1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የንግሥት ሙሁሙዛ የቅኝ ግዛት ተጋድሎ

ሐሙስ፣ መጋቢት 13 2010

ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ግድም ምሥራቅ አፍሪቃ ውስጥ አንዲት ኃይለኛ ሴት ይኖሩ ነበር፤ ንግሥት ሙሁሙዛ ይባላሉ። ሴቶች አብዛኛውን ጊዜ በአደባባይ ጎልተው በማይታዩበት በዚህ ወቅት እኚህ የሩዋንዳው ንጉሥ ባለቤታቸውን ያጡት እጓለ-ምዊት ለበርካታ ነገሮች ታግለዋል። ናያቢንጊ በሚል መጠሪያም የነጻነት ተጋድሎ አርማ ኾነዋል።

https://p.dw.com/p/2tbmd
African Roots Muhumusa
ምስል Comic Republic

ንግሥት ሙሁሙዛ

ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ግድም ምሥራቅ አፍሪቃ ውስጥ አንዲት ኃይለኛ ሴት ይኖሩ ነበር፤ ንግሥት ሙሁሙዛ ይባላሉ። ሴቶች አብዛኛውን ጊዜ በአደባባይ ጎልተው በማይታዩበት በዚህ ወቅት እኚህ የሩዋንዳው ንጉሥ ባለቤታቸውን ያጡት እጓለ-ምዊት ለበርካታ ነገሮች ታግለዋል። የተቀሙትን ፍትሕ ለማስመለስ ብቻ ሲሉ ሳይኾን የተፋለሙት የቅኝ ገዢዎችን ጭቆና ተቃውመው በተደጋጋሚ ለፍትሕ ታግለዋል። ናያቢንጊ በሚል መጠሪያም የነጻነት ተጋድሎ አርማ ኾነዋል።

የሙሁሙዛ ፍልሚያ ለራስ ከመታገል ይጀምራል። በአንድ ወቅት የሥልጣን ማዕከሉ የነበሩት እኚህ ሴት ሥልጣናቸውን ለማስመለስ የተደረገ ፍልሚያ። የሩዋንዳው ንጉሥ ኪጌሊ አራተኛ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1895 ሲሞቱ የንግሡ ባለቤት እና ሕጋዊ ወራሽ ቢኾኑም ገለል እንዲሉ የተተበተበባቸውን ሴራ ለመበጣጠስ ታግለዋል። ሩዋንዳን በሚያስተዳድሩት የጀርመን ቅኝ ገዢዎች እና የሩዋንዳ ሥርዓታቸው ላይም ነፍጥ አንስተዋል። የግል ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሲሉ የጀመሩት ትግል ግን የብሪታንያ አስተዳደር ስር የነበሩት ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ እና የቤልጂግ ኮንጎ ቅኝ ገዢዎች ላይ ለመቀጣጠል አፍታም አልወሰደበት።    
ንግሥቲቱ ተጽእኖዋቸው መጠናከር የጀመረው ወዲያው ነበር ይላሉ በኡጋንዳ ማኬሬሬ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰሩ ምዋምቡትሲያ ንዴቤሳ።.

African Roots Muhumusa
ምስል Comic Republic

"ሙሁሙዛ ኅብረተሰቡን ያስተባበሩት መንፈሣዊ እሴቱን በመጠቀም ነው። ናያቢንጊ በሚል የሚታወቀውን ፈንጋጭ ሥርዓተ-አምልኮ ተፋላሚዎቻቸውን ለማደራጀት እና የትግል መንፈሳቸውን ለማነቃቃት እንደ ርእዮተ-ዓለም ተጠቅመውበታል።"

ሙሁሙዛም የናያቢንጊ መንፈስ እንደኾኑ ምናልባትም ከምዕተ-ዓመታት በፊት የነበሩ ንግሥት መንፈስ እንደኾኑ አድርገው ራሳቸውን አቅርበዋል። በዚህ መንገድም እኚህ አፍሪቃዊት አርበኛ በምሥራቅ አፍሪቃ ቅኝ ገዢዎችን መገዳደር ብቻ ሳይኾን ለመፋለምም ደፍረዋል። ስለ ንግሥት ሙሁሙዛ የምናውቀው ኃይለኛ፣ ብልህ እና ባለ ግርማ-ሞገስ እንደነበሩ ነው። ስለእሳቸው ብዙም ዐይታወቅም። 

"የሴቶች ታሪክ ከታሪክ መዝገብ ውስጥ ተሠርዞ ወጥቷል። ምክንያቱም ታሪክ የሚጻፈው ሥልጣኑን በጨበጡት ነው። በቃል የሚወረሰው ታሪክ ደግሞ አገልግሎቱ በወንዶች እና በንጉሦች ነው። የኢምፔሪያል ቅኝ ገዢዎች ታሪክ ወንዶችን የሚገድል በአንጻሩ አውሮጳን ከፍ ከፍ አድርጎ ሲያወድስ አፍሪቃን ደግሞ ያኮስሳል። ይኼ ታዲያ በሴቶች ላይ ክፋቱ እጥፍ ድርብ ነው፤ ሴቶች አንድም አፍሪቃዊ በመኾናቸው በሌላም በሴትነታቸው ከታሪክ መዝገብ ይፋቃሉ።"

የቅኝ ገዢዎች መዛግብት የሙሁሙዛ ታጋዮች በአካባቢው የሚገኙ ወታደሮችን እንደተገዳደሩ ይጠቁማሉ። በስተመጨረሻ ግን የንግሥቲቱ ልዩ ምትኃታዊ ኃይል ዘመናዊውን ጦር መሣሪያ ሊቋቋም አልተቻለውም። በ1913 ብሪታንያውያን ንንግሥት ሙሁሙዛን አስረው ካምፓላ ከተማ ሜንጎ ውስጥ ወደሚገኘው ጦር ሠፈራቸው ላኳቸው። ከ30 ዓመታት በኋላ ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስም እዚያ ኖረዋል። ዛሬ እምብዛም በስፋት ባይታወቁም ታሪካቸው ግን ሊታወስ እና ሊነገርለት ይገባል ይላሉ ንዴቤሳ።   

African Roots Muhumusa
ምስል Comic Republic

"በዚያ ዘመን የነበረውን ሥርዓት በመገዳደር የትግሉን ሌላ አቅጣጫ የሚወክሉ በመኾናቸው ስለእሳቸው ብዙ ሊነገር ይገባል። የዚያን ጊዜም ከብዙ ነገር መገለል የሚሰማቸው ሁሉ እምቢኝ ብለው እንዲነሳሱ የመነቃቃት አብነት ይኾናሉ።"

ንግሥት ሙሁሙዛ ታሪካቸው በአፍሪቃ እምብዛም ባይታወቅ በራስ ተፈሪያን ንቅናቄ ውስጥ ግን ተካቷል።  በዓለም ዙሪያም ጸረ የዘር መድልዎ አገዛዝ ትንቅንቅ ተምሳሌት ተደርገው ይወሰዳሉ። ናያቢንጊ የተሰኘው ሥርአተ አምልኮዋቸውም የራስ ተፈሪዎች ንቅናቄ ቅርንጫፉ ናያባንጊ አካል መኾን ችሏል። 

ጄን አዬኮ/ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ