1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የንቅሳት ባህል

ሐሙስ፣ ሰኔ 16 2003

አንድ ወጣት ነዉ አሉ! በገጠር ፍየሎቹን ይዞ በጠዋት ለግጦሽ ሳር ፍለጋ ሲወጣ አንዲት ልጃገረድ የዉሃ እንስራዋን ይዛ ዉሃ ልትቀዳ ወደ ወንዝ ስትወርድ ያገኛታል። ታድያ ዉበትዋን አይቶ ድንግጥ ያለዉ ወጣት እረኛ እንዲ ገጥመላት አሉ!

https://p.dw.com/p/RVFI
ምስል picture-alliance / dpa

በተራራ ፍየል ይመስላል ሰርገኛ፣ የእገትዋ ንቅሳት አለዉ አማረኛ
ንቅሳትሽማ ልብ ያስደነግጣል፣ ከጀግናዉ ባለቤት ከተዋበች በልጦአል። አለ አሉ!


ንቅሳት ከአንድ የእድገት ደረጃ ወደ ሌላ መሸጋገርን፣ መአረግን ሃይማኖታዊ እና መንፈስነትን፣ ጀግንነትን ወሲባዊ መስብዕን፣ ወላድነትን ፍቅርን ቅጣትን እንዲሁም ከለላን አመላካች ሆኖ ለበርካታ ዘመናት ማገልገሉ ይገለጻል፣ ንቅሳት የባሮች የእስረኞች መለያ ሆኖ ማገልገሉም አንዳንድ ጽሁፎች ያሳያሉ። በምዕራባዉያን ዘንድ አሁን አሁን ባላንቅሳቱ፣ ባለዉቅራቱ በርከት ብሎ ይታያል! በተለይ በወጣቱ ዘንድ። ታድያ ዉቅራት ማለት ንቅሳት ከባህር ማዶ ተሻግሮ ዛሪ እዚህ በፈረንጆቹ ዘንድ በርከት ብሎ ይታይ እንጂ በዚህ በምዕራባዉያኑ ዘንድ የሚኖሩ አፍሪቃዉያን ንቅሳት መነሻዉ ከአፍሪቃ መሆኑን በኩራት ሲገልጹ ይሰማል። አንዳንድ ኢትዮጽያዉያን በበኩላቸዉ ዉቅራት ንቅሳት መነሻዉ እዝያዉ በኢትዮጽያችን መሆኑን በርግጠኝነት የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም። እዉነት ዉቅራት መነሻዉ ከኢትዮጽያ ይሆን ይህን ጥያቄ ይዘን ወደ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ጥናት መደረጉን ለማወቅ ሄደን ነበር በንቅሳት ላይ እስካሁን ጥናት ያደረገ አልተገኘም፣ ግን በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት የቤተ ክነት ሊቅ ቀሲስ መላከ ምክር ከፍ ያለዉ መራሄን ስለ ቅሳት የሚሉት አላቸዉ።

Henning Forster zeigt stolz sein Tattoo
ምስል DW

ሰዉነትን በንቅሳት ማሸለም ከሃያኛዉ ክፍለ ዘመን ወዲህ በዘመናዊ መልኩ በበርካታ የአለማችን ክፍሎች እንደተስፋፋ ጽሁፎች ያመለክታሉ። በተለይ በሰሜን አሜሪካ በጃፓን በአዉሮጻ ዉስጥ ተወዳጅነቱ ጎልቶ ይታያል። በነዚህ ክፍለ አለሞች የንቅሳት ባህል ሊስፋፋ የቻለዉ የቴክኒክ እና የስነ-ጥበብ ስልጠና ያላቸዉ አዳዲስ ባለሞያዎች ወደ ዘርፉ በመግባታቸዉም እንደሆነ ተመልኮአል። የንቅሳት ቀለም እና መሳርያ በየግዜዉ መሻሻልም ለጥበቡ ጥራት ማደግ አስተዋጽኦ አድርጎአል። በአገር ቤት አሁን አሁን ከሚታየዉ ንቅሳት መካከል፣ የመስቀል የጠባቂ መልአክ፣ የሾህ አክሊል ያደረገ የእግዜር ምስል፣ የህጻናት መላአክ የመሳሰሉ ሁሉ መኖራቸዉ ምናልባት ከጌጥነቱ ባሻገር ወደ ሚቀጥለዉ አለም የመግብያ መታወቅያ ይሆን እንዴ ያሰኛል። በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነዉ ወጣት ዳንኤል አክሎም ቼንጅ ታቶ በተሰኘዉ ሱቁ በዘመናዊዉ ቴክኒክ ነቃሽ ነዉ። ዳንኤል ስለ ንቅሳት ያለን አለ!

ይሄ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ሰባት የዘመናዊ ነቃሾች አሉ የተባለዉ ዘመናዊዉ ንቅሳት ታቱ ወይም ታቶ ይባላል በስያሜዉ። ታቶ የሚለዉ የዘመናዊ ንቅሳት ስያሜ የመጣዉ በደቡብ ፓሲፊክ ዉቅያኖስ ላይ ከሚገኝዉ የታሂቲ ደሴት ነዋሪዎች የሰጡት ስያሜ መሆኑ ተጥቅሶአል። የዘመናዊዉ የመንቀሻ መሳሪያ የኤሌትሪክ ሆኖ ማሹኑ ላይ በተገጥመ ጥቃቅን መርፊ ነዉ ንቅሳቱ የሚከናወነዉ!
በሰሜናዊ የአገራችን ክፍል ብዙ ሴቶች ግንባራቸዉን ጉንጫቸዉን አንገታቸዉን ድዳቸዉን ተነቅሰዉ እናገኛለን። የመንቀሻ መሳርያቸዉም ከትዉልድ ትዉልድ የሚተላለፈዉ ባህላዊ የመንቀሻ መሳርያ አጋም እሾህ፣ መርፊ፣ አልያም ወስፊ ይሆናል። ታድያ በባህላዊዉ ንቅሳት አምራ አጊጣ የባህላዊ ቀሚስዋን አጥልቃ ያየ ሰዉ ነቃሽዋንም ተነቃሽዋንም እንዲህ ያሞካሻል!
ተነቀሽ ተነቀሽ ተነቀሽ በሾክ፣ ትሆኝ እንደሆን የናትሽ ምትክ።
ንቅሳትሽማ መቁጠርያ የሚመስለዉ፣ ያን ዉበትሽን አስበለጠዉ ከሰዉ።
የግንባርሽ መስቀል የአንገትሽ ድርድር፣ ያኑራት ዘላለም ነቃሽን በምድር።

Tattoo Expo in der Schweiz - tätowierter Kopf
ምስል AP

ከዉበት አንጻር የአገራችን እረኛ በወጣትዋ ዉበት ተማርኮ ሲዘፍን እንደ ፎገራ ላም አንገተ ዝንጉርጉር...... ፎገራ ደቡብ ጎንደር ነዉ የሚገኝ፣ የአለቃ ገብረሃና አገር፣ የላም አገር ነዉ አሉ!
እና እንዲህ ሲል አዜመ እረኛዉ!
እንደ ፎገራ ላም አንገተ ዝንጉርጉር፣ መንገዱን አስታ ሰደደችን በዱር።
አንገተ ንቅሳት መልከ ዉዳዉድ፣ ምን ትጠቀሚያለሽ አንቺን ብዪ ባብድ።
የጥርሷ ንቅሳት እየታየኝ ዘርፉ፣ እሄድ እሄድ እና እላለሁ እረፉ።
የአንገቷ ንቅሳት ይመስላል ዝናር፣ እስዋን ያገኘ ወንድ ጀግና ነዉ የምር።
በዚህ በአዉሮጻ በዘመናዊዉ ንቅሳት ክንድ ላይ ደረት ላይ አልያም ባት ላይ ሌላዉ ተመልካች ከሚያያቸዉ የንቅሳት ስእሎች መካከል ለሁለት የተሰበረ ልብ፣ በቀስት የተወጋ፣ በሾህ የታጠረ ከዝያም እየደማ ያለ ልብ፣ የስም ፊደላት፣ አበባ፣ ለጸሎት የተዘረጉ እጆች፣ ከአይን በታች እየወረደ ያለ እንባ፣ የእናት የእህት በህይወት አለመኖራቸዉን የሚያሳይ ማስታወሻ ሁሉ ይቀለማሉ፣ ወይም
ንቅሳትዋን አይቶ የሚመጣ ወንድ፣ ማን ይቀበለዋል ካልያዘ ጎመድ።
አየሁት ዉበትሽን ከእገትሽ በላይ፣ የዛ የጀግና ዘር የበላይ ነሽ ወይ።
ድንቅ ነዉ ዉበትሽ ሲያዩት በትኩረት፣ ነቃሽ ነች እና ጠቢብ በእዉነት።
እየተባለች የምትሞገስ ነቃሽ ባገራችን በስራዋ ጥራት እንዲህ ስትመሰገን፣ በዚህ በአዉሮጻ ደግሞ የስም ፊደል ወይም የእግዜርን መጠርያ ፊደል ዘለዉ ወይ እረስተዉ ሳይነቅሱት ይቀሩ እና ከተነቀሰ በኋላ በላጲስ አይታረም ሆኖ ይቀራል። ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል እንዲሉ! እዚህ በጀርመን ታዋቂ እስፖርተኞች ሙዚቀኞች የከንፈር ወዳጆችዉን በፍቅር ሞቅታ ፈረስ ተቀምጠዉ ሳለ የፍቅረኛዋን ፎቶ ወይም ስም በክንዷ ላይ አልያም የፍቅረኛዉን ፎቶ ባቱ ላይ አስነቅሶ ፍቅሩ ሲቀዘቅዝ፣ ሲቀር እሱን ለማጥፋት የሚደረገዉ ጥረት፣ የቆዳ በሽታ፣ አልያም የሰዉ መጠቋቆምያ ሆነዉ ሲቀሩ ማየቱ የተለመደ፣ የብዙሃን መገናኛዉም ይህንኑ ታሪክ እየሰበሰበ ማሳየቱ አዝናኝ ሆንዋል።

29.03.10 DW-TV Global 3000 THAILAND TATTOOS 2

ከዚህ ባሻገር አንዳንድ በስፖርት የዳበር አካል ያላቸዉ ጎልማሶች በክንድ እና በደረታቸዉ ላይ ተናካሽ ዉሻ የሚመስል አልያም የአንበሳ የነብር ቅርጽ ወይም የተጥመለመለ እባብ አስነቅሰዉ ማየቱ ለተመልካች እንስሶቹን መዉደዱን መግለጹ ይሁን? እዳትጠጉኝ! ማለቱ አንዳንድ ግዜ አጥራጣሪ አይሆንም። ግን በምዕራቡ አለም በተለያየ ሁኔታ ሰዉነትን በተለያየ ቀለም ማስነቀሱ እየሰፋ ያለ ባህል ሆንዋል።

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ