ከሚባሉት ኢራንና ሰሜን ኮሪያን ከመሳሰሉ ሐገራት ሊተኮስ የሚችል ሚሳዬልን የሚያከሽፍ ሚሳዬልና የሚሳዬል መቆጣጠሪያ ሬዳር ፖላንድና ቼክ ሪፐብሊክ ዉስጥ ለመገንባት ማቀዷ የሩሲያን ሐይለኛ ተቃዉሞ-ብዙዎቹን የኔቶ አባል ሐገራትን ቅሬታ አትርፎ ነበር።

Bundesrepublik Deutschland wird 1955 Mitglied der NATO
1955-ም/ጀርመን የኔቶ አባል ሆነችምስል dpa - Bildfunk

ዛሬ ግን የኔቶ-ዋና ፀሐፊ አንድረስ ፎግሕ ራስሙስን ባለፈዉ አርብ ለሊዝበን ጉባኤተኞች እንደተናገሩት የሚሳዬል መከለከያ ግንባታዉ-የአሜሪካ፥ የፖላንድ ወይም የቼክ ሪፕብሊክ ብቻ አይደለም።የሃያ-ስምንቱም አባል ሐገራት ፍላጎት፥ የድርጅቱ አዲስ ሥልት አብይ-መተክል እንጂ።

«የዘመኑን ጥቃት መከላከል የሚችል ዘመናይ የመከላከያ ሐይል እንገነባለን።በመላዉ አለም ከሚገኙ ወዳጆቻችን ጋር እንተባበራለን።ከሩሲያ ጋር ያለንን ግንኙነት አዲስ ሥልታዊ ወዳጅነትን ለመመሥረት ባለመ መልኩ እናጠናራላለን።የጦር ተጓዳኙን የበዛ ወጪን ጡንቻዉን በሚያዳብሩ መስኮች ላይ አዉለን ቀረጥ ከፋዮቻችን ካወጡት ገንዘብ ጋር የሚመጣጠን የደሕንነት ዋስትና እንዲያገኙ እናደርጋለን።በነዚሕ ምክንያቶች ይሕ ጉባኤ በኔቶ ታሪክ እጅግ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ጉባኤዎች አንዱ ነዉ።»

የታሪክ ዑደት የመጀመሪያዉ የኔቶ ዋና ፀሐፊ የተመረጠበትን ጉባኤ ያስተናገደችዉ ሊዝበን አዲስ የተሰኘዉን የድርጅቱን ሥልት ያፀደቀዉን ጉባኤ አስተናጋጅ ማድረጉ ራሱ ልዩ አጋጣሚ ነዉ።

እርግጥ ነዉ ከሶቬት ሕብረት መፈረካከስ ከአስር-አመት በሕዋላ በ1999 የተሰየመዉ የመሪዎች ጉባኤ የድርጅቱን ተልዕኮ ከአዲሱ አለም-ሥጋት ጋር ለማጣጣም ወስኖ ነበር።ይሁንና በተለይ ዩናይትድ ስቴትስ በ2001 በአሸባሪዎች ከተጠቃች ወዲሕ የድርጅቱ ትኩረት በፀረ-ሽብር ዘመቻ ላይ ያነጣጠረ ነበር።

ከያኔ እስካሁን የብቸኛዉ ግዝፉ የጦር ተሻራኪ ድርጅት ጉባኤ ሥለ አለም አቀፉ የፀረ-ሽብር ዘመቻ በጣሙን አፍቃኒስታን ሥላሚያዘምተዉ ጦሩ፥ ጦሩ ሥለሚያደርገዉ ዉጊያ፥ ከመነጋገር-መወሰን ባለፍ ብዙም ያወሳ-የወሰነዉ ጉዳይ አልነበረም።ያሁኑ ጉባኤ ግን የአፍቃኒስታኑ ዘመቻ ሥለሚያበቃበት ጊዜና ሁኔታ ወስኗል።የፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ መስተዳድር አፍቃኒስታን የሰፈረዉን የአሜሪካ ጦር ከሐምሌ 2011 ጀምሮ ማስወጣት እንደሚጀምር አስታዉቆ ነበር።የሊዝበኑ የኔቶ ወሳኝ ጉባኤም -የአሜሪካኖችን ሥልት-የአዲስ ሥልቱ አካል አደረገዉ።ዋና ፀሐፊ ራስሙስን።

«ከመጪዉ አመት መጀመሪያ ጀምሮ የአፍቃኒስታን ወታደሮች የሐገሪቱን ፀጥታ የማስከበሩን ሐላፊነት መረከብ ይጀምራሉ።አላማዉ የአፍቃኒስታን ጦር እስከ 2014 ማብቂያ የመላዉ ሐገሪቱን ፀጥታ የማስከበሩን ሐላፊነት እንዲረከብ ነዉ።»

NATO in Afghanistan
የኔቶ ጦር በአፍቃኒስታንምስል AP

የዋሽንግተኑ ሥልት-የኔቶ አዲስ ሥልትነቱ ሊዝበን ላይ እንደፀደቀ የካቡልም አላማ-ሥልት ሆነ። ፕሬዝዳት ኸሚድ ካርዛይ-አርብ።
«ይሕ የአለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዉሳኔ (ፅናት) ከአፍቃኒስታን ሕዝብ ቁርጠኝነትና ብርቱ ሥራ ጋር የሚጣጣም ነዉ።የሁለቱ ጥምረት የተሳካለት፥ ዘላቂና የማይቀበለስ ሽግግር ይፈጥራል።»

የሊዝበኑን ጉባኤ ከኔቶ ወሳኝ ጉባኤዎች አንዱ ካደረጉት ምክንያቶች፣-አንዱ ከሶቬት ሕብረት ወይም ከተባባሪዎችዋ የሚሰነዘርን ጥቃት ለመከላከል ሲታጠቅ-ሲደራጅ ከሐምሳ ዘመን በላይ ያስቆጠረዉ ድርጅት ከሩሲያ ጋር ለመተባበር መስማማቱ ነበር።ከጉባኤዉ በፊት ከሞስኮ ጋር መተባበሩ የድርጅቱ አዲስ ሥልት አካል እንዲሆን ዩናይትድ ስቴትስ አጥብቃ ታግላ-ተሟግታም ነበር።ጉባኤዉ ትብብሩን ሲያፀድቅ-ለራስሙሰን ወሳኝ እንደሆነ ሁሉ ለፕሬዝዳት ኦባማም ልዩ ሆነ።

«ከሩሲያ ጋር ያለዉን ግንኙነት ባዲስ መልክ ለማደራጀት በጋራ አበክረን ሰርተናል።ይሕም ለሁለቱም ሐገሮቻችን ተጨባጭ ጥቅም አትርፏል።አሁን ደግሞ የኔቶንና የሩሲያን ግንኙነት ባዲስ መልክ እየገነባን ነዉ።ሩሲያን እንደ ወዳጅ ነዉ-የምናያት።»

ኔቶ-ከአፍቃኒስታን ጦሩን የማስወጪያ ጊዜዉ ይሁን-ከሩሲያ ጋር አዲስ ወዳጅነት መመሥረቱ ግዙፉ ብቸኛዉ የጦር ተሻራኪ ድርጅት የዋሽንግተንን ዉሳኔ-ፍላጎት ከማፅደቅ-መቅዳት ባለፍ በራሱ መቆሙን አጠራጣሪ ያደርገዉ ይሆናል።

ከዚሕ ይልቅ የሊዝበኑ ጉባኤ ወሳኝ-ልዩ የመሆኑን ያክል በተለይ የሚሳዬል መከላከያ ግንባታን በተመለከተ ያሳለፈዉ ዉሳኔ ለሩቁ ታዛቢ ግራ አጋቢ ብጤ ነዉ።በኔቶ የሩሲያዉ አምባሳደር አገላለጥ የድርጅቱን ቁልፍ-የያዘችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ባለፈዉ ሚያዚያ ከሩሲያ ጋር «አዲስ» የተሰኘዉን የሥልታዊ ጦር መሳሪያ ቅነሳ (START-ይሉታል እነሱ) ዉል ተፈራርማለች።

የዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ዉሉን ላለማፅደቅ ባለፈዉ ሳምንት እያንገራገረ ነበር።ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ወደ ሊዝበን ከመጓዛቸዉ በፊት ምክር ቤቱ ዉሉን እንዲያፀድቅ አሳስበዋል።
«ዉሉ ካልጸደቀ በኢራን ላይ ተፅእኖ ለማሳረፍ የገነባዉን ትብብር ላደጋ እናጋልጠዋለን።አፍቃኒስታን ለሰፈረዉ ጦራችን በሩሲያ በኩል ትጥቅና-ሥንቅ የምንልክበትን መተላለፊያም መሰናክል ይገጥመዋል። ከዚሕም በተጨማሪ ዉሉ ካልጸደቀ አሜሪካ የኑክሌር ደሕንነትን ለማስከበር ለአስርታት ያበረከትችዉን የመሪነት ሚና እናሳጣታለን።ደሕንነታችንና በአለም ላይ ያለን የመሪነት ሥፍራ-ያጠያይቃል።»

ፕሬዝዳት ኦባማ ከሩሲያዉ አቻቸዉ ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ጋር የተፈራረሙት ዉል ከፀደቀ-ከአለም የኑክሌር አረሮችን ዘጠና በመቶዉን የያዙት ሁለቱ ሐገሮች የኑክሌር አረሮቻቸዉን እና ቁጥር የረጅም-ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳዬሎቻቸዉን ቁጥር ይቀንሳሉ።

የኑክሌር ሚሳዬል ቁጥር እንዲቀነስ አብከረዉ መጣራቸዉን-የተናገሩት፥ከሜድቬዴቭ ጋር የፈረሙትን ዉል ምክር ቤታቸዉ እንዲያፀድቅ የሚሟገቱት ኦባማ ኔቶ ፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬል እንዲገነባ የሊዝበኑ ጉባኤ በመወሰኑ ግን ተደስተዋል።
«በዘመናችን ላለዉ ሥጋት መላዉ ሕብረታችን አፀፋ መስጠት እንዲችል ያደርገዋል።ዜጎቻችንን ከሐገር አቋራጭ ሚሳዬል ጥቃት ለመከላከል መቁረጣችንን ያመለክታል።»

አለም በምጣኔ ሐብት ድቀት-ግራ ቀኝ እየተላጋች ነዉ።ወይም ይሉናል።ሚሊዮኖችን የሚያረግፈዉን በሽታ፥ ረሐብ፥ ድሕነትና የተፈጥሮ መዛባትን ለማቃለል-የበለፀገዉ አለም ከአጠቃላይ አመታዊ ገቢዉ 0.7 ከመቶ ለማዋጣት የገባዉን ቃል-ገቢር ለማድረግ እያቅማማ ነዉ።በአዲሱ የኔቶ-ሥልት መሠረት ሚሳዬል መከላከያ ጦር መሳሪያ ለመገንባት ግን አለም አቀፍ የሰላም ንቅናቄ ባልደረባ ራይነር ብራዉን እንዳሉት የኔቶ አባላት በፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬጋን ዘመን ለጦር መሳሪያ ከወጣዉ ከፍተኛ ገንዘብ ይበልጥ ቢሊዮነ-ቢሊዮናትን ለመከስከስ ተስማሙ።

ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ